15/10/2025
#የሸገር ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ እየፈፀመ ያለውን ሙስሊሙን መስጂድ አልባ የmaድረግ ተግባር እንዲያቆም ተጠየቀ!
በሸገር ከተማ አስተዳደር በኮዬ ፈጬ ክፍለከተማ በቱሉ ዲምቱ የሚገኘው ሰላም መስጂድ በ3 ቀናት ውስጥ ይፍረስ መባሉን ተከትሎ የሸገር ከተማ መጅሊስ አመራሮች በቦታው በመገኘት ምልከታ አድርገዋል፡፡
የሸገር ከተማ መጅሊስ አመራሮች በምላሻቸው የሸገር ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ ጊዜ ካለምንም ውይይት መስጂዶችን ማፍረሱን አስታውሰው አሁንም በቱሉዲምቱ የሚገኘውን ሰላም መስጅድን ለማፍረስ መሞከር ሙስሊሙን ያስቆጣ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አክለውም እንደ ሸገር መጅሊስ የሰላም መስጂድ ይፈርሳል መባልን ተከትሎ በአካል የሸገር ከተማ ከንቲባን ለማነጋገር ብንሄድም ልናገኘው አልቻልንም ብለዋል፡፡
በሸገር ከተማ የሚገኘው የኮዬ ፈጬ ክፍለከተማ አስተዳደር ያለምንም የፅሁፍ ደብዳቤ የመስጅዱ ቦታ ለልማት ይፈለጋል በሚል ይፈርሳል ማለቱን አንቀበለውም ሲሉ የሸገር ከተማና የኮዬ ፈጬ ክፍለከተማ መጅሊስ አመራሮች ገልፀዋል፡፡
የቱሉ ዲምቱ ሰላም መስጅድ ኮሚቴዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው በዛሬው ዕለት የፌደራል መጅሊስና የኦሮሚያ መጅሊስ አመራሮችን አናግረው በጎ ምላሽ እንደሰጧቸው ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ጋር በኦሮሚያና በሸገር ሲቲ መስጂዶች እንደማይፈርሱ ስምምነት መፈፀማቸውን ገልፀውልናል ብለዋል፡፡