St. Atonony Ethiopia catholic church Television network

St. Atonony  Ethiopia catholic church Television network CatholicTV broadcasts local & national religious programming Reaching the Ethiopian the Gospel of our Lord Jesus Christ.

Catholic TV is a non-profit organization and is funded by donations and gifts from people just like you. If you would like to join with us in spreading the good news, we would love to work with you towards that goal. Catholic TV is a 24-hour ambassador of what is truly good and honorable about the Catholic Church in Amharic. For many years, CatholicTV has provided the comfort and consolation of th

e daily Mass and Rosary, particularly for those who are hospitalized and homebound. In these times there is a great need to reach out to younger people, families and many who have become disenchanted with the Church. Simultaneously, we have come to a moment in history when television and the Internet are converging in a very powerful way. With innovative programming CatholicTV attempts to use these tools effectively to present the Lord Jesus and the gifts of His Church to a society longing for meaning and peace.

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን  የ2016 ዓ.ም የዓብይ ጾም መግቢያን በማስመልከት ያስተላለፉት መልእክትየተወደዳችሁ ካቶሊካውያን ምእመናንበአገር ውስጥና ከአገር...
09/03/2024

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2016 ዓ.ም የዓብይ ጾም መግቢያን በማስመልከት ያስተላለፉት መልእክት

የተወደዳችሁ ካቶሊካውያን ምእመናን
በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትገኙ ሁሉ
እንዲሁም በጎ ፈቃድ ላላችሁ ሰዎች በሙሉ

የእግዚአብሔር አምላክ ጸጋና ሰላም በያላችሁበት ይድረሳችሁ፡-

የዐብይ ጾም ወራት የክርስቶስን ስቃይ ሞትና ትንሳኤን ለማክበር የምንዘጋጅበት የሊጡርጊያ ወቅት ነው፡፡ በጾም ወራት ካቶሊካውያን ምእመናን ሶስት ነገሮችን በስፋት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይኸውም መጸለይ፣ መጾምና ምጽዋትን መስጠት ናቸው፡፡ እነዚህም የቤተክርስቲያን ትእዛዛት ናቸው፡፡

ይህ የጾም ጊዜ ንስሐ በመግባት ከአምላክና ከሰው ጋር የምንታረቅበት ጊዜ፣ በጸሎት ፈጣሪን የምንለምንበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር የምንሆንበት ጊዜ፣ እንዲሁም ካለን ለሌላቸው የምናካፍልበት የምጽዋት ወቅት ነው፡፡ ስለ ምጽዋት ሲናገር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡ ‹‹ድሆች ከሃብታችን እንዳይካፈሉ መከልከል ከእነርሱ መስረቅ፣ ሕይወታቸውንም መንሳት ነው፡፡ የያዝነው ኃብት የእኛ አይደለም የእነርሱ እንጂ›› (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁጥር 2446)፡፡

አርባ ቀናትና አርባ ሌሊት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያመለክተው የፈተና የንስሐ የመንጻትና የመታደስ ጊዜ እንደሆነ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ 40 ቀናት ኢየሱስ ወንጌልን የመስበክ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በበረሃ የተፈተነበትን ጊዜ ያመለክታል፤ ‹‹መንፈስ ቅዱስም …ወደ በረሐ መራው፤ በሰይጣንም እየተፈተነ አርባ ቀን በበረሐ ቆየ››ይላል፡፡ (ማር.1፡12-13)፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት የኑሮ መወደድና የሰላም መታጣት ፈተና ውስጥ መሆናችንን እንረዳለን፡፡ በመሆኑም በዚህ የጾም ወቅት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈተናዎች እንድናስብና መልክታቸው ምንድን ነው የሚለውን እንድናስተነትን ግድ ይለናል፡፡

በጾም ወራት ከምንጋፈጣቸው ነገሮች አንዱ ከዓለምና ተሸክመነው ከምንዞረው ስጋችን እንዲሁም ከሰይጣን በኩል የሚመጡብን ፈተናዎች ናቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ የተፈተነባቸው ሶስት ፈተናዎች የእኛም ፈተናዎች ናቸውና እንዳይጥሉን እንዘጋጅ፡፡ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሥጋዊ ምቾትን የመሻት ፈተና
‹‹ፈታኙም ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰለት (ማቴ.4፡3-4)፡፡ ይህ ፈተና ስጋዊ ምቾትን የመሻት ፈተና ልንለው እንችላለን፡፡ ሆድ ሲሞላ የምግብ ጥያቄ ሲመለስ ስጋችን ሌላም ነገር ይሻል፣ ድሎትን፣ ስጋዊ አምሮት እንዲሟላለት ይፈልጋል፣ ይህም አንዱ ፈተናችን ነው፡፡ የምንደክመው ጠግበን ለመብላት ብቻ ሳይሆን አማርጠን ለመብላት ጭምር ነው፡፡

ሰዎች ለመኖር መብላት አለባቸው፤ ለመብላት ደግሞ መስራት የግድ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ያለው የማይሰራ አይብላ የሚል ነው፡፡ ‹‹እንጀራዬ ለእኔ መስታወቴ ነሽ፣ ሁልጊዜ የሰው ፊት ታሳዪኛለሽ›› እንደሚለው የሰው ፊት የሚያሳየን የእንጀራ ጉዳይ ነው፡፡ ስራ ያለው ሰርቶ ሲበላ ስራ ያላገኘ ሰው ሲንከራተት ማየት ያሳምማል፤ የኑሮ ውድነት እንኳንስ የሚበላ ነገር ለማማረጥ ቀርቶ በቀን ሶስት ጊዜ ለመብላት የሚቸገሩ ቤተሰባቸውን የሚያቀምሱት አጥተው ጭንቅ የዋጣቸው ቤቱ ይቁጠረው፤ ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት እድል የሚፈጠረው፡፡

በርግጥ ደልቷቸው የሚኖሩ ነገር ግን ሰዎች ተርበዋል ቢሏቸው ረሃብ ምን እንደሆነ በእውነትም የማይገባቸው ጥቂት ሰዎች አይጠፉም፡፡ እኛ ግን ይህንን ጾም በምንጾምበት ጊዜ የተራቡ ወገኖቻችንን የምናስብበትና ካለን የምናካፍልበት ሊሆን ይገባል፡፡ ከምግብ መራቅ አንዱ የመጾሚያ መንገድ ሲሆን የተራቡትን መመገብና ካለን ለሌሎች ማካፈል ሁለተኛው ነው፡፡ ፈተናችን እዚህ ላይ ነው፣ ምን ያህል ተካፍለን እንበላለን? የምንኖረው ለመብላት ነው ወይስ ለመኖር ነው የምንበላው? ሰዎች ተርበዋል የሚበሉት ነገር የለም ስትባል ለምን ኬክ አይበሉም እንዳለችው ንግስት እኛ በልተን ስናድር ሁሉም ሰው በልቶ የሚያድር ይመስለን ይሆን? ራሳችንን ማየት መፈተን ይኖርብናል፣ ፈተናውን ልናልፍ ይገባል፣ ካለን ላይ በማካፈል ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር በማሳየት፣ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ሰፊ ቦታ በመስጠት፣ ስጋን በጾም ማስራብና እየተራበ የሚጾመውን ሕዝባችንን የመመገብ ኃላፊነትን ምን ያህል እንወጣለን የሚለውን ፈተናችንን የምንመልስበት መንገድ የሚታይበት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ከዲያብሎስ የቀረበለት ፈተና ስልጣኑን በመጠቀም ድንጋዩን ወደ ዳቦ እንዲለውጥ የሚል ነበር፡፡ እኛም በተሰጠን ስልጣን ልንሠራ የሚገባን ለእግዚአብሔር ክብርና ለጋራ ጥቅም መሆኑን ያስታውሰናል፡፡ በዛሬ ጊዜ ራሳችንን መጠየቅ የሚገባን ስልጣናችንና ኃላፊነታችን ልምዳችንና ትምህርታችን ሳይማር ላስተማረንና እንድናገለግለው ለመረጠን ሕዝብ ጥቅም እያዋልነው ነውን ወይስ አይደለም የሚለው ነው፤ ፈተናችን ይህ ነው፣ ምን ያህል ለገባነው ቃል ኪዳን በመኖር ሕዝባችንን በቅንነትና በታማኝነት እናገለግላለን፣ በእውነት የሚያገለግሉትን ምን ያህል እናመሰግናለን፣ ተበለሻሸ ለምንለው አሰራር መስተካከል ምን ያህል እንጸልያለን፣ ከዚህም ባሻገር ኃላፊነታችንንና ስልጣናችንን በመጠቀም ለእግዚአብሔር ፈቃድ ምን ያህል እንገዛለን የሚል ሊሆን ይገባል፡፡

ትኩረትን የመሻት ፈተና
በሁለተኛው ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ የተጠየቀውና ያለፈው ፈተና ትኩረትን የመሻት ፈተና ነው፡፡ ቀጥሎም ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ በመውሰድ ከቤተ መቅደሱም አናት ላይ አውጥቶ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘እግርህ በድንጋይ እንዳይሰናከል፣ በእጃቸው ያነሱህ ዘንድ፣መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል ”። ኢየሱስም፣ “እንደዚሁም በመጻሕፍት፣ ‘እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ተጽፏል” (ማቴ.4፡ 5-7)በማለት መለሰለት።

በእግዚአብሔር ላይ ከመተማመንና እሱን ከመታዘዝ ይልቅ ተአምር ካላደረክ ብሎ እሱን የማዘዝ ያህል ማስቸገር እርሱን መፈታተን ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ሰላም እንደሚያስፈልገን እያወቅን የሰላም መሳሪያ ለመሆን ከሁሉም ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት ማድረግ ሲገባን እንዲያው በደፈናው ጌታ ሆይ የሰላም መሳሪያ አድርገኝ ማለት ብቻውን በቂ አይሆንም፣ ስለዚህ ፈተናችን የሚሆነው የሚጠበቅብንን እናደርጋለን ወይስ የእኛን ድርሻ ለፈጣሪ በመተው ተአምር እንዲያደርግ እንጠብቃለን፡፡
በራሳችን ለራሳችን ማድረግ የሚገባንን ነገር ማድረግ እየቻልን እርሱ ካላደረገ ማለት አምላክን እንደመፈታተን ነው፤ ለምሳሌ የምንራመድበትን እግር እስከሰጠን ድረስ በእግራችን መራመድ ሲገባን ክንፍ ካልሰጠኸኝ ብሎ ተአምር መጠበቅ እርሱን መፈታተን ያስመስልብናል፡፡ በዚህ የጾም ወራት የምንፈተነው ተአምር ፈላጊዎች ነን ወይስ በእምነት አምላካችንን እንታዘዛለን፣ የምንፈልገውን ነገር ሰርተን ከማግኘት ይልቅ በአቋራጭ እንዲሆንልን ወይም ተአምር እንዲደረግ የምንሻ ከሆነ ፈተናውን ወድቀናልና እንደገና ቃሉን ታጥቀን ምላሽ በመስጠት ፈተናውን ልናልፍ ይገባል፡፡ ይህ ፈተና አምላካችንን ጠይቀን እርሱ በእኛ በኩል በሚያከናውናቸው ነገሮች አማካይነት እኛ በሰዎች ዓይን እንድንደነቅ ትኩረትን የመፈለግ ፈተና ነው፡፡ መታየት፣ መሰማት፣ መወደድ፣ መደነቅ ወዘተ…ፈተናዎቻችን ናቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ከፍ ከፍ ሊል እኛ ግን ዝቅ ዝቅ ልንል እነዚህ የጾም ወራት ይጋብዙናል፡፡

ምድራዊ ስልጣንን የመሻት ፈተና
ሶስተኛው ጌታችን ኢየሱስ የተፈተነው ጥያቄ እግዚአብሔርን በመካድ ምድራዊ ስልጣንን እንዲቆናጠጥ የተሰጠው ምርጫ ነው፡፡ እንደ ገናም ዲያብሎስ ኢየሱስን እጅግ ከፍ ወዳለ ተራራ አወጣው፤ የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው አሳየውና፣ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፏልና” አለው (ማቴ.4፡9-10) ።

ጌታችን ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ወንጌሉን ይሰብክ ዘንድ የአባቱን ተልእኮ ሊፈጽም ነፍሳትን ለማዳን የጠፉትን ለመፈለግ ተልእኮ ሲሆን ዲያብሎስ ያቀረበለት ጥያቄ ፈታኝነቱ አምላክን ከማገልገልና እርሱን ከማምለክ ይልቅ ለእኔ ተገዛ አገልጋይ ሁን የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡ የጌታችን ኢየሱስ መልስ ግን ከሰይጣን ጋር መስማማትን ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክን ማምለክ ለእርሱ ብቻ መስገድና ለእርሱ አገልጋይ መሆን እንደሚገባ አስረግጦ ይናገራል፡፡

ዛሬም የብዙዎቻችን ፈተና እግዚአብሔር አምላክ በሰጠን ስልጣን ባስቀመጠን የኃላፊነት ቦታ ላይ በፍቅር እናገለግላለን? ሲሾም ያልሰራ ጡረታ ሲወጣ ይጸጸታል እንላለን ወይሰ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል በሚል ዓይነት ስልጣናችንን አላገባብ እየተጠቀምን ነው? ሌሎች በአገልግሎታችን ይደሰታሉ? አምላክን ያመሰግናሉ? ወይስ በእኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ይማረራሉ? ይህ የጾም ወቅት ራሳችንን የምናይበትና የምንፈተንበት ጊዜ ነው፡፡ ኃላፊነት ከሰሩበት ካገለገሉበት በረከቱ ለሁላችንም ነው፤ ፈተናችን የሚሆነው መስራት በሚገባን ጊዜና ቦታ ለሕዝባችን ማገልገል ሲገባን ስልጣናችንን ለማሳየትና ሌላ ተጨማሪ ከፍያ ተጨማሪ ክብር ከፈለግን፣ በማገልገላችን ልንከበር ሲገባ ቦታው ላይ በመቀመጣችን ብቻ ክብር ካልተሰጠን የሚል ስሜት ከተሰማን፣ ፈተናውን ወደቅን ማለት ነው፡፡ ፈተና የምንወስደው ለማለፍ እንጂ ለመውደቅ አይደለም፤ በዚህ የጾም ወራት ፈተናችንን ለማለፍ ልንዘጋጅ ይገባል፡፡ እንዲሁ የሚደረግ ጾም የለምና ለጥያቄአችን መልስ እንድናገኝና እግዚአብሔርን በማዳመጥ ፈቃዱን ለማድረግ እንጹም፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ፈተናችንን አልፈን፣ ንስሐ በመግባት ከእርሱና ከሰዎች ሁሉ ጋር ታርቀን ካለን ላይ ለወገኖቻችን አካፍለን እርሱ ወደፈለገው የፍቅርና የሰላም ኑሮ መኖር እንድንችል ጾምና ጸሎታችንን ይቀበልልን፡፡ ለትንሳኤው ብርሃን በሰላም ያድርሰን፡፡

አገራችን ኢትዮጵያን ይባርክልን !
እርቀ ሰላሙን ያውርድልን !
አሜን!

የእምድብር  ሀገረስብከት የ20 ዓመታት ጉዞ እግዚአብሔር በሰራው ድንቅ ሥራ ፤ የመጀመሪያው ታላቁ ተባባሪ ፤ ፊታውራሪ እና መልካም እረኛ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሙሴክቡር አባ ሀብቴ የእምድብር ...
15/02/2024

የእምድብር ሀገረስብከት የ20 ዓመታት ጉዞ እግዚአብሔር በሰራው ድንቅ ሥራ ፤ የመጀመሪያው ታላቁ ተባባሪ ፤ ፊታውራሪ እና መልካም እረኛ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሙሴ

ክቡር አባ ሀብቴ የእምድብር ሀገረስብከት ጽ/ቤት ኃላፊ ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ

“ብፁዕ አቡነ ሙሴ ባለፉት 20 ዓመታት በሀገረስብከታችን በአባታችን መልካም እረኝነት 15 አዳዲስ የቤተክርስቲያን ሕንጻ ተገንብተዋል ፤ እንደዚሁም አዳዲስ ቁምስናዎችም ተመስርተዋል ፡፡ እጅግ ያማረ የሀገረስብከቱ ጳጳስ መኖሪያ አሳንጸዋል፡፡ የሀገረስብከቱ የወንጌል ስብከት ስራ ማስተባበሪያ ደረጃውን የጠበቀ ጽህፈት ቤት አቋቁመዋል፡፡ በተጨማሪም 12 የተለያዩ የወንዶች እና የሴቶች ገዳማዊያን መኅበራት በሀገረስብከታችን ገዳም ከፍተው ህዝባችንን በነፍስ እና በስጋ ያገለግሉ ዘንድ አድርገዋል፡፡
ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የረኝነት ሥራዎን ሲጀምሩ፤ መመሪያዎ ሊያደርጉት ከጌታ የተቀበሉትን፤ “ …ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ..” የሚለው የጌታ ጸሎት እውን እንዲሆን ጌታ በሰጦት ጥበብ ተመርተውበታል ፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የጠበቀ ሕብረት ይኖረን ዘንድ በተግባርም ሆነ በቃል የሚቻሎትን ሁሉ አድርገዋል ፡፡ ከወንጌላውያን አማኞች ወንድም እህቶቻችን ተባብረን እንሰራ ዘንድ አስተምረዉናል፡፡ ለሙስሊም ወገኖቻችን ክብር እና ፍቅር ይኖረን ዘንድ መርተውናል፡፡
በሀገረ ስብከታችን ፤ መላውን የሀገረስብከታችን ሕዝብ ያለ ምንም ልዩነት ፤ የትምህርት ብርሃን የሚያይበት ትምህርት ቤቶችን ፤ ታክሞ ጤናው የሚጠብቅበት ጤናጣቢያዎችን እና ሆስፒታሎችን ፤ ታላላቅ እና ሰፋፊ የውሃ እና የግብርና ስራዎችን ፤ የአረጋውያን መንከባከቢያ ፤ የወጣቶች እና የሴቶች ማስልጠኛዎችን ፤ በመገንባት ያለምንም ልዩነት ሁሉም ሰው ሁለተናዊ እድገት አግኞቶ ፤ እግዚአብሔር በሰጠው ሰብአበዊ ክብር መኖር ይችል ዘንድ ሳይታክቱ ደከመኝ ሳይሉ ሰርተዋል ፡፡
በተጨማሪም በአደራ የተረከቡትን ሀገረስብከት በሁለመናው እራሱን ችሎ ቆሞ ወደፊት ይራመድ ዘንድ በመንፈስም ሆነ በስጋ የቆመ ይሆን ዘንድ በማሰብ በቁምስናዎቻችን እና በሀገረስብከታችን ገቢ ያሚያስገኙ ንብረቶችን በማፍራት ፤ ብልህ እና ታማኝ አገልጋይ ማድረግ ያለበትን አድርገዋል፡፡
ከሁሉ በላይ ግን ፤ ኢትዮጵያዊነት እና ካቶሊካዊነት አወኅደው ቅድስት ቤተክርስቲያን የምታስተምረውን እና የምታዘውን በሕይወታቸው ኖረው አሳይተውናል፡፡ እኛም በሀገረስብከቱ የምንገኝ ካህናት እና ምእመናን ፤ ኢትዮጵያዊ ካቶሊካውያን ሆነን በማንነታችን ፣ በባሕላችን ፣ በቋንቋችን እንድንኮራ ፤ ባህላችን እና ሥርዓታችን እንድንወደው ፣ እንድናከብረው ከሁሉ በላይ ደግሞ ኖረንበት እንድንቀደስበት ፤ ኖረውበት እንድኖርበት አስተምረውናል፡፡”

ክቡር አባ ሀብቴ የእምድብር ሀገረስብከት ጽ/ቤት ኃላፊ ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ

የክርስቶስን መወለድ በአግባቡ ለማክበር ለሰው ልጆች ሕይወት፣ ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያንና ለእርሱ ቅዱስ ስፍራዎች ክብርን ስንሰጥ ነው! ቤተክርስቲያኗ የክርስቶስ የልደት በአል በማስመልከት ...
05/01/2024

የክርስቶስን መወለድ በአግባቡ ለማክበር ለሰው ልጆች ሕይወት፣ ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያንና ለእርሱ ቅዱስ ስፍራዎች ክብርን ስንሰጥ ነው!

ቤተክርስቲያኗ የክርስቶስ የልደት በአል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፋለች።

በመልዕክቷም ከራስ ወዳድነት መንፈስ እንውጣ በመላው አገራችን ሞት ይብቃ፣ ሰላም ይስፋፋ ብላለች።

የተራቡ፣ የተጠሙ፣ የታረዙ፣ የተበደሉ፣ የታመሙና የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን እናስታውስ ስትልም ገልጻለች።ከጎናቸው እንሁን እንርዳቸው እናጽናናቸው፡፡

ለኛ ምን ይደረግልን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ምን እናድርግ እንበል፤ መጠጊያ ለሌላቸው መሸሸጊያ እንሁንላቸው፡፡የሚገለሉ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው እናድርግ፡፡

ዘመዳቸው እንሁን፡፡ ምክንያቱም የልደት በዓል ክርስቶስ ዘመዳችን እንደሆነ የሚያበሥረን በዓል ነውና፡፡ በልደት ምስጢር ማንም እንግዳ ሊሆን አይገባውም፡፡

የሰው ልጅ ለማኅበራዊ ችግሮቹ መፍትሔ ይፈልጋል፣ ሊፈልግም ይገባዋል፡፡

ነገር ግን ቆም ብሎ ከእርሱ የማሰብ ችሎታና አድማስ ባሻገር መመልከት ሲችል ብቻ ነው መፍትሔን የሚያገኘው በትህትና ወደ ምጡቁ አምላክ ሲመለከት ነው፡፡

ለፍትህ፣ ለእውነትና ለመልካም ነጻነት መሥራት የማንነቱ መሠረት መሆኑን የሚረዳው የልደት በዓልም ለፍትህ፣ ለእውነትና ለመልካም ነፃነት ሰውን የሚጠራ በዓል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በቅርቡ ከቅድስት መንበር የጳጳሳዊ የእምነት አስተምህሮ ጽ/ቤት ስለ ሐዋርያዊ ቡራኬ ባስተላለፈው ሰነድ ላይ የተሰጠ ማብራሪያ
21/12/2023

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በቅርቡ ከቅድስት መንበር የጳጳሳዊ የእምነት አስተምህሮ ጽ/ቤት ስለ ሐዋርያዊ ቡራኬ ባስተላለፈው ሰነድ ላይ የተሰጠ ማብራሪያ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ አባ ተሾመ ፍቅሬን ለእምድብር ሀገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ “ኮ - አጁተር” እንዲሆኑ ሰየሙ::  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ አባ ተሾመ ፍቅሬን አዲሱ የእ...
17/12/2023

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ አባ ተሾመ ፍቅሬን ለእምድብር ሀገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ “ኮ - አጁተር” እንዲሆኑ ሰየሙ::

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ አባ ተሾመ ፍቅሬን አዲሱ የእምድብር ሀገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ “ኮ-አጁተር” ብለው መሰየማቸውን ቫቲካን ታህሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. አውጇል።

አባ ተሾመ በቀድሞው በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በናደነ ቅዱስ ማርቆስ ቁምስና ተወልደው ያደጉ ሲሆን በአዲስ አበባ ልደታ ማርያም ካቴድራል ማዕረገ ክህነት ተቀብለዋል።
ባሳለፍነው 2015 ዓ.ም. 25ኛው የብር ኢዮቤልዩ የክህነት በዓላቸውን ያከበሩት አባ ተሾመ ፍቅሬ በክህነት አገልግሎታቸው ከቁምስና እስከ ሀገረ ስብከት ጠቅላይ ጽ/ቤት አገልግለዋል። በ1996ዓ.ም. እምድብር አዲስ ሀገረ ስብከት ሆኖ ሲመሰረት የአዲሱ ሀገረ-ስብከት ጠቅላይ ጸሐፊ ሆነው እስከ 2011ዓ.ም. ድረስ ያገለገሉ ሲሆን፤ ከነሐሴ 2011ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። በትምህርት ዝግጅታቸው በሕገ ቀኖና የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ይህንንም በሮም ከሚገኘው የላተራን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ደስታውን እየገለጸ ለክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ የተባረከ የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንላቸው ይመኛል፡፡

አባ ቱሬን በተወለዱ በ99 አመታቸው ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል።   በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በደብረ ዘይት ገሊላ የሱባኤ ማዕከል የምናውቃቸው አባት አባ ቱሬን በተወለዱ በ99 ዓመታ...
12/12/2023

አባ ቱሬን በተወለዱ በ99 አመታቸው ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በደብረ ዘይት ገሊላ የሱባኤ ማዕከል የምናውቃቸው አባት አባ ቱሬን በተወለዱ በ99 ዓመታቸው ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል።
አባ ቱሬን በእ.አ.አ 1945 ዓም በንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ጥሪ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የተፈሪ መኮንን ት/ቤትን እንደገና ከማዋቀርና በማስተማር ብዙ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወይንም የቀድሞው ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ኮሌጅ በዘመናዊ መልክ ሲቋቋም እና ሲዋቀር ጭምር አስተዋጽኦ ካበረከቱ መሀከል አባ ቱሬን አንዱ ነበሩ።
አባ ቱሬን በርከት ያሉ መንፈሳዊ መጽሐፍትን በመጽሐፍና በመተርጎም ለአንባብያን አበርክተዋል።
በኢትዮጵያ ለ64 ዓመታት የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት የታውቃሉ ።
የጽዮን ማርያም ማህበራዊ ድረ-ገጽ ለኢየሱሳውያን ወንድሞች ገዳም መጽናናትን እንመኛለን።
https://t.me/TsionMariamCatholicChurch
https://t.me/tsion_mariam_catholic

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት የ2015 ዓ.ም የፍልሰታ ማርያም በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክ...
22/08/2023

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት የ2015 ዓ.ም የፍልሰታ ማርያም በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት

«ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባስ ወርቅ ዑጽፍት ወኀብርት፣ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፍና ነግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች»(መዝ. 45፣10 )

የተከበራችሁ ብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግላን፣ ዲያቆናት፣ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

እንኳን ለ2015 ዓ.ም ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰታ ማርያም በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የፍልሰታ በዓል ዛሬ እያከበርን እንገኛለን። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች” (ሉቃስ 1፡46-47) በማለት ውዳሴ ታቀርባለች። በዚህ ጸሎት ውስጥ “ከፍ ከፍ ታደርገዋለች እና ሐሴት ታደርጋለች” የሚሉትን ሁለት ግሶች እንመልከት። ሐሴት የምናደርገው በሕይወታችን ውስጥ በጣም ውብ የሆነ ነገር ሲከሰት፣ እንዲሁ በውስጣችን ያለውን ደስታ በቀላሉ በመግለጽ ሳይሆን፣ ነገር ግን ነፍሳችንን እና መላው ሰውነታችን ተሳታፊ በሚሆኑበት ሁኔታ በተቀናጀ መልኩ ሐሴት በማድረግ ለመግለጽ እንፈልጋለን። የማርያም ሐሴት የመነጨው ከእግዚአብሔር ነው። እኛም በሕይወታችን ውስጥ በጌታ ተደስተን ደስታችንን በሐሴት ገልጸን ሊሆን ይችላል፣ በአንድ ነገር ውጤታማ በምንሆንበት ወቅት ተደስተን ሊሆን ይችላል፣ መልካም የሆነ ዜና ሲያጋጥመን ደስታችንን ገልጸን ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ዛሬ ማርያም በጌታ እንዴት ሐሴት ማድረግ እንደሚቻል ታስተምረናለች፣ ምክንያቱም እርሱ “ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልናልና”።
በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥሙን ታላላቅ የሚባሉ ክስተቶች ደግሞ ታላቅ ነገር ያደረግልንን ፈጣሪ ከፍ ከፍ እንድናደርግ ያነሳሳናል። በእውነቱ ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት ለታላቅነቱን፣ አንድ ታላቅ የሆነን ነገር በእውነቱ ከፍ ማድረግን የሚያመልክት ሲሆን ለታላቅነቱ እና ለውበቱ እውቅና በመስጠት እርሱን ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት ነው። ማርያም የጌታን ታላቅነት ከፍ ከፍ ታደርጋለች ፣ በእውነት ታላቅ ነው ብላ አመስግነዋለች። በህይወት ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን መሻት አስፈላጊ ነው ፣ አለበለዚያ በብዙ ትናንሽ ነገሮች እንወሰዳለን። ሕይወታችን ደስተኛ እንዲሆን ከፈለግን፣ በሕይወታችን ውስጥ ለእግዚአብሔር ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ማርያም ታሳየናለች፣ እርሱ ብቻ ታላቅ እንደ ሆነ ታስምረናለች። እነዚህን ታላላቅ የሚባሉ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው ብዙ ጥቅም የማይሰጡ ነገሮችን ለምሳሌም ጭፍን ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ብጥብጥ ፣ ምቀኝነት ፣ ከልክ በላይ በሆነ መልኩ ለቁሳቁሶች ያለንን ፍላጎት . . . ወዘተ የምንከተልባቸው ብዙ ወቅቶች አሉ። በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ስህተት እንፈጽማለን። ማርያም ጌታ በእርሷ ውስጥ ያከናወናቸውን “ታላላቅ ነገሮች” እንድንመለከት ዛሬ ትጋብዘናለች።
ዛሬ የምናከብራቸው “ታላላቅ ነገሮች” ናቸው። ማርያም ወደ ሰማይ ፈልሳለች፣ ትሑት የሆነች ማርያም ከሁሉም በፊት ከፍተኛ ክብርን ተቀበለች። እንደ እኛ ፍጡር የሆነች እርሷ በነፍስ እና በሥጋ ዘላለማዊ ትሆናለች። እናቶች ልጆቻቸው ከሄዱበት ቦታ ወደ ቤት እስኪመለሱ ድረስ እንደ ሚጠብቁ ሁሉ እርሷም እኛን በእዚያ በሰማይ ቤት ሆና ትጠባበቀናለች። በእርግጥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ እርሷን “የሰማይ ደጃፍ” እያሉ ነው የሚያወድሷት። እኛም ወደ ሰማይ ቤት የምንጓዝ ምጻተኞች ነን። ዛሬ ማርያምን ቀና ብለን ወደ ሰማይ እንመለከታለን፣ በእዚያም የእኛ መዳረሻ የሆነውን ግባችንን እናያለን። አንድ እንደኛ ፍጡር የሆነች ከሙታን ወደ ተነሳው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር እንደ ተወሰደች እናያለን፣ ያቺ እንደኛ ፍጡር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳኛችን እናት በመሆን ከጎኑ ትቀመጣለች። በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ አዲሱ አዳም የሆነው ክርስቶስ አዲሲቷ ሔዋን ከሆነችው ማርያም ጋር በጋራ በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ እናያቸዋለን፣ እኛም በእዚህ ምድር ምጻተኞች ሆነን በምንኖርበት ጊዜ ለእኛ ታላቅ የሆነ መጽናናትን እና ተስፋን ይሰጠናል።
የማርያምን የፍልሰታ አመታዊ በዓል በምናክብርበት በአሁኑ ወቅት ለሁሉም የሰው ልጆች በተለይም በጥርጣሬ እና በሐዘን ለተሰቃዩ እና ዓይኖቻቸው ወደ ታች ወደ ምድር አቀርቅረው ተክዘው ለሚገኙ ሰዎች ጥሪ ይቀርብልናል። ቀና ብለን ክፍት የሆነውን ሰማይ እንመልከት፣ ፍርሃት ሊያድርብን በፍጹም አይገባም፣ በጣም ሩቅ የሆነ ሥፍራም አይደለም፣ ምክንያቱም በሰማይ ደጃፍ ላይ የምትጠብቀን አንድ እናት አለችና። የሰማይ ንግሥት የሆነችው እርሷ የእኛም እናት ናት። እርሷ ትወደናለች፣ ፈገግታዋንም ታሳየናለች፣ ትንከባከበናለችም። እያንዳንዷ እናት ለልጆቿ የተሻለውን ነገር እንደ ምትፈልግ እና እንደ ምታስብ ሁሉ “በእግዚአብሔር ፊት ውድ ናችሁና፣ እናንተ የተፈጠራችሁት ትንንሽ የሆኑ የአለም ነገሮችን ለመፈጸም ሳይሆን፣ ነገር ግን እናንተ የተፈጠራችሁት ለሰማይ ታላቅ ደስታ ነው” በማለት ተናገረናለች። አዎን! ምክንያቱም እግዚአብሔር አስደሳች አምላክ ነውና። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጃችንን ይዛ እንድትመራን እንፍቀድላት። በእያንዳንዱ ቀን መቁጠሪያችንን በእጃችን ይዘን የመቁጠሪያ ጸሎት በምናደርግበት ወቅቶች ሁሉ ሕይወታችን ወደ ላይ አንድ እርምጃ እንዲራመድ እናደርጋለን ማለት ነው።
በዛሬ ቀን የቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ላይ ማርያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ገነት በማረግ ክብር ማግኘቷ ላይ እናሰላስላለን። ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስቃይ፣ በመከራ እና በመስቀል ላይ ሞቶ፣ በትንሳኤው ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ ሁሉ፣ እርሷም እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ላይ በመፍለስ ሁለቱም እናት እና ልጅ ወደ ሰማይ እንደ ወጡ ከቅዱስ ወንጌል እንማራለን። ይህ በአጠቃላይ ሲታይ ያለ መስቀል ትንሳኤ፥ ያለ ጭንቀት፣ ሐዘን እና መከራ ፍልሰታ እንደ ሌለ እንማራለን። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት የሚያሳየንም ይህንኑ ነው።
እግዚአብሔር ያቺን ከሁሉም የበለጠች ፍጥረቱን እንደ ሁሉም ሰው በኃጢአት ቆሻሻ እንድትነካ ባይፈቅድም ነገር ግን በምድር ለሚኖሩ ለሰው ልጅ ሁሉ ከሚደርስባቸው ሐዘንና ስቃይ ነጻ እንድትሆን ግን አልፈቀደላትም። እንደ ማንኛውም ሰው እንድትሰቃይ ተዋት። እመቤታችን ማርያም ከሌሎች የበለጠ ሐዘን መከራና ስቃይ ተቀበለች። በስቃይ በኩል ከኢየሱስ ሌላ የሚበልጣት የለም። ቅዱሳን ሰማዕታት ገጥሟቸው ከነበረው የከፋ መከራ እንኳን ከእመቤታችን ማርያም ጋር ሊወዳደር አይችልም። እርሷ ከልጇ ከኢየሱስ ጋር በመሆን ብዙ ስቃይ አሳለፈች።
ሰለዚህም ቅዱሳን «ሰማዕተ ሰማዕታት፣ ንግሥተ ነግሥታት» እያሉ ይጠሯታል። የማርያም ሰማዕትነት ከሌሎች ሰማዕታት የሚበልጠው በሥጋዊ ስቃይ ሳይሆን በመንፈሳዊ በኩል እንደሆነም ይናገራሉ። ይህም ስቃይ እንደ አንድ የተሳለ ሰይፍ ልቧን ይሰንጥቀው እንደነበር ቅዱሳኖቹ ያውቃሉ። ቅዱስ በርናርዶስ «የማርያም ሰማዕትነት ከብረት የጠነከረ ነው» ይላል። ኢየሱስ እንደ ተወለደ የእርሱ ስቃይ ወዲያው ጀመረ። የእርስዋም ስቃይ በዚያው ጀመረ። የልጇን ስቃይና ውርደት በማሰብ በመሰቃየት ልቧ በሐዘን ይወጋ ነበር። ቅዱስ አልበርቶ «የጽዮን ልጅ ድንግል ሆይ የሐዘንሽ ጥልቀትና ስፋት እንደ ባሕር ነው” (ሰቆ. ኤር. 2፣13) የሚለውን የሰቆቃው ኤርምያስን ጥቅስ ለእመቤታችን ማርያም ይደግመዋል። እመቤታችን ማርያም ይህ ሁሉ ሐዘን የደርሰባት በእራሷ ላይ በተፈጸመው ስቃይ ሳይሆን በኋላ በልጇ ላይ ስለሚደርሰው መከራ በማሰብ ነበር።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ሰማይ ከመፍለሷ በፊት 7 የሐዘን ወቅቶችን በምድር ላይ አሳልፋለች።
1ኛ “ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት እንዲሆን፣ ደግሞም ክፉ ለሚያስወሩበት ምልክት እንዲሆን ተወስኗል፤ የብዙዎችም የልብ ሐሳብ የተገለጠ እንዲሆን፣ የአንቺም ነፍስ ደግሞ በሰይፍ ይወጋል” የሚለው የስምዖን ትንቢት (ሉቃስ 2፡32-35) የመጀመርያው ሐዘን የፈጠረባት ነገር ነው።
2ኛ ሄሮድስ ልጁን ለመግደል በፈለገበት ወቅት ወደ ግብፅ የተደረገ ሽሽት (ማቴዎስ 2፡13-) ሐዘን ፈጥሮባታል።
3ኛ ኢየሱስ በቤተመቅደስ ወስጥ በጠፋ ጊዜ ለሦስት ቀናት በድካም እና በሐዘን ዮሴፍ እና ማርያም እርሱን በፈለጉበት ጊዜ (ሉቃስ 2፡43-) እጅግ በሐዘን ተሞልተው ነበር።
4ኛ ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ በሚሄድበት ወቅት መውደቁን በተመለከተችበት ወቅት (ሉቃስ 23፡27-) እንደ እናት ሐዘን ገብቷት ነበር።
5ኛ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በተሰቀለበት ወቅት (ዮሐንስ 19፡18-) ልጇን በመስቀል ላይ ሆኖ ስታይ አዝና ነበር።
6ኛ ኢየሱስን ከመቀል ላይ ባወረዱት ጊዜ (ማርቆስ 15፡43-) በእቅፏ ውስጥ አስገብታ በማቀፍ ክፉኛ አዝና ነበር።
7ኛ የኢየሱስ ስርዓተ ቀብር (ዮሐንስ 19፡41-) ባየችበት ወቅት እጅግ አዝና ነበር።
ማርያም በእነዚህ ሰባት የሐዘን ጊዜያት ውስጥ ሕይወቷን አሳልፋ ነበር። በመጨረሻም ለመፍለስ በቅታለች።
ዛሬም ቢሆን የተወደዳቹ ውድ ሀገራችን ኢትዮጲያ እነዚህን የማርያም ሐዘኖች በሚመስሉ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አገራችን አሁን በገጠማት የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት ከተከሰተው እና እየተከሰተ በሚገኘው መከራ እና ስቃይ እንዲያበቃ እና ሀገራችን ኢትዮጲያ በሰላም በፍቅር በአንድነት፣ በእኩልነት፣ በመከባበር የምንኖርባት ሀገር ትሆን ዘንድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት እንማጸናለን።

መልካም የፍልሰታ በዓል ለሁላችን፡
እግዚአብሔር ሕዝባችንን እና አገራችን ኢትዮጲያን ይባርክልን!
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት
ነሐሴ 16 /2015 ዓ.ም

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when St. Atonony Ethiopia catholic church Television network posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share