Harambee radio 98.7

Harambee radio 98.7 [email protected]
ሀገራዊ እና አህጉራዊ ህብረታችንን ጠብቀን ወደተራራው ጫፍ ለመድረስ Arts & Entertainment

23/08/2023

በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ጡረታ ያልተከፈላቸው አረጋውያን በምግብ እጥረት እየሞቱ መሆኑ ተሰማ

በትግራይ ክልል ከሁለት ዓመታት በላይ የጡረታ ደመወዝ ያልተከፈላቸው አረጋውያን በምግብ እጥረት ለሕልፈተ ሕይወት እየተዳረጉ መሆኑን የክልሉ አረጋውያን ማኅበር ገልጿል፡፡
ከዓመታት በፊት ጡረታ የወጡ አረጋውያን ብዛት 75 ሺሕ ሲሆን፤ አሁን ላይ ቁጥራቸው ወደ 100 ሺሕ የሚጠጉ መሆናቸውን የክልሉ አረጋውያን ማኅበር ያሳወቀ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመታት በላይ የጡረታ ደመወዝ ያልተከፈላቸው አረጋውያንም በምግብ እጥረት እየሞቱ መሆኑን የማኅበሩ ሊቀመንብር አቶ አርዓያ ገሠሠ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የሰባት ወር የሚሆን ተብሎ የጡረታ ደመወዝ ቢለቀቅላቸውም፤ የተወሰኑ ሰዎች ሲያገኙ አብዛኛዎቹ ገና በመጠባበቅ ላይ እንዳሉም ሊቀመንበሩ አክለዋል፡፡
አቶ አርዓያ ለሁለት ዓመታት የጡረታ ደመወዝ አልተከፈላቸውም ከተባሉት አረጋውያን መካከል በምግብ እጥረት የሞቱት ምን ያህል እንደሆኑ አለመታወቁን ጠቅሰው፤ የፌዴራሉ መንግሥት ይህን ችግር እንዲቀርፍ ጠይቀዋል፡፡
ከጥር ወር 2015 ዓ.ም. ወዲህ በክልሉ ከ1 ሺህ 3 መቶ በላይ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን፣ የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን፣ ለፌዴራልና ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ዓርብ ሐምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት አስታውቆ ነበር፡፡
በስርቆት ምክንያት የዕርዳታ ድጋፍ ካቆመ ጊዜ ወዲህ ግን ሕይወታቸው በጥር ወር አልፏል ከተባለው ቁጥር በላይ ከፍ ማለቱን፣ የክልሉ አደጋ ሥጋት ኮሚሽን ለተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ይፋ አድርጎ ነበር፡፡
ኮሚሽኑ የሟቾቹን ቁጥር ይፋ ያደረገው፣ በማዕከላዊ ዞን 22 ወረዳዎች፣ በደቡብ ትግራይ ዞን በስድስት ወረዳዎች፣ እንዲሁም በምዕራብ ትግራይ መሆኑም ተነግሯል፡

23/08/2023

በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ሰዎች መገደላቸውና፣ ከብቶች መዘረፋቸው ተሰማ

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ እሁድ እለት ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ስድስት ሰዎች እንደተገደሉ እና በንብረትም ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንዳሉት ታጣቂዎቹ በሁለት ቀበሌዎች ላይ ዘምተዉ ሰዉ ከመግደልና ንብረት ከማጥፋታቸዉ በተጨማሪ የቁም እንስሳትንም ዘርፈዋል ብለዋል፡፡
የወረዳው አስተዳደር በበኩሉ በሁለቱ ቀበሌዎች ውስጥ በደረሰው ጥቃት የሰው ህይወት ማለፉን አረጋግጧል፡ በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ የተባለ ወረዳ ውስጥ በተለያዩ ጊዜ ለሚደርሱ ጥቃቶች በፋኖ እና በሸኔ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ተጠያቂ እነደሆኑ ነዋሪው ይገልፃል።
የኪረሙ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጅረኛ ሂርጳ በወረዳው ሁለት ቀበሌ ውስጥ ሰሞኑን ከአማራ ክልል የተሻገሩ የታጠቁ ሀይሎች ጉዳት ማድረሳቸውን ስድስት ሰዎች መግደላቸውን አመልክተዋል፡፡
በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ 10 ከሚደርሱት ቀበሌዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በወረዳው 52ሺ በ8 መቶ 22 ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙም የተገለፀ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የምስራቅ ወለጋ ዞን ምንም አለማለቱን የዘገበው ዶቼቨለ ነው፡፡

21/08/2023

ኡጋንዳ ያለዓለም ባንክ ድጋፍ ለመቀጠል ማቀዷ ተገለጸ

የተመሳሳይ ጸታ ጋብቻን የሚከለክል ህግ ማጽደቋን ተከትሎ ብድር እና ሌሎች ድጋፎችን የተከለከለችው ኡጋንዳ የአለም ባንክ ድጋፍ ለመቀጠል እቅድ ማዘጋጀቷ ተሰምቷል።
የዓለም ባንክ ለኡጋንዳ አዲስ ብድር እንደማይሰጥ ማስታወቁን፤ ኡጋንዳም ያለ አለም ባንክ ድጋፍ መኖር እንደምትችል ማሳወቋ የሚታወስ ሲሆን ይህንን ተከትሎም ኡጋንዳ ያለአለም ባንክ ድጋፍ ህይወትን ለመቀጠል የሚያስችል እቅዶችን መንደፏን የኡጋንዳው ሞኒተር ጋዜጣ በድረ ገጹ አስንብቧል።
የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ የሚከለክል ህግ ማጽደቋን ተከትሎ በምዕራባዊያን ሀገራት ስትወገዝ የቆየችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ አዳዲስ የገንዘብ ምንጮችን እያፈላለገች ነው የተባለ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ እንደኛው በአፍሪካ ውስጥ ተጽእኖዋ እያደገ ከመጣው ቻይና ጋር ተቀራሮቦ መስራት ሲሆን ከህንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ማሳደግንም እንደ አማራጭ የያዘችው ኡጋንዳ፤ የዩሮ ቦንዶችን ማዘጋጀት እና ለጨረታ በማቅረብ ገንዘብ ለማግኘት መወጠኗም ተነግሯል።
ሌላኛው ኡጋንዳ እንደ አማራጭ የያዘችው መፍትሄ በሀገር ውስጥ የገንዘብ አጠቃቀም ላይ ማስተካከያዎችን መውሰድ ሲሆን፤ በዚህም ሀገሪቱ ለመንግስት ባለስልጣናት በውድ ብር ሊገዙ የነበሩ የመኪናዎችን ግዢዎችን መሰረዟን እና ከዚህ በኋላ አዳዲስ የመኪና ግዢ እንደማይኖርም የሀገሪቱ ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ምዕራባዊያን አፍሪካን ዝቅ አድርገው መመልከት እና ጫና ማሳደር ይፈልጋሉ፣ እኛ ችግራችንን እንዴት መፍታት እንዳለብን እናውቃለን፣ እነሱም የእኛ ችግሮቻችን ናቸው ሲሉ ፕሮዝዳንት ሙሴቪኒ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ኡጋንዳ ከዓለም ባንክ ጋር ያለባትን ችግር ለመፍታት የሚቻል ከሆነ ውይይት ለማድረግ ትቀጥላለች ማለታቸውም አይዘነጋም።

21/08/2023

በፀጥታ ችግር ምክንያት የአምስት መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መቆሙ ተገለጸ

የፀጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው በኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው መቆሙን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
ሚኒስቴሩ ከያዛቸው 17 የግድብ ፕሮጀክቶች መካከል ወደ አምስት የሚሆኑት ፕሮጅክቶች በፀጥታ ችግር የቆሙ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ ተጀምረው በተለያዩ የፀጥታ ችግሮች ግንባታቸው የቆሙ አሉ ያሉት አቶ ብዙነህ የላይኛው ጉደር ግድብና የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በሚሠራበት አካባቢ በሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ከቆሙት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በትግራይ ክልል የሚገኘው የካዛ ግድብና መስኖ ልማት ሎት ግንባታ በፀጥታ ችግር እንደቆመም አክለዋል፡፡
በተጨማሪ በአማራ ክልል የሚገኘው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ለ18 ዓመት መጓተቱን የገለጹት አቶ ብዙነህ፣ በባሌ በምሥራቅ ባሌ ዞን የሚገኘው ጨልጨል የመስኖ ፕሮጀክት፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው አንገር ፕሮጀክት ውል ከተገባ በኋላ በፀጥታ ችግር ማጠናቀቅ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከ85 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ፈሰስ የጠየቁ 17 የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል የተጓተቱ እንዳሉም የገለጹ ሲሆን በአጠቃላይ ሚኒስቴሩ 27 የግድብ ፕሮጀክቶች እንዳሉት፣ ከ27ቱ ፕሮጀክቶች መካከል 17 የሚሆኑት ከ85 ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ እንደተደረገባቸው፣ ከ27ቱ የአምስቱን ግድቦችን ግንባታ ለማስጀመር ገና የኮንትራክተር ሥራ ተቋራጭ ሒደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ እንዳይሳኩ የአቅም ችግር አለ ያሉት ሃላፊው ከማስፈጸም አንጻር፣ የፋይናንስ አቅም ማነስ፣ የመስኖ ፕሮጀክቶችን የሚገነቡ አማካሪ ድርጅቶችና የሥራ ተቋራጮች ግንባታ በሚያካሂዱበት ጊዜ የተለያዩ የማሽነሪ አቅም ችግር ስለሚኖር በኪራይ ስለሚሠሩ ኪራይም በሚፈለገው ልክ አቅርቦት ባለመኖሩ ፕሮጀክት ተሰጥተው በገቡት ውል መሠረት ሠርተው ማስረከብ አልቻሉም ብለዋል፡፡

21/08/2023

ኢሀፓ የሕዝብን መብት በጠመንጃ ማፈን ጥፋትን እንጂ ሰላምን አያመጣም ሲል ገለፀ

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ኢሀፓ የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ የሕዝብን መብት በጠመንጃ ማፈን ጥፋትን እንጂ ሰላምን አያመጣም ሲል ገልጿል፡፡
ለሀራምቤ ሬዲዮ በላከው መግለጫም በክልሉ ውስጥ በሚደረገው ሕዝባዊ ትግል ሕይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመግለፅ ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናቱን እንመኛለን ብሏል፡፡
ፓርቲው በብሄር ብሄረሰብ ስሪት የተገነባ አገዛዝ ለጊዜው ኢኮኖሚውን ከፍ ቢያደርግም የፀና እና የተረጋጋ ሰለም የሰፈነበት ሀገር ለመመስረት ግን አያስችልም ያለ ሲሆን፤ የአማራ ህዝብ ከአሁን ቀደም በነበረው አገዛዝ እና በአሁንም በመንግስት የጨቋኝነት ፍረጃ እየተካሄደበት እልፍ መከራዎችን እያሳለፈ ይገኛል ብሏል፡፡
ፓርቲው መንግሥት እመራበታለሁ የሚለው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 14፣ “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ፣ በሕይወት የመኖር፣ የአካልና ደኅንነት መብት አለው” የሚለውን ጥሶ የዜጎችን መብት ማፈን፤ የመከሰስ መብታቸው በሕግ የተከበረ መሆኑ እየታወቀ የፓርላማ አባላትን ከቤታቸው ወስዶ ማሠር፣ ሕገ=መንግሥታዊ ጥሰት ከመሆኑ በላይ ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ መፍትሄ አያመጣም ብሏል በመግለጫው፡፡
በመሆኑም ከችግሩ ውስብስብነት አንጻር በአግባቡ ካልተፈታ በሀገር ህልውና ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ በማገናዘብ መንግሥት የሚከተልቱን እርምጃዎች ያለመንም ቅድመ ሁኔታዎች ተግባራዊ እንዲያደርግ ሲል ፓርቲው አጥብቆ የጠየቀ ሲሆን፤ ከቅድመ ሁኔታዎች ውስጥም የመከላከያ ሠራዊትን ከአማራ ክልል በአስቸኳይ ማስወጣት እና ጊዜያዊ አዋጁን መሰረዝ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ በማንነታቸውና በፖለቲካ እምነታቸው የታሠሩ ዜጎችን በአስቸኳይ እንዲፈቱ በአማራ ሕዝብ ላይ ለዘመናት የተፈጸሙት የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የሥነልቦናዊ ጭቆናዎች በዓለምአቀፋዊና ሃገራዊ ነፃ ተቋማት ተጠንተው ተገቢው ፍትኅ አንዲሰጥ እንዲያደርጉ ሲልም አሳስቧል፡፡
የአማራ ሕዝብ ያነሳቸው የኅልውና ጥያቄዎች፣ ደህንነቱና ሙሉ መብቱ እስኪረጋገጡ ድረስ ትጥቅ የማስፈታትን ጉዳይ በይደር እንዲያዝ እና የወልቃይት፣ የጠለምት፣ የጠገዴ፣ የራያ አስተዳደሮች አሁን ባሉበት እንዲቆዩ ማድረግና ሁኔታው ሲፈቅድ በውይይት እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቋል፣
ለተፈናቀሉ ወገኖች ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ ያልተገደበ ዕርዳታ እንዲደረግ፣ የመልሶ ማቋቋም ተግባር እንዲጀመር የተገደቡ የዴሞክራሲ መብቶች ያለምነም ቅድመ ሁኔታዎች መልቀቅ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚከናወኑ እሥራት፣ አፈሳና አፈና በአስቸኳይ ማቆም ይገባል ብሏል፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረገው አፈናና በጋዜጠኞች ላይ የሚደረገው እሥራት በአስቸኳይ ማቆም እና የጎሳ ፖለቲካ በሕግ እንዲታገድ አጥብቀን እንጠይቃለን ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

21/08/2023

በአዲስ አበባ በሞተር ብስክሌት ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱ ተሰምቷል

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለምን እንደሆነ ባልታወቀ ምክንያት በሞተር ብስክሌት ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱ ተነገሯል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች በሙሉ ከዛሬ ጀምሮ ከአሽከርካሪው ውጪ ሌላ ተጨማሪ ተሳፋሪ ሳይጨምሩ የሞተር ብስክሌት ማሽከርከር እንደሚቻል የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አሳውቋል፡፡
ከተፈቀደው የሰው መጫን አቅም በላይ በሚጭኑ ማህበራትና አሽከርካሪዎች ላይ ቢሮው ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
አሽከርካሪዎችም ለትራፊክ አደጋ መንስኤ ከሆኑ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ የራስ ቆብ መከለያ (ሄልሜት) አለመጠቀም፣ ከወንጀል ድርጊት በመራቅና ወንጀል የሚፈጽሙ ሲያጋጥሙም ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ሲልም ቢሮው አሳስቧል።

21/08/2023

ለደረሰው ውድመት መልሶ ግንባታ ኢትዮጵያ የዓለማቀፍ ተቋማት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ተገለፀ

በሰሜኑ ጦርነት በአገሪቱ ላይ ለደረሰው ውድመት መልሶ ግንባታ ኢትዮጵያ የዓለማቀፍ ተቋማትን ድጋፍ በጽኑ ትፈልጋለች በማለት የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚንስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል።
አገሪቱ ለመልሶ ግንባታም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ሚንስትሩ መናገራቸው የተገለፀ ሲሆን መንግሥት ከዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር የጀመረው የብድር ድርድር ከፍተኛ ደረጃ መድረሱም ተገልጽዋል።
የፌደራሉና ክልል መንግሥታት ከበጀታቸው ከፊሉን ለመልሶ ግንባታ እንደሚመድቡ የገለፁት አሕመድ፣ ከሁሉም በላይ ግን የዓለም ባንክ ድጋፍ ያስፈልገናል ማለታቸውም ተሰምቷል።

21/08/2023

ከመጠለያ ውጪ ናቸው የተባሉ ከ60 ሺሕ በላይ የጋሞ ተፈናቃዮችን መንግሥት እንዲያቋቁም የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) ጥያቄ አቀረበ

ከሸገር ከተማና ዙሪያ ቤት የፈረሰባቸው ከ60 ሺሕ በላይ የጋሞ ዞን ማኅበረሰቦች ወደ ዞኑ ተመልሰው በዞኑ በሁሉም ከተሞች እንዲሚገኙ እና የመሬት ጥበት ስላለ እስካሁን መቋቋም እንዳልቻሉና መጠለያ እንዳላገኙ ፓርቲው አስታውቋል፡፡
የተፈናቀሉት ሰዎች አኗኗራቸው ሕገወጥ ነው ከተባለ ሕገወጥነትን ወደ ሕጋዊነት ለማዞር መንግሥት ዕርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል ነገር ግን ዜጎችን ሙሉ ለሙሉ አውጥቶ መጣል ኃላፊነት የተሞላበት የመንግሥት አሠራር አይደለም፡፡ የማቋቋም ኃላፊነቱን መንግሥት እንዲወስድ በተደጋጋሚ እየጮህን ነበር፣ አንድም ተግባራዊ የተደረገ ነገር የለም መንግሥት ቤት ፈርሶባቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን መጠለያ የማግኘት መብት በማስከበር የማቋቋም ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማለት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ዳሮት ጉምአ አሳስበዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ጋሞ ዞን ተፈናቅለው የሠፈሩት ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአጠቃላይ ብዛታቸው ከ60,000 እስከ 70,000 እንደሚሆኑና ተፈናቃዮቹ የሚገኙት በጋሞ በሁሉም ወረዳዎች እንደሆነ የፓርቲው ሊቀመንበር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአገር ውስጥ ተፈናቃይ ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ከነሐሴ 7 እስከ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. አደረኩት ባለው ውይይት፣ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደረጉ የሰብዓዊ፣ የፀጥታና የደኅንነት፣ የተሳትፎና የመንቀሳቀስ መብቶች እየተከበሩላቸው እንዳልሆነ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

21/08/2023

የሳዉዲ የጸጥታ ሃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን መግደላቸው ተሰማ

የሳውዲ የጸጥታ ሃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በየመን ድምበር ሃገሪቱን ለማቋረጥ ሲሞክሩ መግደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል፡፡
መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው ዘገባ ከምስክሮች ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ እና በፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች እና የሳተላይት ምስሎች ከ2021 ወዲህ ያለዉን ጥናት መሰረት በማድረግ ስልታዊ ነው ያለውን ግድያ ዘርዝሯል።
የሳዉዲ አረቢያ መንግስት የፖሊሲው አካል አድርጎ ስደተኞችን የመግደል ተግባር የሚፈጽም ከሆነ እነኚህ ግድያዎች በሰው ልጆች ላይ የሚደረግ ወንጀል ናቸው ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ጠቅሷል፡፡
የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎችን ምናልባትም ልዩ ክፍሎችን ጨምሮ በቅርብ ዓመታት ውስጥ "በመቶዎች ከዚህም ሲያልፍ በሺዎች የሚቆጠሩ" ኢትዮጵያውያንን ሲገድሉ በሕይወት የተረፉትን እና እስረኞችን ለእንግልት፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ተፈጽመዋል ሲል ከሷል።
የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አለመስጠቱ የተገልጸ ሲሆን ሂዩማን ራይትስ ዎች በተጨማሪም ለበርካታ የሳዑዲ ተቋማት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ መልክቱን ቢያጋራም ምንም ምላሽ አላገኝም ሲል ዋሺንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ከ750 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ሲሆን አብዛኞቹ "በመደበኛው መንገድ" ወደ ሃገሪቱ እንደደረሱ የአለም አቀፍ የስደኞች ድርጅት አስታውቋል።
በሳውዲ አረቢያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን ሰሜናዊ የሳዳ ግዛትን የሚቆጣጠረው የሳውዲ አረቢያ እና የየመን ሁቲ ንቅናቄ ስደተኞችን በጥሩ ሁኔታ ባለመያዝ ለጥቃት በማጋለጥ ተከሷል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

17/08/2023

የጋሞ ዞን በክላስተር አደረጃጀት ዉስጥ መካተቱን እንደማይቀበል ተገለጸ

የጋሞ ዞን በክላስተር የክልል አደረጃጀት ዉስጥ መካተቱን እንደማይቀበለው የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ጋዴፓ) አስተወቀ፡፡
የጋሞ ህዝብ ጥያቄ በክላስተር የመደራጀት አይደለም ያለው ፓርቲዉ፤ ህዝቡ ለረዥም ጊዜ ሲጠይቅ የቆየው ራሱን በራሱ የማስተዳደርና በክልል የመደራጀት ህገመንግስታዊ መብቱ እንዲከበርለት ነው ብሏል፡፡
አዲሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረቱት የጌዲኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ የኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጋሞ ዞን በክላስተር የክልል አደረጃጀት ውስጥ መካተቱን እንደማይቀበለው በመግለጽ የጋሞ ህዝብ ጥያቄ በክላስተር ልደራጅ የሚል አይደለም ያለው ፓርቲው፤ ህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግሥታዊ መብቱ እንዲከበርለት ነው የጠየቀው ብሏል፡፡
”የጋሞ ዞን ህዝብ ጥያቄ ከማዕከልነት ጋር የተያያዘ ወይም የከተማ አመዳደብ ኢ-ፍትሃዊነት ጉዳይ አይደለም“ ያሉት የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቡንካሾ ሀንጌ፤ የህዝቡ ጥያቄ የክልልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡
“የጋሞ ህዝብ በፊት ሐዋሳ መጥቶ ነበር አገልግሎቶችን የሚያገኘው፤ በአዲሱ አደረጃጀት ግን አገልግሎት ለማግኘት ዲላ ድረስ መምጣት አለበት፤በዚያ ላይ ከአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል“ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

17/08/2023

ምሥራቅ ጉራጌ የተባለ አዲስ ዞን እንዲቋቋም የአካባቢው ተወላጆች ጠየቁ

በጉራጌ ዞን አራት ወረዳዎችና ሦስት የከተማ አስተዳደር ነዋሪ ተወካዮች ምሥራቅ ጉራጌ ዞን “የተባለ አዲስ የዞን አስተዳደር እንዲዋቀርላቸው ሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ፊት ለፊት በመሰባሰብ ባካሄዱት ሠላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል፡፡

ሠልፈኞቹ የያዟቸው መፈክሮችም እስካሁን ባለዉ ጉራጌ ዞን ሥር ከሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች መካከል አራት የወረዳ እና ሦስት የከተማ አስተዳደሮች “ ምሥራቅ ጉራጌ ዞን “ የተባለ አዲስ የዞን አስተዳደር እንዲዋቀር የሚጠይቁ ናቸው ፡፡ “የምሥራቅ ጉራጌ ዞን “ በሚል በአዲስ ዞን እንዲዋቀሩ ሠልፈኞቹ ጥያቄ ያቀረቡባቸው የመስቃን ፣ የምሥራቅ መስቃን ፣ የሶዶ ፣ የቡኢ ወረዳዎችና እንዲሁም የቡታጅራ ፣ የሶዶ እና የኢኒሴኖ ከተማ አስተዳደሮች ናቸው ተብሏል፡፡

Address

Addis Ababa
1000

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Harambee radio 98.7 posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Harambee radio 98.7:

Share

Category