
26/07/2025
በኦሮሚያ ክልል በሸገር ሲቲ ከተማ የሚገኘዉ አቡ ዘር መስጂድና መድረሳ መፍረሱ ታወቀ።
♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️ ♦️
በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ መልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ በመልካ ገፈርሳ ወረዳ ወረዳ የሚገኘዉ አቡዘር መስጂድና መድረሳ በዛሬው እለት ከፈጅር ሶላት ቡኅላ መፍረሱ ታወቀ።
የአቡዘር መስጂድና መድረሳ በኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የእዉቅና ሰርተፍኬት የተሰጠዉ፣ በወቅፍ አማካኝነት ተበርክቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነበር።
የአቡዘር መስጂድ ከዚህ ቡኅላ እንደማይፈርስ ከከተማው ከንቲባ ከዶር ተሾመ ጋር መነጋገሩና ከታች ባያያዝነዉ በሰርተፍኬትነት በማረጋገጥ የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በሆኑት ሸይኽ ጋሊ ሙክታርና በዶር ሙሀመድ ሷልህ አማካኝነት ማረጋገጫ ተሰጥቶት እንደነበር ያሳያል።
በዛሬው እለት የፈጅር ሶላት እንደተጠናቀቀ የአፍራሽ ግብረ ኀይል በመምጣት የአቡዘር መስጂድና መድረሳን ማፍረሱና ማቴሬያሎችን ጭምር መዉስዳቸዉ ተረጋግጧል።
የአቡዘር መስጂድና መድረሳ ምርጫ ከሚካሄድባቸዉ መስጂዶችና የአከባቢዉ ሙስሊም የምርጫ ካርድ የወሰደበት ሲሆን ይህም ከምርጫ አካሄድ አንጻር እንቅፋት መሆኑ እሙን ነዉ።
በአቡዘር መስጂድና መድረሳ ከምዕመናኑ ሰጋጅ ውጪ 260 የመድረሳ ተማሪዎችን በቋሚነት ያስተናግድ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል የሸገር ሲቲ መጅሊስ ፕሬዝደንት ዶር ሙሀመድ ሷልህ ከሸገር ሲቲ ከንቲባ ዶር ተሾመ ጋር በመደዋወል እንደተነጋግሩና መስጂዱ እንደማይፈርስ እንደተነገራቸዉ ለመስጂዱ ኮሚቴዎች በቃል ቢናገሩም በዛሬዉ እለት በተግባር መስጂዱ ፈርሷል።
በሸገር ሲቲ ከተማ ከዚህ ቀደም በርካታ መስጂዶች በህገ ወጥ ሽፋን በማፍረስ መሪውን(አስተዳዳሪዉን) የኀይማኖት ተቋም በመናቅና ክብር በመንፈግ እኩይ ተግባር መፈጸሙ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው እለትም በተመሳሳይ መልኩ እንዲፍርስ ተደርጓል።
የሸገር ሲቲ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤ ፕሬዝደንት ዶር ሙሀመድ ሷልህ መስጂዱ ከሰዓት ቡኅላ መፍረሱን እንደሰሙ የገለጹልን ሲሆን የሸገር ሲቲ ከንቲባ ዶር ተሾመ መስጂዶች ከዚህ ቡኅላ አናፈርስም በማለት እንደተናገሩና ከዚህ ቀደም በፈረሱ መስጂዶች ምትክ ለመስጠት ቃል የገባነውን እየሰሩ እንደሚገኙ እንደነገሯቸዉ ገልጸዉልናል።
ከክልሉ የመንግስት የስራ ኅላፊዎች እንዳገኘነዉ መረጃ ከሆነ በወቅፍ የተሰጡ በርካታ መስጂዶችን ለማፍረስ እቅድ እንዳለ ተሰምቷል።
የሚመለከታችሁ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኅላፊዎች፣ የፀጥታና የፍትሕ አካላት በተደጋጋሚ ጊዜ በሸገር ሲቲ ሙስሊሞች ላይ ኀይማኖታዊ ተቋማቶቻቸዉና መድረሳዎቻቸዉ በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ እየፈረሱ፤ መብቶቻቸዉ እየተጣሱ እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን ይህ አካሄድ ወዳልተፈለገ ግጭት የሚያመራ በመሆኑ የእኩይ ድርጊቱ ፈፃሚዎችን ለሕግ እንድታቀርቡና መሳጂዶችን በመገንባት ኅላፊነታችሁን እንድትወጡ እናሳዉቃለን።