20/04/2026
የዋን ፕላኔት የ20 ዓመታት የብርሃን እና የፅናት ጉዞ!
በዋን ፕላኔት ሚድያ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ— ዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ስኩል እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ በአንዲት አነስተኛ ጊቢ ውስጥ በ30 ህጻናት ብቻ የጀመረው ጉዞ፣ “እያንዳንዱ ልጅ ለዓለም ብርሃን የመሆን አቅም አለው” በሚል ትልቅ ራዕይ ታጅቦ ነበር። ባለፈው አርብ ግን ይህ ህልም እውን ሆኖ በአፍሪካ ሕብረት (AU Hall) ታላቅ አዳራሽ ውስጥ የድል ዝማሬ ሆኖ ተደምጧል፡፡
የስነ-ምግባር እና የእውቀት ጥምረት
“የ20 ዓመታት የትምህርት ጉዞ በተግባር፦ ማህበረሰቡን ማገልገልና ማብቃት” በሚል መሪ ቃል የተከበረው ይህ በዓል፣ ትምህርት ቤት ከማስተማር ባለፈ ስብዕናን የመቅረጽ ተልዕኮ እንዳለው ያስመሰከረ ነበር።
በትምህርት ቤቱ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ በአቶ ዘላለም አማረ እና በባለቤታቸው ወ/ሮ ጌይል አማረ የተመሠረተው ይህ ተቋም፣ የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስትር አምባሳደር ገነት ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶች እና ታዋቂ የትምህርት ባለሙያዎች በተገኙበት ታሪኩን በደማቅ ቀለም መዝግቧል።
“ትምህርት ቤቱን ስንመሰርት ቀዳሚ ዓላማችን ከሂሳብና ከንባብ በፊት ለሥነ-ምግባር ቅድሚያ መስጠት ነበር” ሲሉ አቶ ዘላለም በንግግራቸው አስታውሰዋል። “ምክንያቱም እያንዳንዱ ልጅ በውስጡ ያለውን ብርሃን ካበራ፣ የአካዳሚክ እውቀቱ ለማህበረሰቡ የተሻለ ለውጥ ማምጫ መሣሪያ እንደሚሆን እናምናለን።”
“የዓለም ብርሃን” በታሪክ መዝገብ
በክብረ በዓሉ ላይ ሌላ ልዩ ትኩረት ስቦ የነበረው በትምህርት ቤቱ መስራች በአቶ ዘላለም አማረ የተጻፈው "The Light of the World" (የዓለም ብርሃን) የተሰኘው መጽሐፍ ምርቃት ነበር። መጽሐፉ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተፃፈ ሲሆን የጸሐፊውን የግል የሕይወት ታሪክ ጉዞ እና ትምህርት ቤቱ ያለፈባቸውን አስቸጋሪ ፈተናዎች፣ አነቃቂ ስኬቶች እና የሁለት አስርተ ዓመታት ታሪካዊ ጉዞዎችን በዝርዝር የሚያስቃኝ ሲሆን፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎችም እንደ አርአያነት ቀርቧል።
የአንድነት እና የልህቀት ውጤት
በዕለቱ በተካሄደው የፓናል ውይይት፣ የቀድሞ እና የአሁኑ ተማሪዎች እንዲሁም ወላጆች መምህራን እና የትምህርት ባለሙያ ስለ ትምህርት ቤቱ ማህበራዊ ተፅዕኖ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል እንዲሁም ለወደፊት የተቋሙ ጉዞው አመላካች ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል። ተቋሙ ለአካዳሚክ ልህቀት ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች ማሰብን ለሚያውቁ የነገ መሪዎች መፍሪያ መሆኑን አሳይቷል።
ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ሰፊ ማሻሻያ እያደረገች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ስኩል ላለፉት 20 ዓመታት ያሳየው ስኬት ለዘርፉ እንደ ተምሳሌት ተጠቅሷል። አቶ ዘላለም በቀጣዮቹ ሁለት አስርተ ዓመታት ጥራት ያለው ትምህርትን በቴክኖሎጂ በማገዝ ለኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢ ህጻናት በነፃ ተደራሽ የሚያደርግ የዲጂታል ፕላትፎርም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉና፣ የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለትምህርት እንቅፋት የማይሆንበትን አዲስ የተስፋ ምዕራፍ እንደሚከፍት ገልጸዋል።
ዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ስኩል ዛሬ ከ1,200 በላይ ተማሪዎችን የሚያስተምር እና 250 ሰራተኞችን የያዘ የትምህርት ማዕከል ለመሆን በቅቷል።
ከ20 ዓመት በፊት የበራው ያ ትንሽዬ ሻማ፣ ዛሬ የብዙዎችን መንገድ የሚያበራ ታላቅ ችቦ ሆኗል፡፡