25/04/2023
"የኪነ-ጥበቡን ዘርፍ መንግስት በቀጥታ መደገፍ አለበት" ስንል ምን ማለታችን ነው? የመንግስት ቀጥተኛ ድጋፍ የሚደረግላቸው ዘርፎችን በምሳሌነት እናንሳና የኪነ-ጥበብ ዘርፉ መደገፍ ስላለበት መሰረታዊ አመክንዮ በዋናነት እንዳስሳለን!
👉ጤና፦ ይሄ ዘርፍ በመንግስት አመታዊ በጀት ተመድቦለት የሚንቀሳቀስ ትልቅ ዘርፍ ነው። ይሄን ዘርፍ መንግስት በቀጥታ ባይደግፈው ሆስፒታል ፣ መድኀኒት ....... ወዘተ አይኖሩም ማለት ነው። የህብረተሰብ የጤና መድህን በቀጥታ ችግር ውስጥ ይገባል ማለት ነው!
👉ትምህርት፦ ትልቁ የትውልድ ግንባታ የሆነው ይህ ዘርፍ መንግስት በቀጥታ በጀት ይዞለት በባለሞያው ባያስመራው ትውልድ እንደ ትውልድ የመቀጠሉ ሁናቴ ከ ዜሮ በታች ስለመሆኑ ጥርጣሬ አያሻም!
👉ግብርና፦ በዚህ ዘርፍ ውስጥ በልቶ ከማደር ጀምሮ የሃገር ኢኮኖሚ መገንቢያ ትልቁ ዘርፍ ነው። ለገበሬ የግብርና ቴክኖሎጂ ከማቅረብ ጀምሮ በተቀናጀ መንገድ መሬትን አርሶ የዕለት ጉርስን ከመሸፈን በላይ ሃገር በምታመርተው የተለያዩ ምርቶች ኢኮኖሚዋን መገንባት የሚያችላት ትልቅ ዘርፍ ነው። ለዚህ ቡናን በምሳሌነት ማንሳት ከበቂ በላይ ነው።
👉ቱሪዝም፦ ከሚዳሰሱ ቅርሶች እስከማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት የሆነችው ሃገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ያላት እምቅ አቅም በተገቢው መንገድ መጠቀም ባትችልም ፣ በመንግስት ቀጥተኛ በጀት ከመመራት ጀምሮ የወደፊቱ የኢትዮጵያ ትልቁ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዘርፍ እንደሚሆን ከመሪዎች መስማት የተለመደ ነው። የመንግስት ትኩረት ካልተለየው ሃሳቡ እንደሚሳካ ጥርጣሬ አያሻም!
👉ኢንደስትሪ፦ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ ከሃገራችን ትላልቅ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዘርፎች የሚጠቀስ ዘርፍ ነው። ዘርፉ በመንግስት ከሚደረግለት ቀጥተኛ ድጋፍ የተነሳ የራሱን ፓርኮች ከመገንባት ጀምሮ ለዜጎች ዋንኛ የስራ አማራጭ እስከመሆን የደረሰ ትልቅ ዘርፍ ነው!
ከላይ የተጠቀሱት ዘርፎችን ለአብነት አነሳን እንጂ መንግስት በቀጥታ የሚደግፋቸው አብዛኛው ዘርፎች ለሃገር የኢኮኖሚ ግንባታ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ መረዳት እጅግ ቀላሉ ነገር ነው!
👉የኪነ-ጥበቡ ዘርፍ በቀጥታ (በበጀት) መንግስት ቢደግፈው ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?
የትኛውም ዘርፍ ቀጥተኛ የመንግስት የበጀት ድጋፍ እና ብቁ በሆነ በዘርፉ ሞያተኛ ከተመራ ትልቅ ውጤት የማያመጣበት አንዳች ምክንያት የለም። በሃገራችን አንዳንድ ዘርፎች የመንግስት ቀጥተኛ ድጋፍ ቢያገኙም ፣ ያን ያህል የተዋጣለት ስኬት እያገኙ አይደለም። ከዚህ አንፃር የስፖርት (ምናልባት ከአትሌቲክሱ ውጪ) ዘርፍ መጥቀስ ይቻላል። ዘርፍን በጀት በጅቶ ከመተው ባሻገር በአመራር ማብቃት የመንግስት ትልቁ ስራ ይሆናል!
በአንፃራዊነት እንብዛም ትኩረት ያልተሰጠው የኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ቀላል የማይባል ገንዘብን ከማንቀሳቀስ ጀምሮ ለዜጎች የስራ ዕድል አማራጭ መፍጠር የቻለ ዘርፍ ነው። እንደ ተሞክሮ ምዕራብ አፍሪካዊቷን የኢኮኖሚ ቁንጮ ናይጄሪያን ብናይ ፣ ኪነ-ጥበብ ለሃገሪቱ GDP ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ የቻለ ተጠቃሽ ዘርፍ ነው! በሃገሪቱ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ የሰው ሃይል (የስራ ዕድል) የተሰማራበት ዘርፍ ነው። ጥሩ የዲሞክራሲ ልምምድ እንዳላት የሚነገርላት ሃገረ ናይጄሪያ በመንግስት መለዋወጥ ውስጥ ለኪነ-ጥበብ የማይለዋወጥ ምልከታ ያላቸው መሪዎችን ማፍራት የቻለችም ሃገር ናት!
ወደ ሃገራችን ስንመጣ ፣ ደርግ በዘመኑ ኪነ-ጥበብን (በተለይ ፊልምን) ለፖለቲካ ማራመጃ (ለፕሮፖጋንዳ) መሳሪያነት መጠቀም ችሎ ነበር። የፊልም ኮርፖሬሽንን ከማቋቋም ጀምሮ በይዘት ፖለቲካዊ እሳቤዎችን ከሚያንፀባርቁ ፊልሞች ጀምሮ በጥቂቱ ሃገራዊ እና ግለሰባዊ ሃሳቦችን በፊልም መልክ ሊያስቃኘን ሞክሯል። ኮርፖሬሽኑን ሲያቋቁም ለሞያው ፍላጎት ያላቸውን ጎሮቤት ሃገር ኬንያ እና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በመላክ ጭምር ያስተማረ ሲሆን ፣ ኮርፖሬሽኑን በቁሳቁስ ረገድ የወቅቱን የሲኒማ ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅ ማድረግ የቻለ መንግስት ነበረ።
የፊልም አይነ-ጥላ የነበረበት የኢህአዴግ መንግስት ፣ ደርግ በአዋጅ ያደረጀውን ኮርፖሬሽን በአዋጅ አስነግሮ ከማፍረስ ጀምሮ ፣ የሲኒማ ቁሳቁሶቹን መርካቶ ወስዶ በኪሎ እስከመቸብቸብ የደረሰ መንግስት ነበረ!
አሁን ያለው ስርዓት የአመጣጡ ሰሞን መሪው ከስልጣናቸው በፊት ከተወሰኑ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ጋር በነበራቸው ግንኙነት እና የተወሰኑ መፅሃፍት ፅፈውም ስለነበር እንዲሁም የጫጉላቸው ሰሞን የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ሰብስበው በማናገራቸው "እንደው ለኪነ-ጥበቡ ቀና ልብ አላቸው" ብለን አስበን ነበር። ነበር ነው ደግሞ! ውሎ ሲያድር ነገሮች የታሰቡትን ያህል እንዳልሆኑ መገመት አይከብድም! ሆኖም የተሰሩ መልካም ስራዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፦ በተለይ በእድሜ ርዝማኔያቸው ያረጁ ትያትር ቤቶች (ሃገር ፍቅር ትያትር ቤትና ማዘጋጃ ቤት ትያትር አዳራሽን በምሳሌነት እናንሳና) እድሳት እንዲደረግላቸው ፣ ብሄራዊ ትያትር ቤት ደግሞ አዲስ ህንፃ እንዲሰራለት መደረጉን አለማንሳት ይከብዳል! ታድያ የታደሱ ትያትር ቤቶችን ለባለሞያው ማስረከቡ የዘገየ ይመስላል!
ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የዘርፉን ሞያተኞች በመሰብሰብ በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ተመልክተናል። ዘርፉ የሚፈልገውን አስፈላጊ ትኩረትና ሃገራዊ ፋይዳል በጥልቀት ያስረዳ ባለሞያ ባይኖርም አንዳንድ መፍትሄ የሚሹ አንገብጋቢ የዘርፉ ማነቆዎች በአንዳንድ ሞያተኞች መነሳታቸው የማይካድ ሃቅ ነው። መንግስት ሞያተኛውን ለማወያየት የሄደበት እርቀት የሚያስመሰግነው ቢሆንም ፣ ተጨባጭ ወደሆኑት ዘርፉን በቀጥታ የመደገፍ አዝማሚያዎች ግን እንብዛም አይስተዋልበትም።
ከትምህርት አንፃር በአብዛኛው ዩኒቨርስቲዎች የትያትር ጥበባት ፣ የሙዚቃ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፊልም እና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ትምህርቶች እንዲስፋፉ መደረጉ ብሎም የግል የትምህርት ተቋማት በዘርፉ ባለሞያዎችን እንዲያፈሩ መደረጉ ከኢህአዴግ መንግስት ጀምሮ አሁን ድረስ ያለ መልካም ተግባር ነው።
ስናጠቃልለው፦ ይሄ ዘርፍ ካለው የኢኮኖሚ እና የስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ብቻ መንግስት በቀጥታ ኢንዱስትሪ አቋቁሞለት ብሎም በሚኒስቴር ደረጃ ሊመራው የሚገባው ሃያል ዘርፍ ነው! ብዙ ጊዜ ይሄን ዘርፍ "መንግስት በቀጥታ ይምራው" ሲባል "የመንግስት ሃሳብ ማንፀባረቂያ መድረክ ይሆናል" ብለው የሚሰጉ አካላት ስለመኖራቸው አያጠያይቅም። መፍትሄው የይዘት ጉዳዮችን በቀጥታ በሞያተኛው ማስመራት እና መንግስት እንደ ማንኛውም ተቋም ዘርፉን የማስተዳደር ሃላፊነት ብቻ መውሰድ ይጠበቅበታል።
የዘርፉ ሞያተኞች በግል የሚደረጉ ሩጫዎች የትም እንደማያደርሳችሁ በመገንዘብ ፣ ሰብሰብ ብላችሁ ጠንካራ የሞያ ማህበራትን በማደራጀት (ያሉትን በማጠናከር) ፣ አስፈላጊውን ጫና የሚመለከተው አካል ላይ በማሳደር ሞያዊ ግዴታችሁ እንድትወጡ ይጠበቃል።
በሃገራችን በቢልዮን ገንዘቦች ፈሰስ ተደርጎላቸው እዚህ ግባ የማይባል ውጤት የሚያመጡ ዘርፎች ሞልተው ሲያበቁ ፣ ይሄን ዘርፍ ለሙከራ እንኳን መንግስት ሃላፊነት ወስዶ በሰው ሃይል ፣ በቁሳቁስ ፣ በቴክኖሎጂ እና በትምህርት ቢደግፈው ከየትኛውም ዘርፍ ያልተናነሰ በሃገር ዕድገት ላይ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት የሌሎች ሃገራትን ተሞክሮ መመልከት ብቻውን በቂ ይሆናል!
ከላይ የተጠቀሰው ሃሳብ እንዲሰምር በመንግስት ውስጥ እና በመንግስት ዙሪያ የምትገኙ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችና ወዳጆች ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል በጥልቀት ከማስረዳት ጀምሮ ፣ በዘርፉ ላይ የአዋጭነት ጥናት ሰርቶ እስከማቅረብ ድረስ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባችሁ ልናስታውሳችሁ እንፈልጋለን!
✊️
#አማኑኤል ደረጀ (የፊልም እና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ባለሞያና መምህር)