14/09/2026
"አፍሪካን የሚያገለግል የኤአይ ቴክኖሎጂ ለማልማት የብሪክስ አገራት ትብብር ወሳኝ ነው"፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
***********************
በህንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ (BRICS) አገራት ጉባኤ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካን በተሻለ ሁኔታ የሚረዳ እና የሚያገለግል የሰው ሰራሽ አስተዋጽኦ (AI) ቴክኖሎጂ ለመገንባት ከብሪክስ አባል አገራት ተቋማት ጋር በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ዘርፉ በሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት የኢትዮጵያ የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲን በመመስረት ዘመናዊ ስራዎችን እያከናወነች እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሥነ-ምግባራዊ እና ሰውን ማዕከል ያደረገ የኤአይ አስተዳደርን እንደሚደግፉ ገልጸው፣ ሆኖም መልካም አስተዳደር ከተግባራዊ አቅም ጋር መጣመር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ህዝባዊ መሰረተ ልማት፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ የክፍያ ስርዓቶች እና የመረጃ ልውውጥ ግንባታ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል።
መረጃዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በህጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችሉ ደንቦችና መመሪያዎች መዘርጋታቸውን ጠቁመው፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ይህንን የዲጂታል ሽግግር የበለጠ እንደሚያፋጥነው ተናግረዋል።
ቀጣዩ የኤአይ ትውልድ ለብዙሃኑ የሰው ልጅ የሚያገለግል መሆን እንዳለበት ያሰመሩበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም በርካታ ቋንቋዎችን መረዳት፣ ወደ ተለያዩ ማህበረሰቦች መድረስ እና ሰፊ የሰው ልጅ እውቀትን መቅሰም እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
አፍሪካም ይህንን ቀጣይ ትውልድ የኤአይ ቴክኖሎጂ በመገንባቱ ሂደት ውስጥ የበኩሏን ድርሻ ማበርከት እንዳለባት ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንን ግብ ለማሳካት ሰፊ ምርምር፣ የኮምፒዩቲንግ አቅም፣ የክህሎት ልማት እና ሂደቱን በበላይነት መምራት የሚችሉ ጠንካራ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብራርተዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ