16/01/2026
የ15ኛው "ፋንታ ሚዲያ ካፕ" ውድድር የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ
ፕራይም ሚዲያ(አዲስ አበባ)_ጥር 08/2018 ዓ.ም
በዮ ስፖርት አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚደረገው እና ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአዝናኙ ሲዝናና የሚዲያ ካፕ ውድድር የምድብ ድልድል ይፋ ተደርጓል።
"ፋንታ ሚዲያ ካፕ" የሚል ስያሜን ይዞ በሚደረገው ውድድር ላይ በአጠቃላይ 29 ቡድኖች በሰባት ምድቦች ይሳተፋሉ።
የውድድሩ ዋና አዘጋጅ አቶ አንዱአለም አስፋው ውድድሩ የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲዝናኑ ከማድረግ ባለፈ በአንድ ቦታ ተገናኝተው የሚተዋወቁበት እና የስራ ልምድ የሚለዋወጡበት ስለመሆኑ ገልጿል።
በመድረኩ የክብር እንግዳ የነበሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ባህሩ ጥላሁን ውድድርን በተከታታይ ለ15 ዓመታት በወጥነት ማዘጋጀት ከባድ መሆኑን በመጥቀስ አዘጋጁን አመስግነዋል።
በምድብ ድልድሉም ሚዲያችን ፕራይም ሚዲያ በምድብ 2 ከሪፖርተር ጋዜጣ ፣ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን እና ከሆፕ ቴሌቪዥን ጋር ተደልድሏል።
በምድብ 1 ፌዴራል ፖሊስ ሚዲያ ፣ላይፍ ኢዝ ጉድ ፣ ዳጉ ስፖርት እና 4-3-3 ስፖርት ፤ በምድብ 3 ፋና ቲቪ ፣ ዲጄዎች ማህበር ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ኢሳት ተደልድለዋል።
በምድብ 4 አርትስ ቲቪ ፣ ኢዜአ ፣ አሃዱ ሬድዮ እና መናኸሪያ ሬድዮ እንዲሁም በምድብ 5 ኢቢሲ ፣ ቲክቶከሮች ፣ ሽርጉድ ኢንተርቴይመንት እና ቻናል ዋን ተመድበዋል።
በምድብ 6 አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ፣ አባይ ቲቪ ፣ ሞዛይክ ስፖርት ፣ ሀገሬ ቲቪ ፣ ንስር ስፖርት በምድብ 7 ደግሞ ኢቢኤስ ፣ ብስራት ኤፍ ኤም ፣ ሳይበርኛ እና አራዳ ኤፍ ኤም ተካተዋል።
ውድድሩ ከጥር 13 ጀምሮ እስከ የካቲት 08 ድረስ 22 አካባቢ በሚገኘው የፉትሳል ሜዳ ላይ የሚካሄድ ይሆናል።
ሻምፒዮን የሚሆነው ቡድን የ200 ሺህ ብር እና ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን 2ኛ 100 ሺህ ብር 3ኛ ደግሞ 50 ሺህ ብር ይሸለማሉ።
በአጠቃላይ ለውድድሩ ከ600 ሺህ ብር በላይ ለሽልማት መዘጋጀቱም በመድረኩ ተገልጿል።
ሀብታሙ ምትኩ