
18/08/2023
የአዲስ አበባ ፖሊስ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ያዘ
**********
የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ድርጅት ጋር በቅንጅት ባከናወነው ኦፕሬሽን በህገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ የተሳተፉ የንግድ ተቋማት ከበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ
ከህብረተሰቡ በመጣ ጥቆማ በቦሌ ክ/ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ መጠጥ (ውስኪ) ቤቶች በተደረጉ ጥናቶችና ጥናቶቹን መሰረት ተደርገው በተከናወኑ የኦፕሬሽን ተግባራት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገንዘቦች መያዛቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
ውስኪ ቤቶቹ በህጋዊ የንግድ ሽፋን ስም በጥቁር ገበያ ( ህገ ወጥ) የገንዘብ ምንዛሬ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበርም መረጋገጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያሳያል፡፡
በአጠቃላይ በአስራ አንድ ቤቶች በተደረገው የጥናትና የኦፕሬሽን ስራዎች በአምስቱ ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ የአስራ አምስት ሀገራት ገንዘቦች ከነ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
ከተያዙት ገንዘቦችም ውስጥ 2 ሚሊዩን 916 ሺ 800 የኢትዮጵያ ብር፣ 54 ሺ181 የአሜሪካ ዶላር፣ 34 ሺ 50 ዩሮ፣ 305 የእንግሊዝ ፓውንድ፣ 7 ሺ 719 የሳውዲ ሪያል፣ 11ሺ440 ድርሀም፣ 52 ሺ የሊባኖስ ፓውንድ፣ 80 ሺ640 የሱዳን ፓውንድ እንዲሁም የተለያዩ ስድስት ሀገራት የገንዘብ ኖቶች ተይዘዋል፡፡
በህጋዊ የንግድ ስራ ሽፋን ተሰማርተው መሰል የወንጀል ተግባራት ውስጥ የሚገቡ የንግድ ተቋማት ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ የወንጀል መከላከል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡