09/04/2026
“አሰብ ወደብ ላይ የሙዚቃ ስቱዲዮ እንከፍታለን” ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ
“የብልፅግና መንግሥት [ተቃዋሚዎቹን] አያስርም”
ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደብ እንደምታገኝ ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ ተናግሯል። በግንቦት ወር በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ አዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ለመግባት የሚወዳደረው ካሙዙ “አሰብ ወደብ ላይ የሙዚቃ ስቱዲዮ እንከፍታለን፤ የሙዚቃ ክሊፕም እንሰራለን” ብሏል።
ካሙዙ ለዘንድሮ ምርጫ እጩ መሆኑ ከታወቀ በኋላ በሰጠው ኢንተርቪው መንግሥት በጦርነት እና ችግር ውስጥ ሆኖ ሀገር እየለወጠ ነው ብሏል። ይህን አለመደገፍ “የጤና ችግር ነው” ሲል ገልጾታል። አክሎም ገዢውን ብልጽግና ፓርቲ አለመደገፍ ለቁጭት ሊዳርግ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
“እኔ የማምነው አብሮ በመሥራትና ለውጥም ካለ አብሮ[ለውጥ] ማምጣት፤ እዚህ ታሪክ ላይ መሥራት። በጣም ታሪካዊ ጊዜ እየሆነ ነው ለኔ። እና እዚህ ታሪክ ላይ ወደፊት መሳተፉ የተሻለ ነው። በኋላ ስንተች ስንተች[መንግሥት] ከተቀየረ በኋላ ለይቅርታም አይመች። ተሸውጄ ነበር ለማለትም አይመችም” ብሏል።
የሙዚቃ ባለሙያው “በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ፣ በዚህ ጦርነት፣ በዚህ ችግር ውስጥ ሀገር እየተቀየረ እየተለወጠ እያየህ፤ እውነት እዚያ ላይ የሆነ ነገር ላድርግ ካላልክ የጤና ችግር ካልሆነ በስተቀር ትልቅ ዕድል ነው።” ሲል ተናግሯል።
ካሙዙ አክሎም አሁን ላይ በገዢው ፓርቲ የተሰሩ ሥራዎችን ማጣጣል አያስፈልግም ብሏል። “ጥያቄ ያለው ሰው ወደ መንግሥት ቀርቦ መጠየቅ ነው ያለበት፤አብሮ መሥራት ግዴታው ነው” ሲል ሀሳቡን አስረድቷል።
በኢትዮጵያ መንግሥትን መቃወም እና ፅንፍ መያዝ ጀግና እንደሚያስብል ገልጾ፤ ከብልፅግና አስተዳደር በፊት መንግሥትን መሳደብ ያሳሥራል አሁን ያለው መንግሥት ግን አያስርም በማለት አባል ስለ ሆነበትን ፓርቲ አብራርቷል።
“እዚህ ሀገር ስትቃወም ነው ጀግና የምትባለው ስትደግፍ ግን ሀገር ወዳድ አይደለህም። መደገፍ ግን ሀገር ወዳድነት ነው። ፅንፍ መያዝ ጀግና ያስብላል። ድሮ በነበረው አሠራር ላይ የሆነ መንግሥትን ሰድበህ መታሰር ጀግና ያስብላል። የአሁኑ መንግስት ደግሞ አያስርም” በማለት አስረድቷል።
ካሙዙ ካሳ በቃለመጠይቁ ያነሳው ሌላኛው ጉዳይ፤ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና አጀንዳ ስላደረገው የባሕር በር እና ወደብ የማልማት ጉዳይ የተመለከተው ነው። ኢትዮጵያ “በቅርቡ የአሰብን ወደብ እንደምታገኝ” ጠቁሟል። በዚህ ወደብ ላይ የሙዚቃ ስቱዲዮ እንደሚከፍትም አሳውቋል።
“ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ሀገር የምትሆንበት ዘመን እየመጣ ነው። ወደብ በቅርቡ እናገኛለን ቀይ ባሕርም። እዛ ስቱዲዮ እንከፍታለን። ክሊፕ እንሰራለን። እዚህ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይመለከተዋል። ሁሉም ሰው ቀለል አድርጎ ማየት የለበትም ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ በጣም ተራ ነገር አይደለም” ማለቱን ኢትዮ ቲዩብ ሰምቷል።