
02/10/2023
በኦሮሚያ እና ሶማሊ የክልል ፀጥታ ኃይሎች መካከል በተደረገ ተኩስ ልውውጥ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል ተባለ
መስከረም 21፤ 2015 ዓ.ም.
(አዲስ ዘይቤ፤ አዲስ አበባ) በኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች የፀጥታ አካላት መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ቢያንስ ስድስት ንፁሀን ዜጎች ተገድለዋል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በባቢሌ አቅራቢያ በኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልል የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ የሞቱት ሰዎች በአካባቢው የሚገኝ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የነበሩ ተፈናቃዮች መሆናቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኢሰመኮ በክስተቱ ላይ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “በአሁኑ ወቅት ግጭቱ የቆመ ቢሆንም፤ በተኩስ ልውውጡ ወቅት ቆሎጂ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ቢያንስ ስድስት ተፈናቃዮች ተገድለዋል፣ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል እንዲሁም በሌሎች የአካባቢው ሲቪል ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል” ብሏል።
በአፍሪካ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና እገዛን አስመልክቶ የተደረገው ‘የአፍሪካ ሕብረት ስምምነት’ ወይም ‘ካምፓላ ስምምነት’በሚገልፀው መሠረት የመንግሥት የፀጥታ አካላት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን የመጠለያ ጣቢያዎች ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ተግባራት ሊቆጠቡ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ የግጭቱን መንስዔ በመለየት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲሰጥ፣ የነዋሪዎች እና የተፈናቃዮች ደኅንነት በዘላቂነት እንዲረጋገጥ፣ ተጎጂዎች እንዲካሱ እና ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ባለማድረግ በንፁሀን ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ የፀጥታ ኃይል አባላትም በህግ አግባብ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥቷል።
Ethiopian Human Rights Commission