
19/08/2025
ስታርታፖ ኮሙኒቲ በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ በማተኮር ለነገው ትውልድ መሰረት መጣል እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ባይሳ በዳዳ ገለፁ።
========================
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በኮሪያ አለም ዓቀፍ ተራህዶ ድርጅት ሲደገፉ የነበሩ ሰርታርታፖች ዓመታዊ የጋራ መድረካቸውን በኢኖቢዝኬ የኢንኩቤሽን ማዕከል አካሄዱ።
መድረኩ ስታርታፖቹ ያላቸውን ልምድ ለማጋራት፣ የስራ ትብብርና ትስስርን ለመፍጠርና የጋራ የሆነ ህብረት ለመመስረት ያለመ ነው።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ባይሳ በዳዳ ከሀገራዊ ስታርታፖች ትብብርና ትስስር የሚገኙ አቅሞችን ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ልማት ግቦች ስኬት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ስታርታፖች በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እያገኙ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ላይ ለመድረስ ፈጠራ በሀገራችን ባህል ሆኖ በማህበረሰብ ውስጥ ሊጎለብት ይገባል ብለዋል።
ሀገራዊ የስታርታፕ አዋጅ መፅደቅ የፈጠራ እድገትን እጅግ እንዲፋጠን ያደርገዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዘርፉ ህጋዊ እውቅና፣ ግልፅ ምዝገባ፣ የተሻሻለ የገንዘብ አቅርቦት፣ የታክስ ማበረታቻዎች እና ጠንካራ የአቅም ግንባታ እርምጃዎችን፣ ለሥነ-ምህዳር ገንቢዎች ጠንካራ ድጋፍና ሌሎች እገዛዎችን እንደሚሰጥም አስገንዝበዋል።
የኮሪያ አለም ዓቀፍ ተራህዶ ድርጅት prof. kwak jaesung (project manager kyunghee university ) በኢትዮጵያ የስታርታፕ ዘርፉን ለማጎልበት በትብብር ላይ ተመስርተው ሰፋፊ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሆኑ ገልፀው በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
በመድረኩ ከኮሪያ በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና የመስጠት፣ የፓናል ውይይት፣ የተመረጡ ስታርታፖች ልምድ የማጋራትና በጋራ ለመስራት የሚያስችል ምክክሮች ተደርገዋል።
Ministry of Innovation and Technology - Ethiopia