![ቅዱስ ሲኖዶስ በሦስተኛው ቀን ውሎው "ገድለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ" በሚል እየተሠራጨ ያለውን መጽሐፍ አወገዘ፡፡ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም [ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ]የቅዱስ ሲኖዶስ ም...](https://img5.medioq.com/958/516/1259102039585165.jpg) 
                                                                                                    24/10/2025
                                            ቅዱስ ሲኖዶስ በሦስተኛው ቀን ውሎው "ገድለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ" በሚል እየተሠራጨ ያለውን መጽሐፍ አወገዘ፡፡ 
ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም [ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ]
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በሦስተኛ ቀን ውሎው ከአጀንዳ 7-13 ባሉት ላይ ውይይት ማድረጉና ውሳኔ ሰጥቷል።
ረዳት ፕሮፌሰር መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል የጥናትና ምርምር መምሪያ እና የቅዱስ ሲኖዶስ የኮሚዩኒኬሽን ሓላፊ ዛሬም ማብራሪያውን የሰጡ ሲሆን።
በአጀንዳ ቁጥር 7 ከአርሲ ሀገረ ሰብከት ካህናትና ምእመናን የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የአርሲ ሀገረ ስብከት ካህናት እና ምእመናን ያቀረቡትን አቤቱታ በንባብ በማድመጥ ጉባኤው የቀረበውን አቤቱታ አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን የሒሳብ ጉዳዮችም ያሉበት በመሆኑ ዝርዝር ማጣራት ስለሚያስፈልገው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በኩል አጣሪ ተመድቦ በሚቀርበው ሪፖርት ጉዳዩ በቋሚ ሲኖዶስ እንዲታይ እና ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉባኤው መወሰኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በአጀንዳ ቁጥር 8 የተወያየውና ውሳኔ ያሳለፈው የሸካ ዞን ራሱን ችሎ ሀገረ ስብከት እንዲሆን የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ መሆኑን ነው ሓላፊው የገለጹት፡፡ 
በዚህም የሸካ ዞን ራሱን ችሎ በሀገረ ስብከት ደረጃ እንዲቋቋም በቀረበው ጥያቄ መነሻነት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በግንቦቱ ርክበ ካህናት በሰጠው ውሳኔ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል ተጠንቶ እንዲቀርብ መደረጉን ጉባኤው አስታውሷል፡፡
በተስጠው ውሳኔ መሠረት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተላኩት ልዑካን ያቀረቡት ጥናት ተቀባይነት ያገኘ በመሆኑ፤ የሸካ ዞን ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ተብሎ ራሱን ችሎ በሀገረ ስብከት ደረጃ እንዲቋቋም እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሊቀጳጳስ ሀገረ ስብከቱ እንዲያደራጁና እንዲመሩ ይደረግ በማለት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ ማሳለፉን በዕለታዊ ማብራሪያቸው ገልጸዋል፡፡
በአጀንዳ ቁጥር 9 በአንድ ግለሰብ ተዘጋጅቶ "ገድለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ" በሚል እየተሠራጨ ያለውን መጽሐፍ አስመልክቶ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል፡፡
ይኸውም በአንድ ግለሰብ ተዘጋጅቶ "ገድለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ" በሚል እየተሠራጨ ያለውን መጽሐፍ የተመለከቱ የታላቁ ደብረ ሊባኖስ አንድነት ገዳም መምህር የሆኑት መጋቤ ምሥጢር አባ ክንፈሚካኤል ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት መጽሐፉ እንዲመረመር ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት መጽሐፉ እንዲመረመር እና ያለበት ግድፈትና የስሕተት ትምህርት ተለይቶ እንዲቀርብ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ የመራው ሲሆን፤ የሊቃውንት ጉባኤውም መጽሐፉን በሚገባ በመመርመር መጽሐፉ ያለበትን ግድፈትና የስሕተት ትምህርት ነቅሶ በማውጣት ከውሳኔ ሐሳብ ጋር አቅርቧል።
ቅዱስ ሲኖዶስም ቀደም ሲል በሊቃውንት ጉባዔ ተመርምሮ ያለበት ግድፈትና የስሕተት ትምህርት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስያንን የማይወክል በመሆኑ "ገድለ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት" በማለት ተጽፎ የቀረበው መጽሐፍ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ የሚያዛባ ሆኖ ስለተገኘ በቅዱስ ሲኖዶስ መወገዙ ተገልጿል፡፡
መጽሐፉ  በውስጥ የየያዛቸው የተሳሳቱ ትምህርቶች በሙሉ ተቀባይነት የሌላቸው ሲሆን  ቅዱስ ሲኖዶስ ታትሞ ሥርጭት ላይ የዋለው መጽሐፍ ሥርጭቱ እንዲታገድ፣ በድጋሚም እንዳይታተም፣ በማናቸውም ሁኔታ መጽሐፉ ለማጣቀሻም ሆነ ለምርምር እንዳይውል በመወሰን ይህም ውሳኔ ለየአህጉረ ሰብከቱ በሰርኩላር ደብዳቤ እንዲላክ በማለት መወሰኑ ተገልጿል።
ቅዱስ ሲኖዶስ የሊቃውንት ጉባኤ የጀመረውን የማጣራት ሥራ በሌሎችም መጻሕፍት እንዲቀጥል እና ከምስጋና ጋር መመሪያው እንዲደርሰው፤ መጽሐፉን አሳትመው ያሰራጩት ግለሰብ በቋሚ ሲኖዶስ ተጠርተው እንዲጠየቁና የፈጸሙት ስሕተት በተመሳሳይ እንዳይደግሙ ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጣቸው መወሰኑ ተገልጿል። 
መጽሐፉ እንዲመረመር ያደረጉት የታላቁ ደብረ ሊባኖስ አንድነት ገዳም መምህር መጋቤ ምሥጢር አባ ክንፈሚካኤልን ቅዱስ ሲኖዶስ ማመስገኑን ሓላፊው ገልጸዋል::
በአጀንዳ ቁጥር 10 በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ 18 አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ተወካዮች ነን የሚሉ ወገኖች ባቀረቡት ማመልከቻ መነሻነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ጉዳይ መምሪያ ጉዳዩን በመመልከት በሰጠው መግለጫ ላይ ተወያይቷል፡፡  
በዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ የክፍሉ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የሀገረ ስብከቱን መዋቅር በማጠናከር በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጣቸውን ሓላፊነት በመወጣት፤ በአካል በሀገረ ስብከታቸው በመገኘት አሉ የተባሉ ችግሮችን በመፍታት በግንቦቱ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያቀርቡ ውሳኔ ማስተላለፉን በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡
በአጀንዳ ቁጥር 11 በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ካልፎርኒያ ኔቫዳና ኦሪዞና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ሥር መንፈሳዊ ኮሌጅ ለመክፈትና የአብነት ትምህርት ማስመስከሪያ ት/ቤት ለማቋቋም ዕርዳታና እውቅና እንዲሰጠው ባቀረበው የዕውቅና ጥያቄ ላይ በመወያየት መንፈሳዊ ኮሌጁና የአብነት ትምህርት ማስመስከሪያ ት/ቤቱ እንዲከፈት የተፈቀደ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ የትምህርት አሰጣጥ፣ ፖሊሲውንና ሥርዓተ ትምህርቱን፣ የሰው ኃይል ትመናውንና መዋቅራዊ ተጠሪነቱን በተመለከተ  ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ቀርቦ እንዲመረመርና የመጨረሻ ጥናቱ ለግንቦት 2018 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ሲል ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል::
በአጀንዳ ቁጥር 12 እና 13 በካናዳ በሚገኙ አህጉረ ስብከቶች ዙርያ ውሳኔ ማሳለፉን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም ውሳኔ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ያቀረቡት ጥያቄ በተመለከተ የኹለቱ አህጉረ ስብከት አስተዳደር ከዚህ ቀደም በግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም በተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት እንዲፈጸም ሆኖ አንዱ በአንዱ ጣልቃ ባለመግባት በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ አርባ ንዑስ ቁጥር 3 የተመለከተው ድንጋጌ ተጠብቆ እንዲሠራበት በማለት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከለኛው ካናዳ ኤድመንተን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሀገረ ስብከቱ ስያሜ እንዲስተካከል  በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሎ የሀገረ ስብከቱ ስያሜ የመካከለኛው ካናዳ ኤድመንተንና አካባቢው በሚለው እንዲስተካከል በማለት ምልዓተ ጉባኤው በመወሰን የዕለቱን ስብሰባ ማጠናቀቁን ረዳት ፕሮፌሰር መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ገልጸዋል፡፡
©EOTCTV                                        
 
                                                                                                     
                                                                                                    ![ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክብረ በዓላትን በተመለከተ ምክክር መደረጉ ተገለጸ!!ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም [ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ]በኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በሀገራችን የሚገኙ ባህላዊና ሃ...](https://img3.medioq.com/636/341/1257986226363413.jpg) 
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                    ![የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የመጀመሪያ ቀን ውሎው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ ሰጠ።ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም [ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ]የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በሰጠው ዕለታዊ መግለጫ በ...](https://img4.medioq.com/643/375/1257282816433754.jpg) 
                                                                                                     
                                                                                                    ![የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለመምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ያዘጋጀው  የአቅም ግንባታ ሥልጠና  ተጠናቀቀ።ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ.ም [ተሚማ/ አዲስ አበባ]በኢት...](https://img3.medioq.com/312/514/1257035543125148.jpg) 
                                                                                                     
                                                                                                     
                                                                                                     
                                         
   
   
   
   
     
   
   
  