
13/09/2025
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል
+++++++++++++++
¶ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከአርባምንጭ ከተማም ሆነ ከዙሪያው ለሚመጡ ታካሚዎች የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል (ዶ/ር) አስታወቁ።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሆስፒታሉ እስካሁን ምንም አይነት አገልግሎት አየሰጠ አይደለም በሚል ከተሰራጨው መረጃ ጋር ተያያዞ የፕሬሰ መረጃ ማጣሪያ ያናገራናቸው የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል (ዶ/ር)፤ ከእውነት የራቁ ሀሰተኛ መረጃዎች ናቸው። ሆስቲታሉ ከተመረቀ አንድ አመት የሞላው ቢሆንም የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሆስፒታሉ ሙሉ አገልግሎት ያልጀመረው የቀዶጥገና መስጫ፣ የጽኑ ህክምና ክፍሎችና ተኝቶ ህክምና ክፍሎች የማስተካከያ ስራዎችን እየሰራን ነው ያሉቱ ፕሬዚዳንቱ አብዛኞቹን ተጠናቀዋል። የተወሰኑ ስራዎችን እንደጨረስን ሙሉ አገልግሎት የምንጀምር ይሆናል ብለዋል፡፡
ሆስፒታሉ በቀዶ ሕክምና፣ በውስጥ ደዌ፣ በማህጸንና ጽንስ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል። በክልሉና በአጎራባች ክልሎች ለሚገኙ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎች አገልግሎት መስጠት የሚያሰችል አቅም እንዳለው ተገልጿል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል።
በገነት ኃይለማሪያም
#መረጃ