27/10/2023
ኪሪያዚስ(Kyriazis) ኬክ ቤት
በ20ዎቹ ዕድሜ እያለን ምርጥ ጎጆ ኬክና ማኪያቶ እንደነበራቸው አስታውሳለሁ። በሩ ላይ ደሞ የአመታት የጋዜጣ ደንበኛ ነበረኝ፤ ገና ስመጣ አይቶ የእለቱን የምርጫዬን ጋዜጣ ይዞ የሚጠብቀኝ።
በኛ የልጅነት ዘመን ደሞ አይስክሬም ነበራቸው፣ ብር ካምሳ። ትዝ ይለኛል አንዴ እንዳውም እኔና አብሮአደጌ ከሆያሆዬ ድርሻችን ላይ 75 75 አዋጥተን አንድ አይስክሬም ገዛን። በዛ የነሀሴ ክረምት አስባችሁታል?!
መቼም በዚያ ዘመን የአፍጣጩ፣የቀላዋጩ እና ጉልበተኛው ብዛት ለጉድ ነው። አይስክሬማችንን ገዝተን፣የሰው አይን እንዳትገባብን በኔ ጃኬት ሸፍነናት፣ያቺን የክሬም ቅልጥም ሳትሟሟብን ቶሎ ልንግጣት፣ በበረባሶ፤ በነሀሴ ጭቃ ዘጭዘጭ እያልን አራዳ ህንፃ ስር ሄድን።
ያኔ ዋናው አራዳ ህንፃ ገና እየተሠራ ሱቆቹ ግን አብዛኞቹ አልቀው ነበር። አንዱ ያላለቀው ሱቅ ስር ሆነን የደቦ አይስክሬማችንን በስማብ አልናት።
ወይኔ ቢሌ!!! ዛሬ ድረስ ሳስበው ራሱ እርር ነው ምለው፣ የማይሆን ዕድር ገብቼ። ከዚህ ጓደኛዬ ጋ የምላስ ጨዋታ በፍፁም አያዋጣም። ተረብ ብትለው ያስለቅሰሀል። አንዱን አልቃሻ ፍሬንድ 'የፋሮች አለቃ' ብሎት ወላጅ ይዞ መጣ፤ጭቃሜዳ ድረስ። አሁን ደሞ በአስክሬም መጣብኝ። ምላሱ እንደ ቀጭኔ ምላስ ረጅም ነው። በኔ ተራ ሚጢጢዬዬ ላስስ አርጌ ስሰጠው እሱ ሆዬ አንዴ ቡድስስስስ ሲያረገው ቁልል የነበረው ክሬም ኮብራ ይሰራል። በሶስት ዙር እኔ ቆንጣሪ እሱ ገማጭ ሆነን የክሪያዚሷን አይስክሬም ግብአተ-ሆድ አስፈፀምን። በኋላም የአይስክሬሟን ብስኩት እንደሸንኮራ እኩል ተካፍለን እየበላን ተቃቅፈን ወደቤት።
አይ ፒያሳ! ትዝታዎችሽ እንደኬኮችሽ እንደአይስክሬሞችሽ!?
ጣፍጭልን አቦ!