
15/07/2025
እሷ የ24 ዓመት ወጣት ነበረች። ከኮሌጅ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ነበር።
እሱ የ3 ወር ህፃን ነበር። ከአንድ ሆስፒታል ውጪ በካርቶን ሳጥን ውስጥ ተጥሎ የተገኘው እንዲህ ከሚል ማስታወሻ ጋር ነበር፦
"ይቅርታ አድርጉልኝ። እባካችሁ ውደዱት።"
ማንም ሊወስደው አልመጣም።
ቤተሰብም ሆነ ወገን አልጠየቀውም። ምንም የስልክ ጥሪ አልነበረም... ዝምታ ብቻ።
በዜና ላይ "ህፃኑ ኤልያስ" ብለው ሰየሙት። ነገር ግን ሁሉም ሰው መጨረሻው የመንግስት የህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ እንደሚሆን ገምቶ ነበር።
ከእሷ በቀር።
ራሄል እናት የመሆን ምንም እቅድ አልነበራትም። እሷ በሆስፒታሉ የህፃናት ማቆያ ክፍል በበጎ ፈቃደኝነት ታገለግል ነበር።
ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ እቅፍ ስታደርገው፣ ጥቃቅን እጆቹ ጣቷን አጥብቀው ያዙና ሊለቋት አልቻሉም።
ልቧም አልለቀቀውም።
የጉዲፈቻ ተቋሙ "ገና ወጣት ነሽ፣ ብቻሽን ነሽ፣ ልምድም የለሽም" አሏት።
እሷም እንዲህ አለቻቸው፦
"ባል ላይኖረኝ ይችላል። ገንዘብም ላይኖረኝ ይችላል። ነገር ግን ፍቅር አለኝ። እሱ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልገው ይሄንን ነው።"
ኤልያስን በጉዲፈቻ ወሰደችው።
የእሷ ነጭ ቆዳና የእሱ ጠይም ሉጫ ፀጉር የብዙዎችን አይን ይስብ ነበር።
የሰዎችን ሹክሹክታ ትሰማ ነበር፦
"በፍፁም ልጇ አይመስልም!"
"አመት እንኳን አትቆይም።"
"ሲያድግ ይጠላታል።"
ነገር ግን ነፋስና ዝናብ ሲበረታ እንዴት ተጠግቷት ከእቅፏ እንደማይወጣ አላዩም።
ወይም ደግሞ የፒያኖ ትምህርቱን ክፍያ ለመሸፈን ብቻ ሶስት ስራዎችን እንደምትሰራ አላወቁም።
ወይም ለመጀመሪያ ጊዜ "እማዬ" ብሎ ሲጠራት እንዴት በእንባ እንደታጠበችም አላዩም።
ጀግንነትን፣ የመኝታ ሰዓት ታሪኮችን እና ወሰን የሌለውን ፍቅር እየመገበች አሳደገችው።
ዓመታት ነጎዱ።
ኤልያስም ቁመናው ገዝፎ፣ ደግና ብሩህ አዕምሮ ያለው ወጣት ሆነ።
18 ዓመት ሲሞላውም በነፃ የትምህርት ዕድል የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ገባ።
በምረቃው የእራት ግብዣ ላይ መድረክ ላይ ወጥቶ እንዲህ አለ፦
"ሰዎች ሁልጊዜ 'እውነተኛ እናትህ ወዴት ናት?' እያሉ ይጠይቁኝ ነበር።
መልሱ ይኸውላችሁ፤ እሷ እዚች ጋር ናት።
ማንም ያልፈለገኝን እኔን የመረጠችኝ ሴት።
ስም፣ ቤትና የወደፊት ተስፋ የሰጠችኝ።
እሷ ምናልባት አልወለደችኝም ይሆናል...
ነገር ግን ህይወቴን አትርፋለች።"
በክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሁሉ አለቀሱ።
ራሄልም እንባዋን መቆጣጠር አቃታት።
ኤልያስ ግን ፈገግ ብሎ በጆሮዋ እንዲህ ሲል ሹክ አላት፦
"እማዬ፣ አሁንም እጄን እንደያዝሽልኝ ነው። እኔም በፍፁም አልለቅሽም።"