
21/07/2025
ከ14,000በላይ ለሚሆኑ የሰንበት ት/ ቤት ተማሪዎች በሀገረ ስብከት ደረጃ የብሔራዊ ፈተና ምዘና ማከናወኑን የአንድነቱ ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ ገለጹ።
ሐምሌ ፲፬/፳፻፲፯ ዓ/ሜ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ከ14,000በላይ ለሚሆኑ የሰንበት ት/ ቤት ተማሪዎች በሀገረ ስብከት ደረጃ የብሔራዊ ፈተና ምዘና ማከናወኑን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ተቀዳሚ ምከትል ሰብሳቢ ላእከ ኄራን ገለጹ።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በቡራኬ ያስጀመሩት የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ወቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል የምዘናው ማከናወኛ ሰንበት ትምህርት ቤት ጨምሮ በሁሉም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት በሚገኙ 160 የምዘና መውሰጃ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በተሳካ ሁኔታ የምዘና መርሐ ግብሩ መጠናቀቁን የአንድነቱ ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ ላእከ ኄራን መንክር ግርማ ገልጸዋል።
ላእከ ኄራን መንክር ግርማ አክለውም ተመዛኞች ዓመቱን ሙሉ በሰንበት ት/ቤቶች ሲማሩ መቆየታቸውን አስታውሰው በትናትናው ዕለት ከ168 ሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጡ 14,800 የሚሆኑ ተመዛኞች የተፈተኑ ሲሆን፤ በሁሉም የመፈተኛ ጣብያዎች ፈተናዎቹ መሰጠታቸውን እንዲሁም የቋንቋ እና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች አስተርጓሚ እና አንባቢ ተመድቦላቸው የተፈተኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ የሁሉም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት አንድነት ጽ/ቤት እና ትምህርት ክፍሎች በየክፍላተ ከተሞቻቸው ያሉ ተፈታኞችን የክትትል ጣቢያዎች አዘጋጅተው በጥሩ መልኩ ያስተባበሩ መሆናቸውን የክፍለከተማ ቤተክህነት ሓላፊዎችም በተመደቡበት ጣቢያ በመገኘት በጸሎት በመክፈት እና ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ የገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎችም በጸሎት በመክፈት እና አስፈላጊ ድጋፍ በመስጠት ለመርሐ ግብሩ መሳካት ሁሉም የበኩላቸውን ተወጥተዋል ብለዋል።
ዘገባው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት ነው።