
01/05/2025
6 ዓመት ከ6ወር የሴቶች ፀጉር ቤት ገብቶ የሰረቀ.....
የንግድ ቤትን የበር ቁልፍ በመገንጠል ልዩ ልዩ ንብረቶችን የሰረቁ ሦስት ወንጀል ፈፃሚዎች እጅ ከፍንጅ ተያዙ፤ አንደኛው ወንጀል ፈፃሚ በፈጣን የፍትህ ችሎት (RTD) በ6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት መቀጣቱን የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ሚያዚያ 7 ቀን 2017 ዓ/ም የሺዋስ ሰጤ ተገኑ የተባለው ግለሰብ ፋንታሁን ገለታው እና ኪዳነማርያም ፋንታሁን ከተባሉ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አየር ጤና አካባቢ ከሚገኝ
የሴቶች ፀጉር ቤት በር ቁልፍ በመገንጠል ሁለት ካስክ፣ አንድ ስቲም፣ 21 ኢንች ቴሌቪዥን እና ሌሎች ንብረቶችን በመስረቅ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 አዲስ አበባ A 48332 በሆነ ተሽከርካሪ ጭነው ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ዘነበ ወርቅ አካባቢ የሰረቁትን ንብረት በማውረድ ላይ እንዳሉ በወንጀል መከላከል ስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ፖሊስ አስፈላጊውን ማስረጃ በማሰባሰብ የምርመራ መዝገቡን በማደራጀት በአቃቢ ህግ አማካኝነት ክስ እንዲመሰረትባቸውም አድርጓል።
ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራንዮ ምድብ 1ኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ/ም ባስቻለው ፈጣን የፍትህ ችሎት (RTD) የሺዋስ ሰጤ ተገኑ በ6 ዓመት ከ6ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ተጠርጣሪዎች ጉዳይ እየመረመረ መሆኑን ገልፆ የሺዋስ ሰጤ ተገኑ የተባለው ወንጀለኛ በተመሰሳይ ወንጀል የምርመራ መዝገብ እንደተደራጀበት የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ነዋሪው መኖሪያ አካባቢውንም ሆነ ግቢውን ለወንጀል የሚያጋልጡ ችግሮችን በመለየት እና ከፖሊስ ጋር ያለውን አጋርነት በማጠናከር ለወንጀል መከላከል ስራ ሚናውን መወጣት እንደሚጠበቅበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል።
Via AAP