
07/12/2021
"ከችግራችን በልጦ መገኘት!" ከንስር የምንማራቸው 9 ትምህርቶች
ከንስር ጠቃሚ ትምህርቶችን መቅሰም እንደምትችሉ ታውቃላችሁ? አዎ፣ በህይወታችሁ ጠንካራ መሆን እንድትችሉ የሚያስችሏችሁ የተለዩ ችሎታዎች አሏቸው። ንስር የሀይል፣ የድልና የጀግንነት ምልክት ነው። በአለም ላይ የሚገኙ ሃያ ሰባት አገራት በብሔራዊ አርማቸው ላይ አስፍረውታል።
1. የላቀ የእይታ አቅም
ንስሮች ታዳኞቻቸውን ቁልቁል እስከ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ መንጥረው ማየት ይችላሉ፡፡ አንድ ንስር ታዳኙን በሚመለከትበት ጊዜ የአይኖቹ ይጠብና ሙሉ ትኩረቱን ታዳኙ ላይ በማድረግ ለማጥቃት መብረር ይጀምራል።
በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም ጥርት ያለ እይታ ሊኖረን ይገባል፡፡ ግልጽ እይታ ካለን ከግባችን ለመድረስ ትኩረት በማድረግ ለመስራት ያስችለናል። ከንስሮች የምናገኘው የመጀመሪያው ትምህርት ምንጊዜም አይናችንን ከአለምነው ግብ ላይ አለማንሳት ነው፡፡
2. ከችግሮቻችሁ በላይ በልጣችሁ ተገኙ
ንስሮች አውሎ ነፋስ እና ዝናብ በሚበረታባቸው ወቅቶች ፍጹም ደስተኛ ይሆናሉ፤ ግዙፍ የሆኑ ክንፎቻቸውን ይዘረጉና አውሎ ነፋሱ ከደመና በላይ ወደላይ እየገፋ እንዲወስዳቸው ያደርጋሉ። ሌሎች ወፎች በዛፎች ቅርንጫፍ ውስጥ ሲደበቁ ንስሮች ግን ከደመናዎች በላይ በፈንጠዝያ እየቀዘፉ ይበራሉ። አውሎ ነፋሱ በሚነፍስበት ጊዜም ንስሮች ከላይ ሆነው ይመለከታሉ።
ይህ ከተፈጠረው ችግር በልጦ የመገኘትን ጥበብ ከንስሮች ልንማረው የሚገባ ትልቅ ትምህርት ነው። ብዙ ጊዜ ባጋጠሙን ችግሮች የተነሳ ተስፋ በማጣት ከአላማችን ስንዘናጋ ይታያል፡፡ ነገር ግን የችግራችንን ስፋት እና ጥልቀት በመገንዘብ ራሳችንን ከችግራችን አስበልጠን ማየት መቻል አለብን። ይህንን ስናደረግም ችግሮቻችንን ለመቅረፍ የምንከተላቸው መንገድ ተቀይሮ በብልሀት ወደ ውጤት እንዳረሳለን።