Azmeraw mengistu

Azmeraw mengistu ጥበብ ከእግዚአብሄር የሚሰጥ ፀጋ ነው!

11/04/2024
07/04/2024

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሕዱ አምላክ አሜን
በዓለ ደብረ ዘይት
ትርጉሙ፦ ደበረ ዘይት ትርጉሙ የወራ መብቀያ፣ በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። ወይም «ደብር» ማለት «ተራራ» ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «ወይራ» ማለት ነው። በተገናኝ «ደብረ ዘይት» ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ የይወራ ተራራ ማለት ይሆናል።

ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ቦታ የሚገኝ ተራራ ሲሆን በመካከል የቄድሮን ሸለቆ ብቻ ነው ያለው። ከግርጌው ጌቴ ሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ ይገኛል። የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበትና በኋላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋዋ ያረፈበት ወይም የድንግል መካነ መቃብር በዚህ ተራራ ግርጌ ይገኛል። ቤተ ፋጌ እና ቢታንያ በኮረብታው ጫፍ እና በምስራቅ ዳገታ ላይ ይገኛሉ። ይህ ተራራ በመፅሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ብዙ ድርጊቶች የተደረጉበት ቦታ ነው። ጌታችን ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአት በዚህ ተራራ ላይ በትንቢት መልክ ተናገረ (ማቴ.24፥3)። በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዐረገ (ሉቃ. 24፥50)። በዚሁ ተራራ ላይ ቀን በከታማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት የሚያድርበት የኤሌዎን ዋሻ ይገኛል። በኋለኛው ምጽ አቱ በዚሁ ቦታ እንደሚገለጥ ትንቢት ተነግሯል።(ዘካ. 14፥3–5)።

ስያሜው፦ የዓቢይ ጾም እኩሌታ ላይ ያለው ሰንበት በዚህ ተራራ ተጠርቷል። ይህንን ዕለት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የዳግም ምጽአት አድርጎ መዝሙሩን ጽፏል። በዚህ ተራራ ላይ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3)። ተብሎ እንደተጻፈው ለደቀ መዛሙርቱ የደግም ምጻቱን፣ የዓለምን ፈጻሜ፣ የትንሣኤ ሙታንን፣ ትምህርት በሰፊው ስላስተማረ በዓሉ በተራራው ስም ተሰይሟል።

የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ
ከዕለታት አንድ ቀን ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሥነ ሕንፃ በትኩረት እያንዳንዱን ነገር በመመልከት አደነቁ። ጧት በጸሎት ጊዜ ጸሎታቸውን አድረሰው ሲጨርሱ የጧት ፀሐይ አርፎበት ያሸበረቀውን ቤተ መቅደስ ውበቱን አስተውለው ምን ጥበበኛ እንዳሠራው እየተነጋገሩ ጌታችንንም አብሮ እንዲያደንቅ ሲጠብቁ አስደንጋጭ ነገር ተናጋረ። ያ የሚያደንቁት ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ፤ አያይዞም ከሞት በኋላ ተነሥቶ እንደሚያረግና ነገር ግን ዓለምን ለማሳለፍ ዳግም እንደሚመጣ ወደፊት የሚሆኑ ሚሥጢራትን እና በቤተ መቅደሱና በሕዝቡ ላይ ሊደርስ ያለውን በትነሹ ጥቆመቸው። ይህም ነገር እረፍት ነሳቸውና ወደ ደብረ ዘይት ከተሻገሩ በኋላ በሰፊው እንዲገልጽላቸው ጠየቁት። ጥያቄውም «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3) የሚል ነው። በዚህ የጥያቄያቸው ክፍል እንደምናየው ጥያቄያቸው ዕለትና ምልክት ነው። ወይም «መቼ» እና «ምን» የሚል ነው። የቤተ መቅደሱ መፍረስ መቼ ይሆናል? የዓለም መጨረሻና የመምጣትህስ ምልክቱ ምንድን ነው? ጌታችንም በቀኙ ያቁመንና ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳይል በጥያቄያቸው ላይ ብቻ አተኩሮ ሰፊ መልስ ሰጥቷቸዋል።
መቼ ይሆናል ላሉት የመጀመሪያው ጥያቄ «ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም [ሰውም] ቢሆን የሚያውቅ የለም» (ማቴ.24፥.36)። ሲል አጭር መልስ ሲሰጥ።ስለ ሁለተኛው ጥያቄ ስለ ምልክት ጉዳይ ግን መሸከም እስኪያቅታቸው ድረስ አስተምሯቸዋል። በመልሱም ውስጥ ማስጠንቀቂያዎች፣ ምክሮች፣ ማጽናኛዎችና ምሳሌዎች በብዛት ቀርበዋል በተደጋጋሚ ተወስተዋል።

ምልክቶቹ፦
1ኛ/ ሐሰተኞች ክርስቶሶች

ጌታችን በአንደኛ ደረጃ የተናገረው ምልክት በተለያየ ጊዜ በተለያየ ሀገር ብዙ ሐሰተኞች ክርስቶሶች እንደሚነሡ ነው። የጌታ ቃል አይቀርምና ከዚህ ቀደም ብዙ ሰዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ተነሥተው ነበር። ዋናው በዮሐንስ ራእይ ዕራፍ 13 አውሬ ተብሎ የተጠቀሰውና በቅዱስ ጳውሎስ «የዐመፅ ሰው እርሱም የየጥፋት ልጅ» የተባለው ብዙ ጥፋትና መከራ የሚያደርሰው እና በለ 666 መለያ ምልክቱ ሐሳተኛ ክርስቶስ እሲከገለጥ ደረስ መንገድ ጥራጊዎች የሆኑ አለማማጅ ሐሰተኞች ክርስቶሶች ተነሥተዋል። በእውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ ዳግም መምጣት የሚደመሰሰው ሐሳዊ መሲሕ የመጨረሻውና ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚወጋ የታላቁ መከራ ፈጻሚና አስፈጻሚ ይሆናል። ለዚህ ነው መድኃኒታችን እስኪመጣ ድረስ እናዳንሰናከል አስቀድሞ «ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ … በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ» (ቁጥ. 5 እና 23) ሲል ያስጠነቀቀን።

በሀገራችንም በኢትዮጵያ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንገሥት እኔ ክርስቶስ ነኝ የሚል ሐሳዊ/ሐሰተኛ ክርስቶስ ተነሥቶ እንደነበር በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቧል። ይህ በሀገራችን ተንሥቶ የነበረው ሐሳዊ ክርስቶስ ልክ እንደ እውነተኛው ክርስቶስ 12 ሐዋርያት፣ 72 አርድእትና 36 ቅዱሳት አንስት አስከትሎ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያለ ሲንቀሳቀስ ንጉሡ አስቀርበው አንተ ማን ነህ? ቢሉት በድፍረት እኔ ክርስቶስ ነኝ አላቸው። ንጉሡም ክርስቶስማ ከደንግል ማርያም ተወልዶ አስተምሮ፣ ተሰቅሎ፣ ዓለምን አድኖ ከሞት ተንሥቶ ዐርጓል ዳግም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል አንተ ግን ማነህ? ቢሉት አዎ ትክክል ነው። ከዚህ ቀደም ከቤተ እሥራኤል ከምትሆን ከድንግል ማርያም ተወልጀ፣ አስተምሬ ተሰቅየ ሙቼ ተነሥቼ ዐርጌ ነበር፤ አሁን ድግሞ ጥቁሮች አፍርካውያን ባይታወር አደረገን እንዳይሉኝ ከእናቴ ከድንግል መርዐተ ወንጌል ለጥቁሮቹ ዳግም ተወልጀ ነው አላቸው። ንጉሡም ሰይጣን በሰው እያደረ እንዴት ይጫወታል ብለው በሰይፍ አስቀጡት ተካታዮቹም ተበተኑ ይባላል።

2ኛ/ ጦርነት

ጦርነት ዱሮም ነበረ። የዚህ ዘመን ጦርነት ግን የበዛና በብዙ ሀገራት የሚካሄድ ነው፣ የዱሮ ጦርነት ሴቶችን፣ አቅመ ደካማ ሺማግሌዎችንና ሕፃናትን ለእልቂት የማያጋልጥ ነበር። የዘመናችን ጦርነት ግን ማንንም የማይለይ ለማንም የማይራራ ሁሉን የሚደፈጥጥ የሁሉን ደም የሚያፈስ አስቃቂነቱ ከመግለጫ ቋንቋ በላይ ሆኖ ይታያል። ይህንንምም ጌታችን የዳግም ምጽ አቱን ምልክት ለጠየቁት ለደቀ መዛሙርቱ ሁለተኛ ምልክት አድርጎ «ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና» (ቁጥማቴ .6-7) ሲል ተናግሮታል።

3ኛ/ ረሀብ

የረሀብ ወሬ ወደ ሌላ ሀገር መሄድ ሳያስፈልገን በገዛ ሀገራችን የምናየው የምንዳሳሰው ያለው ለመርዳት የሌለው ለጸሎት የሚሮጥባት ሀገራችን ኢትዮጵያ አለች። ይህም ሰው ሰራሽ ችግር ለጠላቶቻችን ማሣለቂያ አድርጎን ይኖራል። በተለው የተፈጥሮ ችግር ሳያጋጥማት በሰው ሰራሽ ችግር 8 000 000 ሕዝብ ለአስቸኳ ምግብ ርዳታ የተጋለጠበት ሁኔታ ያሳዝናል። ይህም ዓይነት በጥልና በተንኮል በጭካኔ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር የምጽአት ሦስተኛ ምልክት ሆኖ በጌታችን ለደቀ መዛሙርት ተነግሯል «ረሀብም ቸነፈርም በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል» (ማቴ. 24፥7) ተብሎ እንደተጻፈ።

4ኛ/ የምድር መንቀጥቀጥ

የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት ዓመታት በርካታ ጉዳት በተለያዩ ሀገሮች እንዳደረሰ የሚዘንጋ አይደለም። በ1999፣ ጀምሮ እስከ ዛሬ በተለያዩ ሀገሮች በተለያየ ጊዜ የበዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ አያሌዎችን ቤት ንብረት አልባ ያደረገ የመሬት መቀጥቀጥ ተከሥቷል። በሄይቲ፣ በታይዋን፣ በቱርክ፣ በፊልፕንስ፣ ወዘተ ተከሥቷል። ይህም ለደቀ መዛሙርቱ የዓለም ፍጻሜ ምልክት የማግኘት ጥያቄ የተሰጠው «የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል» (ማቴ. 24፥7) ተብሎ በጌታ የዓለም ፍጻሜ ምልክት ተደርጎ የተነገረው ቃል አይቀርምና እየሆነ ነው።

5ኛ/ የክርስቲያኖች መከራ

የክርስቲያኖች መከራ እየጀመረ ይመስላል። ሰይጣን ኢቴስቶችን፣ እስላሞችንና አይሁድን በመጠቀም በክርስቲያኖች ላይ ከምን ጊዜውም በላይ ችግር መፍጠር የቸመረበት ጊዜ ነው። በአውሮፓ የክርስቲያኖች ጥያቄ ቶሎ የማይመልስ የቤተ ክርስቲያንን ጥያቄ ለማስተናገድም መንግስታዊ መሥሪያ ቤቶች ፈቃደኛነታችውን እያጡና ይህንን ወንጀላቸውን ለመሸፈንም በሕግ አንቀጽ እየፈጠሩለት ይታያሉ። «በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ» (ማቴ. 24 ቁጥ.9)። ተብሎ እንደተጻፈው ሃይማኖተኛነት እንደ ኋላ ቀርነት ከሐዲነት እንደተራማጂነትና ሥልጡንነት የሚታይበት ዘመን ላይ እንዳለን ግልጽ ነው። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ አመለካከት ክርስቲያኖችን ወደ ማግለልና ወደ መወንጀል የሚያድግ መሆኑ ከሚታዩት ፍንጮች መረዳት ይቻላል።

Address

Bole
Addis Ababa

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Azmeraw mengistu posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share