 
                                                                                                    07/08/2025
                                            መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ የተረጎመችዉ አስቴር ጋኖ ‼️
መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ በመተርጎም ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዎ ያደረገች፤ የኦሮምኛ ስነ ጽሑፍና ስነ ቃል ላይ አሻራዋን ጥላ ያለፈችዉ ኢትዮጵያዊ አስቴር ጋኖ በ1872 በኢሉባቦር ግዛት ተወልዳ በ1962 ዓ.ም ነቀምቴ ውስጥ ከዚህ አለም በሞት የተለየች ኢትዮጵያዊት ስትሆን ስሟ ከሚጠራበት ስራዎች መካከል የሚጠቀሰው ከአነሲሞስ ነሲብ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ወደኦሮምኛ መተርጎሟ ነው።
ገና በለጋ እድሜዋ በሊሙ ኢናሪያ ባሪያ ፈንጋዮች ተይዛ በሽያጭ ለባርነት ወደ አረብ ሀገር በመወሰድ ላይ እያለች ይዟት ይነጉድ የነበረው ጀልባ በጣልያን መርከበኞች በቁጥጥር ስር በመዋሉ ከባርነት ተርፋ እምኩሉ (ኤርትራ ውስጥ) የስዊድን ሚሲዮን የሴቶች ት/ቤት በመግባት ትምህርቷን ጨርሳለች።
እንደተመረቀችም የመጀመሪያ ስራዋ የኦሮመኛ መዝገበ ቃላትን ማጠናቀር ነበር። ይህም መዝገበ ቃላት አነሲሞስ ነሲብ በ1893 አዲስ ኪዳንን በ1899 ደሞ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ እንዲተረጉም ረድቶታል።
በ1894 ከአነሲሞስ ጋር በመሆን ‘የኦሮሞ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ቃሉ ተቀይሯል) ፊደል መጽሐፍ’ የሚል መጽሐፍ አሳትማለች።
የመጽሐፉ ይዘትም፦ የእረኛ ዘፈኖች፤ የሕፃናት ዘፈኖች፤ የፍቅር ዘፈኖች፤ ምሳሌዎች፤ ተረት ተረቶች፤ እንቆቅልሾች፤ የሕፃናት ጨዋታዎች፤ የአቴቴ ዘፈኖች፤ የኦሮሞ ፀሎቶች፤ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።
በ1904 ከአነሲሞስ ጋር በመሆን ከእምኩሉ ወደ ወለጋ ተመለሰች። እስከ አለተ ዕረፍቷ ድረስ በነቀምቴ ከተማ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በማገልገልና ለአካባቢዉ ነዋሪዎችም መሰረታዊ ትምህርት በመስጠት አሳልፋለች። ዘመኗን ህይወቷን ለእግዚአብሔር ስራ ሰጥታ ያገለገለችዉ አስቴር ጋኖ በ1962 ዓ.ም በነቀምቴ ከዚህ ዓለም ድካም አርፋለች።
Bible Association                                        
 
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                         
   
   
   
   
     
   
   
  