11/01/2026
የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ይፋዊ ምሥረታ በአድዋ ሙዚየም አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል!
ጥር 3 ቀን 2018 ዓ.ል
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥላ ሥር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል፣ ከምሥረታው አንሥቶ ከወጣቶች ጋር የተያያዙ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ካውንስሉ በሥሩ የሚተዳደሩ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሙስሊም ወጣቶች ካውንስሎችን የማደራጀት ሥራውን የቀጠለ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት እሁድ ጥር 3 ቀን 2018 ዓ.ል የአዲስ አበባ ከተማ የሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ይፋዊ ምሥረታ መርሐ-ግብር በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ እየተካሄደ ነው።
በዚህ የምሥረታ መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ ታላላቅ ዑለማዎች፣ ኡስታዞች፣ በርካታ ወጣቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስልን በኃላፊነት የሚመሩ አመራሮች ይሰየማሉ ተብሎ ይጠበቃል።