13/12/2025
በንጉሥ ነጃሺ ዙርያ የተሠራ "አርዱ ሲድቅ" ዘጋቢ ፊልም ምርቃትና ሲምፖዚየም መካሄዱ ተገለፀ!
- ሀሩን ሚዲያ፥ ታህሳስ 4/2018
ትካል ረድኤት ቢላል (ቢላል ኤይድ) የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም መድረክ ላይ በበጎ ለማስተዋወቅ በንጉሥ ነጃሺና በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች ዙርያ ያዘጋጀውን ዘጋቢ ፊልም ዛሬ በአዲስ አበባ አድዋ ሙዚየም ማስመረቁ ተገልጿል።
የሲምፖዚየሙ ዋና ዓላማ በትግራይ ክልል በሚገኘው በንጉሥ ነጃሺ መስጅድ የሚገኙ ቅርሶችን ሙስሊሙ ማኅበረሰብ እንዲያውቅ ከማድረግ ባሻገር እንዲጠቀምበት መሆኑን የፕሮግራሙ አዘጋጅ አሚር ሳሊህ መናገራቸውን ሚንበር ቲቪ ዘግቧል።
የነጃሺ ታሪክ በዓለም ትልቅ ቅርስ ሆኖ እያለ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አለመመዝገቡን የገለጹት አሚር፤ ለማስመዝገብ ነጃሺ ዜሮ ዜሮ መንደር በሚል ኢኒሼቲቭ ተጀምሮ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
‘አርዱ ሲድቅ’ ወይም የእውነት ምድር በሚል ዘጋቢ ፊልም መዘጋጀቱን የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።
ዘጋቢ ፊልሙ ከኢትዮጵያ ባለፈ በውጪ ሀገሮች ለማሳየትም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሲምፖዝየሙ አዘጋጅ ለሚንበር ቲቪ ተናግረዋል። በቀጣይ በሳዑዲ ጂዳ ከተማ ለማቅረብ የተዘጋጁ ሲሆን በአምስት ቋንቋዎች መተርጎሙን ገልጸዋል።
የፕሮግራሙ የክብር እንግዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የነጃሺ ታሪክ “ለእስልምና መስፋፋት ያለውን ትልቅ ትርጉም የሚገልጽ ነው” ያሉ ሲሆን ታሪኩንም የሁላችንም ታሪክ ነው ብለዋል።
በዝግጅቱ ከአቶ ጌታቸው ረዳ በተጨማሪ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለ ሃይማኖትን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸው ተመላክቷል።
© ሀሩን ሚዲያ