26/07/2026
የባንዲራን ጉዳይ በተመለከተ
በአስር ሰዎች ደረጃ ተከፋፍሎ በተደረገው የንዑስ ቡድን ምክክር ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አለማ ፣ አርማ፣ መዝሙር እንዲሁም የክልሎች መዝሙር ፣ሰንደቅ አላማ እና አርማ ምን ይሁን በሚሉ ነጥቦች ላይ ተመካካሪዎች አማራጭ ሃሳብ አስቀምጠዋል።
ባለፉት ቀናት ፤10 ሰዎች ባሉት ንዑሳን ቡድን ተከፋፍለው ውይይት አድርገው 50 አባላት ላሉት ተመካካሪ ቡድን ቀርበው በቃለ ጉባዔ ፀድቆ ሰኞ ይጀመራል ወደ ተባለው 250 አባላት ወዳሉት ቡድን ከተላላፉ አጀንዳዎች ውስጥ በሀገር ግንባታ ስር የሚገኘው ፣ ሀገራዊ ምልክቶች እና መገለጫዎች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ የሚለው ንዑስ አጀንዳ አንዱ ነው።
ሀገር ግንባታ በሚለው ዋና አጀንዳ ስር ከተዘረዘሩት 7 ንዑሳን አጀንዳዎች ውስጥ የሀገር ባለቤትነት ጉዳይ ፣ታሪክ እና ማንነት ፣የቋንቋ ጉዳዮች ፣ የሀገር ግንባታ እና ብዝሃነት አስተዳደር ፣ሀገራዊ ምልክቶች እና መገለጫዎች እና ሎሎችም ንዑሳን አጀንዳዎች ተዘርዝረዋል ።
ለንዑሳን አጀንዳዎቹ ደግሞ ለእያንዳንዳቸው ከሶስት እስከ ሰባት የሚደርሱ የውይይት መሪ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ለምሳሌ ሀገራዊ ምልክቶች እና መገለጫዎች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ በሚለው ንዑስ አጀንዳ ስር ሶስት የውይይት መሪ ጥያቄዎች ተነስተዋል ።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ማለትም ቀለማቱ እና አርማው፣ብሔራዊ በዓላት እና መዝሙር የሁሉም ማህበረሰቦች ወካይ እንዲሆኑ ምን መለወጥ ያስፈልጋል የሚለው ጥያቄ አንደኛው ነው።
የክልል መዝሙር እና የክልል ሰንደቅ አለማ አስፈላጊ ነው ወይ? የሚሉ ተጨማሪ ሁለት የውይይት መነሻ መሪ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።
በዚህ ንዑስ አጀንዳ ስር በቀረቡ መሪ ጥያቄዎች ላይ 50 አባላት ባሉት ቡድን ደረጃ ተወያይተው ቃለ ጉባዔ ይዘው ማጠናቀቃቸውን የተናገሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ወክለው በምክክሩ ላይ መሳተፋቸውን የተናገሩት አቶ ፈይሰል አብዱላዚዝ፤ የሀገሪቱ ሰንደቅ አለማ አርማ ምን ይሁን? የክልሎች ባንዲራ እና መዝሙርስ ምን መሳይ ይሁን? ለሚለው ሀሳብ በርካታ አማራጭ ሃሳቦች እንደቀረቡ ነግረውናል ።
የሀገሪቱን ሰንደቅ አለማ በተመለከተ አረንጓዴ ፣ቢጫ፣ቀይ ቀለም ያለው የአሁኑ ሰንደቅ አላማ አንዳይነካ ነገር ግን አርማው ይቀየር የሚሉ ሀሳቦች መነሳታቸውን ተናግረዋል ።
የቀረቡ አማራጭ ሀሳቦች ደግሞ አሁን ያለው የኮከብ አርማ አንዲቀር እና አሁን ባለው ሰንደቅ አላማ ላይ ለምሳሌ ልክ አንደ "አሜሪካ ባንዲራ" የሁሉም ብሔረሰብ አርማ ይቀመጥ የሚለው እንደ አንድ ሀሳብ መቅረብ አለበት የሚል መኖሩን አስረድተዋል ።
ከፊሉ ተወያይ ደግሞ የብሔረሰብ አርማ ሳይሆን የሰላም ምልክት የሆነችው "እርግብ" አርማ ትሁን የሚል ሃሳብ አቅርቧል ብለዋል አቶ ፈይሰል።
እርሳቸው በተሳተፉበት ቡድን በዋናነት እንዲሆን የተስማሙት ግን አሁን ያለው ሰንደቅ አላማ ሳይነካ በሀገሪቱ ያሉትን ሁሉንም ክልሎች ሊወክል የሚችል አርማ ይደረግ የሚለው ላይ አንደሆነ ተሳታፊው ዘርዝረዋል ።
የክልል ሰንደቅ አላማን በተመለከተ በአገሪቱ "ከአንድ ሰንደቅ አላማ ውጪ መኖር የለበትም " እና የሁሉም ክልሎች ሰንደቅ አላማ አሁን ያለው አረንጓዴ ፣ቢጫ፣ ቀይ ቀለም ያለው ሆኖ ነገር ግን አርማ የሚወክላቸውን እንዲጠቀሙ በሚለው ላይ ተነጋግረናል ብለዋል።
መዝሙርን በተመለከተ ደግሞ የአሁኑ ይቀጥል የሚለው ላይ ብዙዎች እሳቸው ባሉበት በቡደን ደረጃ መስማማታቸውን ጠቅሰው ክልሎች መዝሙር እንዲኖራቸው ነገር ግን የመዝሙሩ ይዘት ጠብ አጫሪ አንዳይሆን የሚለው ላይ ወይይት አድርገናል ሲሉ ነግረውናል።