17/09/2026
በፍሳሽ መውረጃ ቱቦ ወደ መኖሪያ ቤት በመዝለቅ የስርቆት ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት
ተከሳሽ አዲሱ እንደግ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመው ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ካራ ቆሬ አካባቢ ነው።
ተከሳሹ በፍሳሽ መውረጃ ቱቦ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ግቢ ከገባ በኃላ የግል ተበዳይ ቤታቸውን ክፍት አድርገው መኝታ ቤት በነበሩት ሰዓት ሳሎን አስቀምጠውት የነበረውን የዋጋ ግምቱ 40 ሺህ የሚያወጣ ሳምሰንግ ታብሌት ስልክ እና 2500 ብር የሚገመት ጃኬት በአጠቃላይ 42,500 ብር የሚገመት ንብረት ሰርቆ ሊሰወር ሲሞክር የግል ተበዳይ ባሰሙት የድረሱልኝ ጥሪ በፖሊስ አባላትና በህብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፈንጅ መያዙን በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የካራ ቆሬ አካባቢ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ አስፈላጊውን ምርመራ በማጣራት አቃቤ ህግ ክስ እንደመሰረተበትም ፖሊስ ገልጿል።
ተከሳሹ ከዚህ ቀደምም በውንብድና ወንጀል ተከሶ በ2 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፎበት በማረሚያ ቤት ፍርዱን ጨርሶ እንደወጣና ደጋጋሚ ወንጀል ፈፃሚ መሆኑንም የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ያመለክታል።
የተከሳሽ አዲሱ እንደግ ጉዳይን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራንዮ ምድብ ፈጣን ወንጀል ችሎት ጥፋተኝነቱን በሰው ማስረጃዎች ካረጋገጠ በኋላ ተከሳሹን ያስተምራል ሌሎች ወንጀል ፈፃሚዎችን ያስጠነቅቃል ሲል በፈፀመው የስርቆት ወንጀል መስከረም 6 ቀን 2019 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ4 አመት ከ7 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ