
27/06/2025
"ክለቡ ጥያቄዬን ከመለሰ በኢትዮጵያ መድን መቀጠል እፈልጋለሁ"
ገብረመድህን ሃይሌ
ከኢትዮጵያ መድን ጋር ታሪካዊ ድል ያስመዘገበው አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ በክለቡ የመቆየት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡ ጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሱ የረዳው አሰልጣኙ ድሎቹን ማበላለጥ እንደሚከብደው ተናግሯል፡፡
‹‹ሁሉም የዋንጫ ድሎች የራሳቸው መልክ አላቸው፡፡ አንዱን መምረጥ ይከብደኛል ፤ ዋንጫ ያነሳሁባቸው ሦስቱም ክለቦች አዲስ ታሪክ በማስመዝገባቸው ኩራት ይሰማኛል፡፡›› ብሏል።
ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ( AMN) ጋር ቆይታ ያደረገው ገብረመድህን ሃይሌ ኢትዮጵያ መድንን በማሰልጠን ቢቀጥል ደስተኛ እንደሆነ ገልጿል።
በክለቡ ለመቀጠል ግን እንዲሟሉ የሚፈልጋቸው ነገሮች እንደሉ ጠቁሟል፡፡ ‹‹በቀጣይ ኢንተርናሽናል ውድድር ላይ እንሳተፋለን፡፡ ክለቡ ይህን ታሳቢ ያደረገ አደረጃጀት ሊከተል ይገባል፡፡›› ብሏል፡፡
‹‹ለክለቡ ሃላፊዎች ምን እንደምፈልግ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ እስካሁን ምላሽ አልሰጡኝም፡፡ በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ነገሮች ከተስተካከሉ እና ቡድኑ ከተደራጀ በመድን እስከመጨረሻ ብቆይ ደስ ይለኛል፡፡›› በማለት ፍላጎቱን አብራርቷል፡፡
በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ያሸነፈው ኢትዮጵያ መድን በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል፡፡