
29/07/2025
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት የ2017 ጉዞውን ገመገመ
( ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም)
ላዕከ ዜና አስቻለው ሽፈራው
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ዓመታዊ የግምገማና ሥልጠና መርሐ ግብር አካሄደ ።
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ቀናት በተካሄደው መርሐ ግብር የኢኦተቤ ቴቪ (EOTC TV) እና የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (AON) የ2017 ሪፖርት እና የ2018 ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል ።
መርሐ ግብሩ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት የበላይ ኃላፊ ፣ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎት የተከፈተ ሲሆን፣ ብፁዕነታቸው ጉባኤውን እየመሩ በሪፖርትና ዕቅዱ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል ።
በመርሐ ግብሩ ላይ በመገናኛ ብዙኃን ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ የነበሩ ክንውኖች፣ ስኬቶችና ክፍተቶች በየሥራ ክፍሎች በዝርዝር ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
ውይይቱን ተከትሎም ብፁዕነታቸው በሰጡት አባታዊ የሥራ መመሪያ ፣ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቱ ያላሻሻላቸው የሙያና የአስተዳደር ክፍተቶች አሁንም መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣዩ የሥራ ዓመት እነዚህ ክፍተቶች እርምት ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ውይይትና ግምገማው ቀጣይነት እንዳለውም ለተሰብሳቢዎች አሳውቀዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መምህር ዶክተር አካለወልድ ተሰማ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኦርቶዶክሳዊነት በዓለም ላይ እየገጠመው ስላለው ፈተናና ፣ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ኃላፊነት የሰጠቻቸው የቤተ ክርስቲያን ሚዲያዎች ስለሚጠበቅባቸው ድርሻ አብራርተዋል ።
በተጨማሪም መጋቤ ሐዲስ ለማ በየነ የአፋን ኦሮሞ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቴሌቭዥን ጣቢያው ከአፋን ኦሮሞ ጋር በስምንት የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ሥርጭቱን በውጭ ላሉ ተመልካቾች ጭምር ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ቴሌቭዥን ጣቢያውን በሙያና ቴክኖሎጂ ለማሳደግ በአስተዳደሩ በኩል ያለውን ፍላጎትና ዝግጁነት ገልጸዋል ።
በጉባኤው ሁለተኛ ቀን በዘመናዊ የሚዲያ አሠራርና በተቋማዊ ለውጥ ላይ ያተኮረ ሥልጠና፡ የአስተዳደርና ሥራ አመራር መምህር በሆኑት ዶክተር ግርማ መኮንን በስፋት ተሰጥቷል።
እንዲሁም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ታላላቅ የቴሌሽዥን ጣቢያዎች ሰፊ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ተገኝተው ለሁለቱም የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ዕውቀትና ልምዳቸውን በስልጠና አካፍለዋል።
የጉባኤው ተካፋዮች በስልጠናው ላይ የቀረቡት ሙያዊና አስተዳደራዊ ትምህርቶች ሰፊ ልምድ የቀሰሙበት እንደነበር በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል ።