19/06/2025
ከዓመታት በፊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ አሁን ርዕሱንና ጸሐፊውን የማላስታውሰውን የታሪክ መጽሐፍ አንብቤ ነበር። (አንብቦ ለመጨረስ የማይመች ግዙፍ መጽሐፍ ስለ ነበር ገጾቹን አገላብጬ ነበር ማለት ይቀላል)። ይህ መጽሐፍ የሀገራትንና ሕዝቦችን ከታሪክ ህልውና የመክሰም ትወራዎችን በሚዘረዝርበት ርዕስ ስር - በትክክል ካስታወስኩ - ወደ ሰባት የሚሆኑ መላ ምቶችን ያስቀምጣል። እነዚህን መላ ምቶች ከዘረዘረ በኋላ የአይሁድ ሕዝብ ከእነዚህ መላ ምቶች በአንዱም ሊገለጽ እንደማይችል ያሳስባል። መላ ምቶቹ ትክክል ከሆኑ የአይሁድ ሕዝብ እንደ ማንኛውም ህልውናው እንደ ከሰመ ሕዝብ መጥፋት የነበረበት ቢሆንም በልዩ ሁኔታ ተጠብቆ እስከ ዛሬ ድረስ አለ። በታሪክ ሁሉ በአይሁድ ሕዝብ ላይ የደረሰውን መከራና እንግልት ስንመለከት ህልውናው ተጠብቆ መኖሩ ተዓምር የሚያሰኝ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን ስንመለከት የአይሁድ ሕዝብ እንዲጠፋ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ሐማ ስለ ተባለ ፋርሳዊ (ኢራናዊ) ታሪክ እናነባለን። በመጽሐፈ አስቴር መሠረት ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ክፉኛ የሚጠላ ሰው የነበረ ሲሆን የአይሁድ ሕዝብ እንዲጠፋ ለማድረግ ከፍተኛ የጥፋት ድግስ አዘጋጅቶ ነበር። ነገር ግን ሐሳቡ ከሽፎ ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው መስቀያ ላይ እርሱ ራሱ ተሰቅሏል (አስቴር 7፡10)። በሌላ ወገን ደግሞ የአይሁድ ሕዝብ በምርኮ ሲሠቃይ ከነበረበት የግፍ አገዛዝ ነጻ ወጥቶ ወደ ሀገሩ እንዲመለስና እንደ ሕዝብ ህልውናው እንዲቀጥል ስላደረገ ሌላ ኢራናዊ ንጉሥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናነባለን። የንጉሡ ስም ቂሮስ ሲሆን የአይሁድ ሕዝብ ህልውና እንዲቀጥል ሰበብ ከሆኑት ሰዎች መካከል ዋነኛው ነው (ዕዝራ 1፡2)።
ፖለቲከኞች እንደሚሉት በፖለቲካው ዓለም ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅም ሆነ ጠላት የለም። ዛሬ እርስ በርስ ለመጠፋፋት የሚቀጣቀጡት እስራኤልና ኢራን ከሃምሳ ዓመታት በፊት በፓህላቪ ዘመን ወዳጆች ነበሩ። በአያቶላዎች ዘመን ደግሞ ጠላቶች ሆነዋል። ነገ ደግሞ ተመልሰው ወዳጅ ሊሆኑ ይችላሉ።
እግዚአብሔር አምላክ ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ያለውን ጉዳይ ገና እንዳልጨረሰ መጽሐፍ ቅዱስን ካነበበ ሰው የተሰወረ አይደለም። ብሔራዊ ንስሐ አድርገው ወደ መሲሁ የሚመለሱበት ዘመን ይመጣል (ዘካርያስ 12፡10፣ ሮሜ 11:25–26 ፣ ሆሴዕ 3:4–5)። ሰይጣን ይህንን ሕዝብ ማጥፋት ይፈልግ የነበረው ለመሲሁ መንገድ በመሆን የአብርሃም በረከት ተፈጻሚ እንዳይሆን ነበር። የመሲሁ በረከት በዚህ ሕዝብ አማካይነት ስለ ተፈጸመ አሁን ደግሞ በበቀል ይህንን ሕዝብ ይፈልገዋል። በነገረ ፍጻሜ ውስጥ ካለው ሚና አንጻርም ይህ ሕዝብ እንዲጠፋ የሰይጣን ምኞት ነው።
በመጨረሻው ዘመን ከሚከሰቱት አስጨናቂ ክስተቶች መካከል አንዱ የጎግ ማጎግ እስራኤልን ለማጥፋት መሰብሰብ ነው (ሕዝቅኤል 38፡8)። በእስልምና የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ መሠረት መጨረሻ ከመሆኑ በፊት ሙስሊሞች የአይሁድ ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ እንደሚፈጽሙ ይታመናል (Sahih Muslim Book 54, Hadith 105)። በተለይም ደግሞ የሺአ ሙስሊሞች ማሕዲ ብለው የሚጠሩት ሐሰተኛ ክርስቶስ ሲገለጥ የአይሁድን ሕዝብ እንደሚጨፈጭፍ ተስፋ ያደርጋሉ። ለዚህ ነው እስራኤልን እንደ ሀገር፣ አይሁድንም እንደ ሕዝብ የሚጠሉት። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ደግሞ ጌታ እስራኤልን ይታደጋታል (ራዕይ 20፡7–9)። የሚገርመው ነገር በመጨረሻው ዘመን እስራኤልን ለማጥፋት ከሚሰበሰቡት ሀገራት መካከል ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ አሁን የሙስሊም ሀገራት ናቸው። (በዚህ ውስጥ ግን ሳኡዲ አረብያ አልተካተተችም። ምናልባት ሁኔታዎች ተለዋውጠው ሳኡዲ የክርስቲያን ሀገር ወደ መሆኑ ትለወጥ ይሆን? አናውቅም።) At this point, I might sound like an apocalyptic preacher but all of this is right there in the Bible.
ሐሳቤን ሳጠቃልል፦ ለኢየሩሳሌም ሰላም እንጸልይ (መዝሙር 122፡6)። እግዚአብሔር ሕዝበ እስራኤልን እንዲታደግ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ መሲሁን ወደ ማወቅ እንዲመጡ እንዲረዳቸው እንጸልይ። ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የዓለም ሕዝቦች ሰላም እንጸልይ። ክስተቶችን ደግሞ በቃሉ ውስጥ በተጻፈው መሠረት እንመዝን። ሰላም ለእስራኤል! ሰላም ለኢራን!
©Daniel
ለተጨማሪ መረጃ የፌስቡክ ገፃችንን ይከታተሉ
https://www.facebook.com/CInewsethiopia