
19/07/2025
ሐምሌ ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ አባ ሖር በሰማዕትነት ሞተ፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል
ሐምሌ ዐሥራ ሁለት በዚህች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። በዚች ቀን የፋርስ ንጉሥ ወደ ሆነ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት እግዚአብሔር ላከው ከሰናክሬም ሠራዊትም መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞች ወንዶችን ገደለ።
ይህም እንዲህ ነው ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን በከበባት ጊዜ ሕዝቅያስንና ፈጣሪው እግዚአብሔርን እየዘለፈ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ እንዲህም አለ እግዚአብሔር ያድናችኋል እያለ ሕዝቅያስ አያስታችሁ ከእጄ የሚያድናችሁ ማን ነው።
የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስም እጅግ አዘነ ወገኖቹንና ሀገሩ ኢየሩሳሌምንም ያድን ዘንድ ማቅ ለብሶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እግዚአብሔርም ልመናውን ተቀብሎ ወደ ፋርስ ንጉሥ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት የመላእክት አለቃ ሚካኤልን ላከለት። ድንቅ ሥራንም ሠርቶ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ሰዎች ሁሉ አዳናቸው።
ስለዚህም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የሚካኤልን በዓል መታሰቢያ በዚች ቀን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ።