GrandMom The Promise Land

GrandMom The Promise Land +++ትምህርተ ሃይማኖት ከዓለም ማዕዘናት ወቅታዊ ጉዳዮች+++ For Orthodox

17/11/2025

ወንድ የሆነ ይምጣ
እኔ ከፊት ሆኜ እመራለሁ !!
#አቡነ አብርሀም

መድሎተ ጽድቅ ፫ ደራሲ: መምህር ያረጋል አበጋዝዘውግ : ሥነ መለኮትየመ/ር ያረጋል አበጋዝን (ከዚህ በኋላ መዓርጉን ሳልጠቅስ ስሙን ብጠራ የውዴታ እንጂ ክብሩን የመቀነስ ተደርጐ አይወሰድብኝ...
13/11/2025

መድሎተ ጽድቅ ፫
ደራሲ: መምህር ያረጋል አበጋዝ
ዘውግ : ሥነ መለኮት

የመ/ር ያረጋል አበጋዝን (ከዚህ በኋላ መዓርጉን ሳልጠቅስ ስሙን ብጠራ የውዴታ እንጂ ክብሩን የመቀነስ ተደርጐ አይወሰድብኝ!) ሦስቱንም ቅጾች አንብቤያቸዋለሁ፡፡ ቅጽ ፩ዱን በተለያየ ጊዜ በልዩ ልዩ አጋጣሚ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ቅጽ ፪ን አንድ ጠበቃና የሕግ አማካሪ የሆነ የደሴ የፌስቡክ ጓዴ ቀድሞ አንብቦ አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳሳ ቢተገትገኝ በመቀደሜ አፍሬ አነበብኩት፡፡ በቁጭት ዘለቅሁት፡፡ ቅጽ ፫ቱ ከእኔው ‹‹ጽንዐ ተዋሕዶ›› ጋር በተቀራራቢ ጊዜ ወጥቶ ስለነበረ ከሰነበተብኝ ‹የኅትመቱ እንዴት ይከናወን ይሆን› የሩቅ ሐሳብ መውጫ እንዲሆነኝ ጀመርኩት፡፡ ሳበኝ! ወደዘመኔ ሳበኝ! በተለይ እስከ ገጽ 206 የሚነሡት ጭብጦች አሁናዊ (ዘመናውያኑ contemporary የሚሏቸው) የክርስትና ፈተናዎች በመሆናቸው መሰጠኝ፡፡ ማስታወሻዬን ይዤ ወጣሁት፡፡ ስጨርስ ስለ ለሦስት ነገር መናገር ሻተኝ፡፡ እነዚህም፡- ቢሆን ቢጨመር ኖሮ መልካሙን መጽሐፍ እጅግ በጣም ሸጋ፣ እንደው ‹‹በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት›› የሚባለው ዓይነት ዓመት በዓል ያደርገው ነበር ያልኳቸውን ሐሳቦች (ማሳዛኔ! ‹‹ኂስ›› ላለማለት መሽከርከሬ!)፣ የመጽሐፉ ጥቅል በረከት፣ ያረጋል አበጋዝ ምላሽ የሰጠባቸው የተመረጡ ጭብጦች የሚሉ ናቸው፡፡ እንሂድባቸው፡፡
---

ሀ . የመጽሐፉ በረከት
---

ይህ መጽሐፍ የሚሞግተውን ሐሳብ የፍልስፍና መነሻ በመቆፈር ስለሚነሳ በቅርንጫፍ ከመንጠላጠል ያድነናል፡፡ ለተጨማሪና ዘርፈ ብዙ ንባብ ይጋብዛል፡፡ በአቀራረብ ጥልቀቱ ከሃይማኖት ክበብ ውጪ ያለ ልበ ሰፊ ሰውም ሊያነበው የሚችል ጭብጥና አቀራረብ አለው፡፡ ‹‹የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አስተምህሮ /እምነትና ሥርዓት/ እንዲህ ነው!›› ብሎ ደንግጎ ለመነሣት የሚፈልግ የሌላ እምነት ወይም ዓለማዊ ጸሐፊ ሊያጣቅሳቸው ከሚገቡ መጻሕፍት ውስጥ የያረጋል አበጋዝ መድሎተ ጽድቅ ተከታታይ መጻሕፍት አስፈላጊ እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ እንደ ተለመደው ያረጋል የያዘውን ርእስ ያደማል፣ አቀራረቡ ኦሪጅናል ነው፣ ለወደፊት ጸሐፍት መነሻና ማጣቀሻ መሆን ይችላል፣ ክርክራዊ አቀራረቡ ፍሰት አለው፡፡ ቃል ይተረጕማል፣ ያራቅቃል፡፡ ዐውድ ይጠብቃል፤ ከጭብጥ አይወጣም፡፡ ለማስረጃዎች ተገቢነት ትኩረት ይሰጣል፤ ማለትም ጥቅስና የታሪክ ማስረጃ ሲያቀርብ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነና አስፈላገነት ያለውን ነው፡፡ ያረጋል አበጋዝ አያመቻምችም! በዓለም ላይ የሚዋልሉ አሁናዊ ሐሳቦችን ለአንባቢ ውሳኔ ክፍት አድርጎ በምንታዌ አይተዋቸውም፡፡ አዙሮ አሽከርክሮ ኦርቶዶክሳዊውን እይታ ግን እንዲህ ነው ይለናል እንጂ፡፡ የያረጋል ቸርነት ለግል ውሳኔ መንገድ በመክፈት ሳይሆን በመጽሐፉ ዋጋ ነው የሚገኝ፡፡ ከይዘቱ፣ ከማጣቀሻው ብዛት፣ ከወሰደው ጊዜ፣ ከኅትመቱ ጥራት፣ ከመጻሕፍቱ ተፈላጊነት፣ ከጸሐፊው ልፋትና ማንነት (ፕሮፋይል) አንጻር በቤተ ክርስቲያን ጸሐፍት ከሚጻፉ መጻሕፍት ውስጥ በርካሽ እያነበብን ያለነው ያረጋል አበጋዝን ይመስለኛል፡፡ በዚህ በኩል በአንባብያን ስም ‹‹ስለ በጎነትህ እግዚአብሔር ይስጥልን!›› ማለት እፈልጋለሁ፡፡
---
ለ . ያረጋል አበጋዝ ምላሽ የሰጠባቸው የተመረጡ ጭብጦች
---
1. ‹‹ ››፡- ያረጋል አበጋዝ አጥብቆ የሚሞግተው አነጋገር ‹‹ወደ ቃሉ መመለስ›› የሚለውን የተሐድሶዎች ሐሳብ ነው፡፡ የሐሳቡ መዳረሻ ወደ ቃሉ መመለስ ሳይሆን ‹‹ወደ እኛ አረዳድ፣ ወደ ፕሮቴስታንታዊ ትርጓሜ መመለስ›› ማለት ነው ይላል - ለዚያውም በሺህ ከሚቆጠሩ ቅርንጫፎቻቸ ወደ የትኛው ‹‹ተመለሱ›› እንደሚሉ እንኳ ግልጽ እንዳልሆነ ደጋግሞ ይሞግታል፡፡ ይህን ጭብጥ በመድሎተ ጽድቅ ፩ና ፪ ያስነበበን ሲሆን በዚህኛውም ቅጽ (ገጽ 21-23) ያነሳሳዋል፡፡ ለውጥን በሚመለከትም ለውጥ ሁሉ በጎ ነው ከሚል መነሻ መንጎድ ያለበትን ድክመትና በቤ/ክ ሊለወጥ የሚችለውን ሊለወጥ ከማይችለው አለመለየትን እያነሳሳ በተሐድሶዎች የሚቀነቀነው ‹‹ለውጥ›› ማባሪያ የሌለው መበጣጠስ መሆኑን ያለፉትን የ500 ዓመታት ተሞክሮዎች እያነሳ ይሞግታል (ገ.281-311)፡፡
2. ፡- ያረጋል አበጋዝ ሁለት የሃይማኖት ብይኖችን ይተቻል፡፡ አንደኛው ‹‹ሁሉም ሃይማኖት ትክክል ነው›› የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ‹‹ሌሎች ሃይማኖትም እውነት አላቸው›› የሚል ነው፡፡ ሁለቱንም ይነቅፋል (ገ.31-33)፡፡ ርቱዕና መጽሐፋዊ አካሄድ የሚለው ‹‹ትክክለኛ ሃይማኖት አንዲት ብቻ ናት›› የሚለውን ነው፡፡ እንዲህ ማለት የሌሎችን እምነት መጋፋት ማለት አይደለም፤ ሁሉም የማመን መብት እንዳለው እንደዚህ ብሎ ማመንም መብት ነው፤ ይህን መቃወም በራሱም ፀረ ብዝኃነት ነው፤ ሌሎችን ከማስገደድ ጋር አይያያዝም፡፡ ሌላውን በሰውነቱ ከማክበርም አይከለክልም ይለናል፡፡ ‹‹የሌሎችን የእምነት በጻነት ለማክበር የራሳችንን እውነት መጣል የግድ አይደለም፡፡››(ገ.34)፡፡ ጌታም ‹‹… አውነትን በፍቅር እየያዝን … እንደግ›› አለን እንጂ ‹‹እውነትን ጥለን እንፋቀር አላለንም›› - የያረጋል ማሰሪያ ነው (ገ.92)፡፡ ሁሉም ሃይማኖት ትክክል ነው፤ ዋናው እምነት ነው የሚል አካሄድ ባራኪ አምላክን ፍለጋ ነው ይላል ያረጋል (ገ.35)፡፡ አያይዞም አካሄዱ ‹ፍጹም አውነት የለም፤ እውነት አንጻራዊት ናት› ከሚለው ድኅረ ዘመናዊነት (post modernism) ጋር የተገናኘ መሆኑን በመጥቀስ ‹‹እውነት አንጻራዊት ናት›› ከተባለ ይህ ዐረፍተ ነገር በራሱም ፍጹም አይደለም፤ ምክንያቱም አውነት አንጻራዊት ናት (እውነትን እኔ በሴት ጾታ አደረግኋት እንጂ ያረጋል በወንድ አንቀጽ ነው የሚጠራት) ተብሏል ሲል ይሞግታል (ገ.37)፡፡ ያረጋል አያመቻምችም!
3. ፡- እነዚህን ቃላት ይዘት ተኮር ትርጓሜ ይሰጥባቸዋል፡፡ ሃይማኖት የምንለው ይዘቱን፣ ምንነቱን፣ አጠቃላይ መለያየውን (ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለይበትን አስተምህሮ)፣ ሚዛኑን፣ ቁጥር ተሰጥቶት ‹‹አሐዱ/ አሐቲ/›› ሊባል የሚችል መሆኑን ከገጽ 39 እስከ 104 እየደጋገመ ያሳስበናል፡፡ በእነዚሁ ገጾች ውስጥ እምነትን፡- ውስጣዊና ግላዊ መታመን፣ በደረጃ ከሰው ሰው የሚለያይ እያለ ማሳያ ጥቅሶችን በርከት አድርጎ ያቀርባል፡፡ ብዙ ጊዜ በተሐድሶዎች የሚቀርበውን ‹‹ሃይማኖት በዛ እንጂ እምነት አንዲት ናት›› የሚል ማለዘቢያ ቃል ይገለብጠውና ‹‹ሃይማኖት አንዲት ናት፣ እንደየአማኙ ብርታትና ድክመት የሚለያይ እምነት ነው›› ወደማለት ይወስደናል፡፡ በአንዲት ሃይማኖት ውስጥ እንደየብርታታችን የተለያየ የትንካሬ ደረጃ ያለው እምነት ሊኖረን ይችላል፡፡ ይህ እይታ ‹‹እምነት እንጂ ሃይማኖት አያድንም›› የሚለውን ሃይማኖትን አስተሐቃሪ (ፀረ ዲኖሚኔሽን) መፈክር አጥብቆ ይወድራል፡፡ ጉዳዩ በመድሎተ ጽድቅ ቅጽ ፪ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ››ን በሚነቅፈው ርእስ ስር ቤተ ክርስቲያን በነገረ ድኅነት ያላትን ቦታ በስፋት ከተተነተነበት ነጥብ ጋር እየተገናኘ ቢነበብ ሸጋ ነው፡፡ ነገረ ድኅነትን ከነገረ ቤተ ክርስቲያን በማሰናሰል በኩል ያረጋል ብርቱ ነው፡፡
4. ፡- በሃይማኖት ጉዳይ የትክክል መሆንና አለመሆን ሲነሳ ‹‹ኧረ’ኔ በማንም አልፈርድም!›› የሚለውን ቸልተኛ አባባል ሲገሥጽ አትፍረድ ለምግባር እንጂ ለእምነት አይደለም ይለናል (ገ.98-104)፡፡ ‹‹በሃይማኖት ውስጥ ያለውን እውነት መናገር ማለት ራሱ ጌታ የተናገረውን መመስከር እንጂ በማንም ላይ ፍርድ መፍረድ አይደለም›› (ገ.99) - የያረጋል ቃል ነው፡፡ ይሄ ፍርድ አይደለም ምስክርነት ነው ይለናል (ገ.100)፡፡ ‹‹የሁሉም የሆነ የማንም አይደለም›› የሚለውን የፈረንጅ ብሂል በሚያዘክር መልኩ ሁሉም ሃይማኖት ትክክል ነው ማለት አንዱም ትክክል አይደለም ማለት ነው ይለናል (ገ.102)፡፡
5. ፡- ከገጽ 105 እስከ ገጽ 206 የተተነተነው ይህ ሐሳብ እጅጉን መሳጩና (ካለንበት ውዥንብር አንጻር) ወቅታዊው የመጽሐፉ ክፍል ሆኖብኛል፡፡ የኢትዮጵያን በቁሳዊ እድገት ወደ ኋላ መቅረት ሃይማኖታዊ ተሐድሶ ካለማድረግ ጋር ማገናኘትን፣ ቁሳዊ ስኬትንና ብልጽግናን የጽድቅና የአስተምህሮ ርቱዕነት ለማድረግ መሞከርን፣ የአሜሪካንና የደቡብ ኮርያን ኢኮኖሚያዊ ስኬት አምላካዊ ቡራኬ አድርጎ ማቅረብን ‹‹የልብ አድርስ›› በሆነ የፍሬ ነገር ትንተና፣ አመክንዮና ማስረጃ ይሞግታል፡፡ ሙያውም ለጉዳዩ ቅርበት ያለው መሆኑ ትንተናውን ምሉዕና የሥልጣን (authoritative) እንዳደረገው ይስሰማኛል፡፡ የያረጋል ወርቃማ ብርዕ እንዲህ ትላለች፡- ‹‹ … የክርስቲያን ዋና ዓላማ የእግዚአብሔርን መንግሥቱንና ጽድቁን መፈለግ እንጂ ምድራዊ የሆነውን ብልጽግናና ቁሳዊ ሀብትን መሻት አይደለም፤ ምክንያቱም እነዚህኞቹ እስከ ሠራን ድረስ ለሚያምኑት ብቻ ሳይሆን ለማያምኑትም እንኳ የሚሰጡ ተራ ነገሮች ናቸውና፡፡ በዚህ ዓለም ያሉ ነገሮች የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን የሚሰጡን የሃይማኖት ዋጋዎች ሳይሆኑ ለሚሠራ ሁሉ ሊገኙ የሚችሉ ናቸው፤ ሰው በመሆናችን የሚሰጡ ናቸው›› (ገ.112)፡፡ እንዲያ ማለት ግን ብልጽግና ርኵሰት ነው ማለት አይደለም፡፡ ‹‹የኢኮኖሚ ብልጽግና እና ምድራዊ ሥልጣኔ የክርስትና ሃይማኖት ዋና ግቦች አይደሉም እንጂ፣ ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ጠንካራ ሥራ መሥራት የለባቸውም ማለት ግን አይደለም፡፡›› (ገ.134)
6.‹‹ ‹‹ና_የኢኮኖሚ_እድገት_የምክንያትና_ውጤት_ግንኙነት_አላቸውን? ጥያቄውን አሳጥሬ ያቀረብኩት እኔ ነኝ - ከገጽ 135 እስከ 160 ለሚደረደሩት የያረጋል የክርክር ነጥቦች ማንሻ እንዲመቸኝ፡፡ ‹‹የፕሮቴስታንት የሥራ ባህል ሥነ ምግባር /Protestant Work Ethic›› የሚለው የማክስ ዌበር ብሂል በምዕራቡ ዓለም የማኅበረ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተንሰራፋ ነው፡፡ በየመማሪያ መጻሕፍቱ ነባራዊ ሀቅ የሆነ ያህል ይደጋገማል፡፡ ለጉዳዩ የቀረበ ሙያና ንባብ ያለው ያረጋል ይህን የተዘረጋ ሐሳብ እንዲህ ሲል እየጠቀለለ ያነሳዋል፡- (1) ከነባራዊ ሀቅ አንጻር በዚያ ዘመንም በጀርመን ሀገር ካቶሊክ የሚበዛባት ባቫሪያን የተባለች ግዛት ፕሮቴስታንታውያን ከሚበዙባቸው ግዛቶች ይልቅ እጅግ ሀብታሟ ግዛት ነበረች /ገ.136/፣ (2) የቅኝ ግዛት ዘረፋና ተቋማዊ ለውጦች የእድገቱ መሠረቶች ነበሩ /137/፣ (3)የካፒታሊዝም ዋና ዋና መደቦች የሆኑት ታላላቅ የመሬት ከበርቴዎች፣ ነጋዴዎችና ባንከሮች በዘመኑ እድገት ላይ ነበሩ፤ በኢኮኖሚው ላይ የአይሁዳውያን ሡታፌም አይሏል /ገ.138/፣ (4) ፈጠራዎች ጎልብተው ነበር፤ በተለይም ከ‹‹ጥቁር ሞት›› በኋላ የሰው ኃይል እጥረት መፈጠሩ ፈጠራንና ቴክኖሎጂን አበረታተዋል /ገ.139፣ ገ.142/፡፡ እነዚህ ሁሉ ምንጫቸውና መነሻቸው ከተሐድሶ በፊት ነበር፡፡ (5) አያሌ ጸሐፍት ይህን የዌበር ሐሳብ ሞግተዋል /ገ.143-47/፣ (6)በጂኦፖለቲካ ፍላጎትና በውስጥ አስተዳደር ዲሲፕሊን የመጣውን የደቡብ ኮርያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከአጎራባቾች ጃፓንና ቻይና ፈጣን እድገት እንኳ ሳያነጻጽሩ ለፕሮቴስታንታዊ ሥነ ምግባር በ‹‹በአንበሳ ድርሻ››ነት መስጠት አያስኬድም፣ (7) አጠቃላይ ታሪካዊ እይታው ‹‹ውኃን በሜትር ወይንም ጨርቅን በሊትር›› የሚለካ አውሮፓዊ የሥዕለ ሕሊና መር (euro-centric) የታሪክ አረዳድ ነው - ይላል ባለመገሥጽ ብርዑ ትሑቱ ወንድማችን ቁሳዊ እድገትን ከፕሮቴስታንታዊነት የሚያስተሳስረውን ተሐድሶአዊ ምኞት ሲመክት፡፡
7. ፡- ወደ ዝግመታዊ ለውጥ አውሮፓዊ ሥዕለ ሕሊና የሚያደላው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ (ገ.165)፣ የ‹‹ሳይማር ያስተማረን›› አባትን ናቂ ራስን አድናቂ የ‹‹ምሩቁ›› ኢትዮጵያዊ መፈክር (ገ.183)፣ መጽልመ ደብተራው አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ከሕወኃት እስከ ኢህአፓ ያሉ የ‹‹ያ ትውልድ›› አባላት ከገጽ 195 እስከ 206 በመድሎት እየተመዘኑ ይወቀሳሉ፡፡
8. ‹‹ #ሴኩላሪዝም››_በአውሮፓና_አሜሪካ፡- ያረጋል ወቅትንና የፍልስፍና የመደብ ጀርባን በጥልቀት ተረድቶ ትንታኔ ከሰጠባቸው ርእሶች አንዱ ይሄ ነው፡፡ በቅርቡ ወንድማችን ዳንኤል ክብረት ስለ መንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት ሲናገር የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት በአሉታ ከሚመለከተው አውሮፓዊ እይታ ይልቅ ግንኙነቱን በአዎንታ የያዘው የአሜሪካ አካሄድ የተሻለ ነው የሚል ድምጸት ያለው ንግግር ሲናገር ሰምቼ አነበብታለሁ ብዬ ነበር፡፡ የያረጋል መድሎተ ጽደቅ ቅጽ ፫ አንዱ ንባቤ ሆነ ማለት ነው፡፡ ሆኖም የያረጋል ምንጮች የዳንኤል ክብረትን ሐሳብ ስለመደገፋቸው እጠራጠራለሁ፡፡ ያረጋል በማስረጃ ተደግፎ ይናገራል፡-
‹‹በአሜሪካ ቸርቾች ብዙ ሰው ለሚያይ ሰው አሜሪካ ከምዕራብ አውሮፓ በተሻለ በሴኩላሪዝም ያልተጠቃችና ክርስትና በደኅና ሁኔታ ያለባት አገር ልትመስለው ትችል ይሆናል፡፡ ልዩነቱ ግን በአውሮፓ በእግዚአብሔር አናምንም የሚሉ ሰዎች ቸርች አይሄዱም፤ በአሜሪካ ግን ብዙ ኤቴስቶች /በሀልዎተ እግዚአብሔር የማያምኑ ሰዎች/ ቸርች ይሄዳሉ፡፡ ለምን? ምክንያቱም የአሜሪካ ቸርቾች ራሳቸው ሴኩላር ስለሆኑ ነው፡፡ … ‹የአሜሪካ ቸርቾች ውስጣዊ ሴኩላራይዜሽን - internal secularization የተፈጸመባቸው ናቸው፡፡ አውሮፓ ሕዝቡ ከቸርቾቹ እየወጣ በመሄዱ ሴኩላር የሆነ ሲሆን የአሜሪካ ቸርቾች ግን ራሳቸው ሴኩላር በመሆናቸው አባላቶቻቸውን በውስጣቸው ለመያዝ ችለዋል፡፡›› (ገ.127)፡፡
ባጭሩ፡- በአውሮፓ ዓለማዊውና መንፈሳዊው ሕይወት በመስመር ተለይቶ ዓለማዊው እየበረከተ ቢሄድም በመንፈሳዊው ዓለም ያሉት እነዚያው ጥቂቶቹ ከአሜሪካ በተሻለ መንፈሳዊ ለዛና መጽሐፋዊ ስብከት ሲካሄድባቸው የአሜሪካውያኑ ግን ዓለማውያኑን ለመሳብ ሲባል ቸርቿን ዓለማዊት ያደረገ የሳይኮሎጂ፣ የቢስነስ ካውንስሊንግ፣ የስሜታዊነትና የምድራዊ ሕይወት ግልባጮች ሆነዋል፡፡ ዓለማውያንን ለመሳብ ሲባል የተጀመረው ‹‹ልምምድ›› መጨረሻው ዓለማዊት ቸርች መፍጠር ሆነ፡፡ ይህቺ ‹‹ልምምድ›› የምትል ቃል የፕሮቴስታንታውያን ወርቃማ ቃል ስትሆን ሰሞኑን ደግሞ በመሪዎቻችን በኩል ፖለቲካዊ ‹‹ጃርገን›› ሆና በጆሯችን ተሹማለች፡፡ በነገራችን ላይ የያረጋልን መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ የብልጽግና ፓርቲ መሪ የሆኑትን የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹መደመር›› መጽሐፍ ማንበብ ግድ ብሎኝ ነበር፡፡ እንደፈራሁት በ‹‹ቁሳዊነት›› የታጨቀ አይደለም፡፡ ለሀገራችን ጸሐፍት ቀላል በሆነው ደባትርን የማስተሐቅር ተግባርም አላገኘኋቸውም፡፡ ያዝልቅላቸው!

ሐ . ቢሆን ኖሮ
---
(1) በምንጭ ረገድ በተጠቀማቸው ያልኳቸው ሁለት ምንጮች አሉ፡፡ መጀመሪያ ብሔራውያን ምንጮች ከዚህም በላይ ቢጠቀሱ መልካም ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- የፕሮቴስታንት የሥራ ትጋት ለሚለው መላምት የገዳማውያንን በሥራ ክፍፍል የተጋዘ ጥብቅ የሥራ ዲሲፒሊን እንደ መመከቻ መጠቀም ይቻል ነበር፡፡ በ‹‹ሶላ››ዎች - በተለይ ቅጽ ፪ ላይ - የሉተራን ተቺ እየሆነ የመጣውን The New Perspective on Paul /ጳውሎስን በአዲስ ንጻሬ/ በሚል የሚታወቅ እንቅስቃሴ መሰል አቀራረብ የተከተሉ ሥራዎችን ምነው ባያቸው አሰኝቶኛል፡፡
(2) መድሎተ ጽድቅ በሚል የወጡት ሦስት መጻሕፍት በቁጥር ብቻ ከሚለዩ በዐቢይ ርእስ ስር ንዑስ ርእስ ቢጨመር የበለጠ ገላጭ ይሆናል፡፡ ቅጽ ፩ ‹‹ነገረ ድኅነትና ምሥጢራት ላይ የተነሡ ጥቄዎች ሲፈተሹ››፣ ቅጽ ፪ ‹‹አምስቱ የሉተር ሶላዎች /ብቻዎች/ በመጽሐፍ ሚዛን››፣ ቅጽ ፫ ‹‹የተሐድሶዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ሐተታዎች ሲመዘኑ›› በሚል ወይም ተቀራራቢ ሐረግ ንዑስ ርእስ ቢወጣላቸው ብያለሁ፡፡
(3) መጽሐፉ ከሚያነሣው ጭብጥና ከማጣቀሻው አንጻር ከማዕከላዊነት በላይ ላሉ ዘመናውያን አንባብያንን የሚደርስ ሆኖ ይታያል፡፡ የአብነት ቤቶቹ አበው ዘመናውያን ሐሳቦች ጋር እንዲተዋወቁ፣ በንባብ ያልጎለመሱ አንባቢዎችም የሚያነሳቸውን ሐሳቦች ተረድተው እንዲከተሉት አንዳንድ ጽንሰ ሐሳቦችን በዋናው መስመር ወይም በኅዳግ ማስታወሻ ቢያብራራ የሚያሰኙ ነጥቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ፣ ኢኩሜኒዝም፣ ሴኩላሪዝም፣ የፕሮቴስታንት የሥራ ሥነ ምግባር፣ የእውነትና የባህል አንጻራዊነት… ወደ ቲዎሪ ያደጉ ሐሳቦች በመሆናቸው ጽንሰ ሐሳባዊ ይዘታቸው አስቀድሞ እየተበየነ ሐተታው ቢቀጥል ለፍሰቱም ለቀጣይ የንባብ አነሳሽነትም ያግዝ ይመስለኛል፡፡
(4) በቃልና ጽንሰ ሐሳብ ብያኔ በኩል የሃይማኖት ትርጓሜ (ገ.39) የግእዙን አረዳድና ሶርያዊ መነሻውን መሠረት ቢያደርግ መልካም ነበር፤ ሃይማኖት ሶርያዊ ምንጭ ያለው የግእዝ ቃል ሲሆን ዋነኛ ትርጓሜውም እምነት (faith) ማለት መሆኑን የፊለክሲኖስ ዘማንቡግ ሥራዎችም ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካም ይጠቁማሉና፡፡
(5) የአውሮፓን አመለካከት በባህል አንጻራዊነት (cultural relativism) የሚመራ የሚያስመስለው ንባብ (ገ.167) ትክክል አይመስልም፤ የእነርሱ መርህ ዓለም አቀፋዊነት (universalism) ይመስለኛል፡፡ የአውሮፓ የባህል ብይንና የእውነት ብይን የተለያየ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ከእውነት አንጻር እውነት አንጻራዊት ናት ወደማለት ያደላሉ፤ ከባህል አንጻር ግን የራሳቸውን አስተሳሰብ ‹‹ዓለም አቀፍ›› ብለው ይጠራሉ፣ የባህል አንጻራዊነትን የሚሰብኩ አፍሪካውያን፣ ኤስያና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ይመስሉኛልና ዳግም ቢታይ፡፡
(6) የኅዳግ ማስታወሻዎች ከቁጥር 160 እስከ 164 እንዳሉ ጥቆማ ይሰጥና ይታለፋሉ (ገ.118)፤ ከታች ስንወርድ አናገኛቸውም፡፡ ችግሩ በእኔ እጅ ባለው ቅጅ ብቻ ካልሆነ ቢታረም፡፡
(7) የብልጽግና ወንጌልን ሰባኪዎችን ከ‹‹ሜይን ስትሪም ፕሮቴስታንት›› መለየት (ጸጋ ዘአብ በቀለ ብልጽግናዎችን እየወቀሰ መልሶ ያላደግነው በኦርቶዶክስ ችግር ነው እያለ ራሱን ቢቃረንም) ለይቶ ማየት ይገባ ነበር፡፡ የብልጽግና ወንጌልን የሚቃወሙ በርካታ ፕሮቴስታንታውያን መኖራቸውን አስታውሶ በዚያው ልክ ይህ አካሄድ ባገራችንም ያደረሰውን ጅምር ምስቅልቅል መጥቀስ ይቻል ነበር - ወቀሳው ጥቅል (hasty generalization) እንዳይሆን፡፡
(8) በተከታታይ በቀረቡት የመድሎተ ጽድቅ ቅጾች በአቀራረባቸው የሙግት መልክም ስላላቸው በተሐድሶዎች በኩል በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ የክርክር ጸያፎችን /fallacies/ ከማሳያ ሐረጋት ጋር በዚህኛው ቅጽ ጠቅልሎ በሠንጠረዥ ማቅረብ ቢቻል ብዬ ተመኝቻለሁ፡፡
(9) ስለ ማርቲን ሉተር ሰብእና ለመናገር የዋለው ገጽ የበዛ ሆኖ ታይቶኛል፤ ክርክሩን ሳይሆን ተከራካሪውን ማጥቃት በሚል የሙግት ህፀፅ (fallacy of Ad Hominem) እንዳያሳማ እንደ መስጋት ብያለሁ፡፡ የሰውዬውን የምግባር ድኩምነት ደጋግሜ ሳላነብ አልቀርምና እንደ መታከት ብሎኝም ይሆናል፡፡
(10) ስለ ‹‹ሴኩላሪዝም›› አውሮፓዊና አሜሪካዊ ገጽታ በቀረቡት ነጥቦች ላይ መንግሥትና ሃይማኖት ሊኖራቸው የሚችል ግንኙነት በዐይነ ኦርቶዶክስ ምን መምሰል አለበት የምትል አመላካች መውጫ መንገድ ብትኖር ሸጋ ነበር ብያለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ‹‹ቢሆን ኖሮ›› ይህም ቢታከል መጽሐፉ የበለጠ መልካም ይሆን ነበር ለማለት ነው፤ ሆኖም አለመሆኑ የመጽሐፉን ልዕልና አያጎድለውም፤ እንዲህ ማለቴ ፍጽምና ከመሻት ነው፡፡
---

#ሲጠቃለል፡- ኦርቶደክሳዊ አስተሳሰቦችን በአንጻረ ፕሮቴስታንት ለመፈተሸ የፈለገ ሁሉ የያረጋል መጻሕፍትን ቢያነብ መንገዱ ይቃናል፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ወጣትማ ግዴታው ነው! ያረጋል አበጋዝ ኦርቶዶክሳዊ ሕይወትን በመጽሐፍም በገቢርም ከሚሰብኩ ወንድሞቻችን አንዱ ነው! ይጻፍ፤ እናነባለን! ያኑርልን ወንድማለም!

Reviewer : በአማን ነጸረ is a Lawyer, Deacon, Author and a Social Critic

“እርሱ ደሙን አፍስሶልናል ስለዚህ ሌላ ደም መፍሰስ የለበትም!” 💠💠☦️አቡነ ናትናኤል ☦️💠💠"በክርስትናችን በሃይማኖታችን መገደላችን የሚቆመው መቼ ነው? ነፃነት እንፈልጋለን:: የሰው ልጆች...
06/11/2025

“እርሱ ደሙን አፍስሶልናል ስለዚህ ሌላ ደም መፍሰስ የለበትም!”
💠💠☦️አቡነ ናትናኤል ☦️💠💠
"በክርስትናችን በሃይማኖታችን መገደላችን የሚቆመው መቼ ነው? ነፃነት እንፈልጋለን:: የሰው ልጆች ደም በከንቱ መፍሰስ መቆም አለበት:: ይኼ ፖለቲካ አይደለም:: ሰላም መሻት ፣ ዕረፍት መፈለግ ፣ አንሙት ማለት ፖለቲካ ሳይሆን ሰብአዊ መብት ነው:: ሰው መሆን ነው:: ደከመን:: ብዙ ጊዜ ሰማን:: እናንተም በእኛ ፈረዳችሁብን:: እናንተም ወቀሳችሁን:: እውነት አላችሁ::
ግን ለማን ነው የምንነግረው ይኼንን? ማን ነው የሚሰማን ይኼንን? ማን ነው የሚያቆመው ይኼንን?

ተለማመድነው እኮ:: ስንቶቻችን ስናልቅ ነው የሚቆመው? ይብቃ:: ሕዝባችን ዕረፍት ይፈልጋል:: ሞት ሰለቸን በቃን:: ደም መፍሰስ ሰለቸን:: ይበቃናል:: ምድሪቷ ዕረፍት ያስፈልጋታል:: ሕዝቡ ዕረፍት ያስፈልገዋል:: ስለ እኛ ደም ፈሰሰ እኮ:: በእርሱ ቁስል ተፈወስን እኮ:: ሌላ ደም አያስፈልግም:: መከራችን እንዲያበቃ ጸልዩ"

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ከጥቅምት 11 -  17 ቀን 2018 ዓ.ም  ያካሄደውን ውይይት አጠናቋል። ቅዱስ ሲኖዶሱ  በቤተ ክርስቲያን፣ መንሳፈ...
27/10/2025

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ከጥቅምት 11 - 17 ቀን 2018 ዓ.ም ያካሄደውን ውይይት አጠናቋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በቤተ ክርስቲያን፣ መንሳፈዊ አስተዳደርንና ማኅበራዊ ጉዳዮችን መሠረት ባደረጉ አጀንዳዎች ላይ በአንድነት በመወያየት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገሪቱ ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት በግንቦት 2017 ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሠየመው የሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ የደረሰበትንም ውጤት ለግንቦት 2018 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤው እንዲያቀርብ ተውስኗል።

በተጨማሪም በትግራይ አህጉረ ስብከት የቅድስት ቤተ ክርስቲያኒቱ የሰላም፣ የአንድነት እና የይቅርታ በር ክፍት መሆኑን በመግለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ በክልሉ ለሚገኙት አባቶች፣ ካህናትና ምእመናን ያልተቋረጠ የሰላም ጥሪውን አስተላልፏል።

ቅዱስ ሲኖዶስ አባት እንዲመደብላቸው ጥያቄ ባቀረቡ አህጉረ ስብከቶች ዙሪያ የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርቡ ብፁዓን አባቶችን በመሰየምና ተገቢውን ውይይት በማድረግ ውሳኔ ማስተላለፉንም በመግለጫው ይፋ አድርጓል።

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአረርቲ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በደረሰው አደጋ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማሳከምና የተጎጂ ቤተሰቦችን ለመርዳት የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በቤተ ክርስቲያን፣ መንሳፈዊ አስተዳደርንና ማኅበራዊ ጉዳዮችን መሠረት ባደረጉ አጀንዳዎች ላይ በአንድነት በመወያየት ውሳኔዎች ማሳለፉን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

💒 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ☸️  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ 4ኛ ፓትርያርክ ኾነው የተሾሙት፣ ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም. ሲኾን፣ በፖሊቲካዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን ለቀው ከ...
24/10/2025

💒 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ☸️

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ 4ኛ ፓትርያርክ ኾነው የተሾሙት፣ ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም. ሲኾን፣ በፖሊቲካዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን ለቀው ከሀገር ከመውጣታቸው በፊት እስከ ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ድረስ ለቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ አመራር ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ፣ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በስሙ በተሠየሙበት በሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓል ወደ ቅድስት ሀገራቸው ኢትዮጵያ መመለሳቸውን፣ ይታወቃል፡፡

💒ልደት
በፊት ስማቸው አባ ዘሊባኖስ ፈንታ የሚባሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ በአለታ ወረዳ አረጊት ኪዳነ ምሕረት በተባለችው ገዳም ሰበካ፣ ልዩ ስሙ ማር ምድር በ1930 ዓ.ም.፣ ከብላታ ፈንታ ተሰማና ከወ/ሮ ለምለም ገሰሰ ተወለዱ፡፡

💒መንፈሳዊ ትምህርት
ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ፣ በተወለዱበት ገዳም መሪጌታ ላቀው ከሚባሉ መምህር፣ ንባብና ዳዊት ተማሩ፡፡ ከዚያም በኋላ አጭታን ኪዳነ ምሕረት በምትባለው ደብር ምዕራፍና ጾመ ድጓ ተምረዋል፡፡
ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ሔደው ጎንጅ ቴዎድሮስ በተባለው ገዳም ለኹለት ዓመት ከመሪጌታ ወርቁ፣ ወደ ዋሸራ በመዛወር በቅኔ ዝነኛ ከነበሩት ከመሪጌታ ማዕበል ፈንቴ ለኹለት ዓመት በጠቅላላ በአራት ዓመት የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ከዚያም በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመልሰው፣ በደብረ ታቦር አውራጃ እስቴ ወረዳ አጋጥ ደብረ ጽዮን፥ የምዕራፍ፣ ጾመ ድጓና ድጓ ትምህርታቸውን ከመሪጌታ ሙጩ አጠናቀዋል፡፡
ወደ አቋቋም ቤት በመግባት፣ መነጒዘር በሚባለው ደብር፣ ከመሪጌታ ሚናስ ለኹለት ዓመት የአቋቋም ትምህርት ተምረዋል፡፡ ከዚያም ቁት አቡነ አረጋዊ ደብር፣ ከመሪጌታ ውብ አገኝ ለአንድ ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት ተምረዋል፡፡ ወደ ደብረ ታቦር አውራጃ ተመልሰው፣ ከጥንቱ መምህራቸው ከመሪጌታ ሙጩ ላቀ ዘንድ የድጓ ትምህርታቸውን በመቀጠል ጽፈውና አመልክተው ከጨረሱ በኋላ፣ በነፋስ መውጫ አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው በስመ ጥሩዋ በቤተ ልሔም አራት ዓመት ቆይተው ድጓ አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡
የድጓ ትምህርታቸውን ካስመሰከሩ በኋላ ወደተወለዱበት ገዳም ሔደው፣ በአረጊት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ለሰባት ዓመታት ያህል ድጓ አስተምረዋል፡፡

💒ሥርዐተ ምንኵስናና መንፈሳዊ አገልግሎት
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ሥርዐተ ምንኵስናን ከመምህርነት ጋራ አጣምሮ ለመያዝ ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ ስለኾነ በጣና ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ በመግባት ማዕርገ ምንኵስናን ከመምህር ኃይለ ማርያም(በኋላ የባሕር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ መልአከ ገነት) በ1961 ዓ.ም. ከተቀበሉ በኋላ፣ በዚሁ ዓመት ማዕርገ ቅስናን፣ ከጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡
የገዳምን ሥነ ሥርዐት ይበልጥ ማጥናት ስለፈለጉ፣ በባሕር ዳር አውራጃ ልዩ ስሙ ጋሾላ በተባለ ገዳም ገብተው የገዳሙን ሥነ ሥርዐት እያጠኑና ለገዳማውያን እየታዘዙ ለኹለት ዓመት ገዳሙን ረድተዋል፡፡ በገዳሙ በነበሩበት ጊዜ፣ በጸሎተ ማኅበር፣ የልማት ሥራ በመሥራትና አቅመ ደካሞችን በመርዳት ገዳሙን አገልግለዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በቅዳሴና በማሕሌት እያገለገሉ ትርጓሜ ሐዲሳትንና አቡሻኽርን ተምረዋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርታቸውንም በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት እስከ ኹለተኛ ደረጃ ተከታትለዋል፡፡
በተጨማሪም ለመምህራን፣ የተደረገውን የስብከት ዘዴ ኮርስ ለኹለት ዓመታት ተምረው የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

💒በቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት
የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው በመሾም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበረውን ችግር ተገንዝበው ለአገልጋዮች መኖሪያ ቤት አሠርተውላቸዋል፡፡ የእሑድ(የሰንበት) ት/ቤት ወጣቶችም የመሰብሰቢያ አዳራሽ ስላልነበራቸው አንድ አዳራሽ ከነሙሉ ድርጅቱ አሠርተው በመስጠት ችግራቸውን አቃለውላቸዋል፡፡ ተጀምሮ የነበረው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠናቀቅና በአካባቢው የነበሩ ምእመናንም በሰበካ ጉባኤ እንዲደራጁ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡

💒ሢመተ ጵጰስና
ባላቸው በቂ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀትና ባሳዩትም የመንፈሳዊ አገልግሎትና የሥራ ወዳድነት፣ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ባደረገችው የ13 ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምእመናን በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው የኦጋዴን አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ኾነው ተሾመዋል፡፡
በዚህ አውራጃ፣ በጠላት ፈርሶ የነበረውን ቤተ ክርስቲያን በማሠራትና በማሳደስ፤ በጦርነት ምክንያት የተሸበረውንና የተደናገጠውን ሕዝብ በማጽናናት ስለ ኢትዮጵያ አገሩ ፍቅር በማስተማርና በማስረዳት ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን ፈጽመዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በ1971 ዓ.ም. ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተዛውረዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በጎንደር ሀገረ ስብከት የፈጸሙአቸው ሥራዎች፡-
በወቅቱ በነበረው አለመረጋጋት፣ በጭልጋና በደባርቅ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ሕዝቡን በማስተማር ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በየጊዜው በሚያሳዩት መልካም የሥራ ውጤት፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሊቀ ጵጵስና ማዕርግ ተቀብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷን እንድትችል ለማድረግ ቀዳሚ ተግባር የሚኾነው ምእመናንን በሰበካ ጉባኤ ማደራጀትና ማጠናከር ስለኾነ፣ በሀገረ ስብከት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤን በማቋቋምና በማጠናከር፣ የሰንበት ት/ቤቶችንም በማስፋፋት ቅርሳቅርሶች በክብካቤ እንዲያዙ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ለሕዝበ ክርስቲያን እንዲደርሱ፣ የቤተ ክርስቲያን መመሪያና ደንብ ቃለ ዐዋዲ በተግባር እንዲተረጎም አድርገዋል፡፡
በጎንደር ክፍለ ሀገር የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታደሱና በርከት ያሉ አዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ አድርገዋል፡፡ በተለይም በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ፡-
የአረጊት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን በግል ገንዘባቸው ቆርቆሮ እንድትለብስ አድርገዋል፡፡
በዚሁ ወረዳ ውስጥ የምትገኘውን ደብረ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ ከግል ገንዘባቸው ብር 9ሺሕ በማውጣት ቆርቆሮ እንድትለብስ አድርገዋል፡፡
መንፈሳዊ አዳሪ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ፣ የካህናት ማሠልጠኛ እንዲቋቋምና ካህናት በተግባረ እድ የሚሠለጥኑበት ት/ቤት እንዲከፈት አድርገዋል፡፡
ምንም መተዳደሪያ ያልነበራቸው የአብነት መምህራንና ሊቃውንት፣ ለክህነት ከሚከፈለው ገንዘብ ደመወዝ እንዲቆረጥላቸው በማመቻቸት ሳይሰለቹና ሳይቸገሩ ሞያቸውን ለትውልድ እንዲያስተላልፉና የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችም በትምህርት አቅማቸውን እንዲያሻሽሉበት አድርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ለአንድ የዜማ መምህር፣ ለአንድ የቅዳሴ መምህር፣ ለአንድ ዕቃ ቤት ጠባቂ በድምሩ ለሦስት ሰዎች ከራሳቸው ደመወዝ በመክፈል ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ በብፁዕነታቸው ሊቀ ጵጵስና፣ 43 አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፤185 አብያተ ክርስቲያናት ተሠርተዋል፡፡

💒የልማት ሥራዎች፤
ሀ/ በጋይንት አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው በታላቋ ደብር ቤተ ልሔም ከአንድ በጎ አድራጊ ርዳታ በመጠየቅ በናፍጣ የሚሠራ አንድ የሞተር ወፍጮ አቋቁመው ለካህናቱና ድጓ ለሚያደርሱ ተማሪዎች ደመወዛቸውን እንዲችሉ ጥረዋል፡፡
ለ/ በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ ሊጋባ ቅዱስ ሚካኤል በተባለው ቤተ ክርስቲያን አካባቢ አንድ የሞተር ወፍጮ በጎ አድራጊዎችን በመጠየቅ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ አገልጋይ ካህናትም የወር ደመወዝተኛ እንዲኾኑ አድርገዋል፡፡
ሐ/ ጥንታውያን መጻሕፍት ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት፡- ጠቢበ ጠቢባን፣ ሙሉ ሲኖዶስ፣ የቅዳሴ አንድምታ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸውን ውሳኔዎች በሙሉ በብራና እንዲጻፉ አድርገዋል፡፡ በጭልጋ፣ በሊቦ፣ በደብረ ታቦር፣ በጋይንት አውራጃዎችና በእስቴ ወረዳ የችግኝ ጣቢያዎች አቋቁመው በየዓመቱ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ችግኞች በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሰበካና ለሕዝባውያን ድርጅቶች እንዲከፋፈሉ በማድረጋቸው የተራቆቱ መሬቶች በዛፎች እንዲዋቡ ጥረዋል፡፡
መ/ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በማስፈቀድ በማኅደረ ማርያም የሐዲሳት፣ የድጓና የቅዳሴ ት/ቤት አሠርተው ለመምህራኑ ከ50 እስከ 200 ብር ደመወዝ እንዲከፈላቸው፣ ለደቀ መዛሙርቱ ድጎማ እንዲሰጣቸው አድርገዋል፡፡
ሠ/ ጥንታዊውንና ታሪካዊውን የጣና ቂርቆስ ገዳም በብር 8ሺሕ835 እንዲታደስ አድርገዋል፡፡ በጣና ለሬማ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ብር 4ሺሕ ረድተዋል፡፡ የደረሞ ቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን ብር 21ሺሕ 114 በማውጣት አሳድሰዋል፡፡ እንዲሁም ጥንታዊውን የግርቢ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በብር 8ሺሕ860 ብር እንዲታደስ አድርገዋል፡፡ በአዘዞ በሰሚ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ካህናቱ ማሠልጠኛ የሚወስደው መንገድ በምግብ ለሥራ መርሐ ግብር እንዲሠራ አድርገዋል፡፡
በጎንደር መንበረ መንግሥት ጥበበ እድና የአዳሪ ቤቱ ዙሪያ ርዳታ በመጠየቅ ከ9ሺሕ በላይ በማወጣት እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ በጎንደር ጉባኤ ቤትና የዶክተር አየለ ዓለሙ የመቃብር ቤት የአራቱ ጉባኤያት ሥዕል እንዲሠራበት አድርገዋል፡፡
በሊቦ አውራጃ በቆላ እብናት ለአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ብር 15 ሺሕ ረድተዋል፡፡ በጎንደር ከተማ በአዘዞ አባ ሳሙኤል በመጠለያ ለሚረዱ ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ መምሪያ ጋራ በመተባበር የኤልክትሪክ ምጣድ ርዳታ አድርገዋል፡፡ በዳባት ወረዳ የሚገኘውን የደፍቂ ቅዱስ ሚካኤልን በብር 5ሺሕ፣ ቆማ ፋሲለደስን በብር 5ሺሕ አሳድሰዋል፡፡ ለአምስትያ ገዳም ብር 4ሺሕ፣ ለጣርክ ማርያም ብር 7ሺሕ ረድተዋል፡፡
ዐደባባይ ኢየሱስም በብር 40ሺሕ እንዲታደስ አድርገዋል፤ የድምፅ ማጉያም አስገብተውለታል፡፡ በጎንደር ዙሪያ አውራጃ ለቸንከር ተክለ ሃይማኖት ርዳታ በመጠየቅ ብር 764ሺሕ አበርክተዋል፡፡
በዚያው በጎንደር ዙሪያ ከማክሰኝት እስከ አርባያ ለመንገድ ሥራ ብር 30ሺሕ ርዳታ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡ ከእብናት እስከ ጎሐላ ለመንገድ ሥራ የብር 6ሺሕ ርዳታ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡
በስሜን አውራጃ ለሚገኙ ጥንታውያን ገዳማት፤ ለቤተ ሚናስ ዋልድባ ከብር 10ሺሕ በላይ፤ ለጣዕመ ክርስቶስ ብር 10ሺሕ፣ ለሰቋር ዋልድባ ብር 4ሺሕ ግምት ያላቸው የቁሳቁስ(የዓይነት) ርዳታ አድርገዋል፡፡
በጎርጎራ ገዳም በደሴተ ጣና ለሚገኙ ገዳማት፤ ለማን እንዳባ ገዳም ብር 1ሺሕ880፤ ለብርጊዳ ማርያም ገዳም ብር 1ሺሕ ለበሬ መግዣ እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ መምሪያ ርዳታ ሰጪ ድርጀቶች በመጠየቅ አቅም በፈቀደ መጠን በተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናት የቆዳ፣ የሽመና፣ የሹራብ ሥራ፣ የልብስ ስፌት፣ የወፍጮ ቤትና የዳቦ ቤት እንዲቋቋምና አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ለስብከተ ወንጌል፣ ለሰንበት ት/ቤትና ለሕዝብም መሰብሰቢያ የሚያገለግሉ አዳራሾች በየአብያተ ክርስቲያናቱ አካባቢ አሠርተዋል፡፡ ሕዝቡ ንጹሕ ውኃ ማግኘት እንዲችል የውኃ ጉድጓድ በማስቆፈር ለዚሁ የሚያገለግል ሞተርና ቧምቧ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረዋል፡፡

💒 ለሀገረ ስብከቱ ያስገኟቸው ሽልማቶች፤
የሰበካ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ደንብ በትክክል እንዲፈጸም በማድረጋቸውና ሰበካ ጉባኤን በሚገባ በማደራጀታቸው፣በየዓመቱ በሚደረገው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ የሥራ ግምገማ በተደረሰበት ውጤት የጎንደር ሀገረ ስብከት ቅድሚያ ቦታ እንዲይዝ አድርገዋል፡፡
በዚህም መሠረት፡- ከ16ቱ አህጉረ ስብከት፣ ከ1975 እስከ 1977 ዓ.ም. በተከታታይ እንዲሁም በ1979 ዓ.ም. አንደኛ፤ በ1978 ዓ.ም. ኹለተኛ በመኾን በውጤታማነት እንዲሸለም አድርገዋል፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ከዚህ በላይ ጠቅለል ባለ መልክ በተዘረዘረው ዓይነት ተልእኳቸውን በትክክል የተወጡ አባት ከመኾናቸውም በላይ በ1979 ዓ.ም. በተደረገው የብሔራዊ ሸንጎ አባላት ምርጫ በጎንደር ዙሪያ አውራጃ ምርጫ ጣቢያ ደንቢያ ከመረጠው 26ሺሕ127 ሕዝብ መካከል 17ሺሕ249 ድምፅ በማግኘት ተመርጠው ሕዝብን አገልግለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ የበላዮቻቸውን መካሪ፣ የበታቾቻቸውን አክባሪ፣ በሥራ ታታሪ፣ መንፈሳዊ አባትነታቸውና ትሑት ሰብእናቸው አርኣያነት ያለው ቁጥብ አባት ናቸው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ መካሄድ ጀመረየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።ጉባዔውን አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእ...
22/10/2025

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።

ጉባዔውን አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በፀሎት አስጀምረዋል።

በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ በተለያዩ መንገዶች እየተከናወኑ የሚገኙ ቤተክርስቲያንን የመዳፈር ተግባራት ለመፍታት በሕግ አግባብ መንቀሳቀስ ይገባል።

የነገ ትውልድ ልማታዊ ተስፋ እውን የሚሆነው ሰላምና አንድነት ሲኖር በመሆኑ ሁሉም ለሀገር ሰላምና አንድነት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም ጉባዔው የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በምልዓተ ጉባዔው ላይ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት የመጡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተገኙ ሲሆን በቤተክርስቲያኗ እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

20/10/2025

የተከለከሉ ምግቦች ስለምን ተከለከሉ

💠💠💠💒የጽጌ ጾም💒💠💠💠በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ እርሱን ለማስገደል አሰበ፡፡ ያንጊዜ...
15/10/2025

💠💠💠💒የጽጌ ጾም💒💠💠💠

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ እርሱን ለማስገደል አሰበ፡፡ ያንጊዜም ጌታችን በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብፅ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታችንን ያገኘው መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ ሀለት ዓመት ከዚያ በታች የሆኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በግፍ አስፈጅቷል፡፡

በተአምረ ማርያምና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ውሃ በጠማቸው ጊዜ ውሃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንን ውሃ ክፉዎች እንዳይጠጡት መራራ ማድረጉ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ሆኖ እንዲቆይ ማድረጉ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ እንደ ቀድሞው ደኅና እንድትሆን ማድረጉ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የጌታችንና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኃ ግንቦት ነው፤ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ በዘመነ ጽጌ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በሰፊው ተገልጧል፡፡

የጽጌ ጾም በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ያሉት አርባ ቀናት ዘመነ ጽጌ (ወርኃ ጽጌ) እንደሚባሉ ይታወቃል። በነዚህም ቀናት በየቤተ ክርስቲያኑ የሚነበቡ ምንባቦች፣ የሚዘመሩ መዝሙሮች፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚቆመው ማኅሌት፣ በጠቅላላው የሚነገረው ስብሐተ እግዚአብሔር ሁሉ ሰማይ በከዋከብት ምድር በጽጊያት አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው። በወርኃ ጽጌ ለሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት መነሻው ‹‹መልአኩ ሕፃኑና እናቱን ወደ ግብጽ ይዘሃቸው ሽሽ፤ ሕፃኑን ሊገድሉት ይሻሉና›› ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሰረት ሕፃኑን እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ ዮሴፍ ወደ ግብፅ መሰደዱና እመቤታችንና ሕፃኑን ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ ወደ አገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው። (ራእይ ፲፪፥፲፮)

በዐሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡ አባት አባ ጽጌ ብርሃን ‹‹የሮማን ሽቱ የቀናንም አበባ የምትሆኝ ማርያም ሆይ ፥ በረሃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪ ጠወልግ ድረስ በስደትና በለቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እኅትሽ እንደ ሶሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፤ በዚህም ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር።›› ብለዋታል፡፡ እንዲሁም አባ አርከ ሥሉስ በስደቷ የደረሰባትን ኀዘን፣ ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት ‹‹ሰቆቃወ ድንግል›› በሚለው ድርሰታቸው እንዲህ አሉ፦ ‹‹ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሽ ጊዜ የደረሱብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንዳጎበጎቡ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር።››

በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታትም ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን የሚተነትነው ቅዳሴ ማርያም ነው፤ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው፡፡

የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው። በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጥዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌተ ጽጌና ከሰቆቃወ ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው። ዝክሩም በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፥ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢው ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው። ዐቅመ ደካሞች ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል። ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው።

የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ዜና ገድል የጽጌን ጾም አስመልክቶ የሚከተለውን ይተርካል፦ ‹‹አባ ጽጌ ብርሃን የተባለው አባት እንደ መዝሙረ ዳዊት መቶ ኀምሳ አድርጎ ማኅሌተ ጽጌን ደረሰ። አባ ጽጌ ብርሃን ይህንን በደረሰበት ጊዜ የወረኢሉ ተወላጅና የደብረ ሐንታው አባ ገብረ ማርያም አማካሪው ነበር። ድርሰቱንም ሲደርስ ቤት እየመታና በአምስት ስንኝ እየከፋፈለ ነው። አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም ከመስከረም ፳፮ ቀን እስከ ኅዳር ፭ ቀን ማኅሌተ ጽጌን ለመቆምና የጽጌን ጾም ለመጾም በየዓመቱ በደብረ ብሥራት እየመጡ ይሰነብቱና ቁስቋምን ውለው ወደየ በአታቸው ይመለሱ ነበር።›› ከአባታችን የገድል ክፍል ለመረዳት እንደሚቻለው አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም የጽጌን ማኅሌት መቆም ወቅቱንም በፈቃዳቸው መጾም የጀምሩበ ዘመን በዐሥራ አራተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።

ከዚያ ወዲህ ግን ጥቂት በጥቂት እያለ አብያተ ክርስቲያናት በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ጀመሩ። ጥቂት መነኩሳትና አንዳንድ ምእመናን በፈቃዳቸው ወቅቱን መጾም ጀመሩ። በዘመናችን በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ስለ ተለመደ ከማታው በሦስት ሰዓት ይደወላል። ሴት ወንዱ፥ ትንሹም ትልቁም ይሰባሰባል፤ ማኅሌተ ጽጌው እየተዜመ፤ አስፈላጊ የሆነው በጽናጽል በከበሮ እየተወረበና እየተሸበሸበ እስከ ጥዋቱ ፲፪ ሰዓት ድረስ ተቁሞ ይታደራል። የጽጌ ጾም የውዴታ (የፈቃድ) እንጂ የግዴታ አይደለም። የእመቤታችን ስደት በማሰብ ከትሩፋት ወገን የሚጾም ስለሆነ ምእመናን ሁሉ እንዲጾሙት አይገደዱም፤ የሚጾመው የማይጾመውን ለምን አልጾምክም ብሎ ሊፈርድበት ስለ ራሱም እየጾምኩ ነው ብሎ መናገር አይገባውም። የፈቃድ መሆኑንም የሚያሳየው ይኸው ነው፤ የማይጾመውም በልቡ ያመሰግናል፤ ስደቷን እያሰበ ማኅሌቷን እየዘመረ ያሳልፋል።

አምላካችን እግዚአብሔር የጽድቅ ፍሬን ሳናፈራ በሞት እንዳንወሰድ በቸርነቱ ይጠብቀን፤ አሜን፡፡

የመስከረም ጌጦችወንዞች ንጹህ ሆነው ታዩ፡፡ ጋራ ሸንተረሩ  አደይ አበባ ለበሰ፡፡ ምክንያቱም መስከረም ገብቷል።  ወርሃ መስከረም ከገባ ቀናት መቆጠር ጀምረዋል። የዘመን መለወጫ በዓል ስሜቱና...
07/10/2025

የመስከረም ጌጦች

ወንዞች ንጹህ ሆነው ታዩ፡፡ ጋራ ሸንተረሩ አደይ አበባ ለበሰ፡፡ ምክንያቱም መስከረም ገብቷል። ወርሃ መስከረም ከገባ ቀናት መቆጠር ጀምረዋል። የዘመን መለወጫ በዓል ስሜቱና ድባቡ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡ ከመልክዐ ምድሩ ውበት በተጨማሪ ውብ እና ድንቅ የሆኑ በዓላት የሚከበሩበት ወርም ነው፡፡

የዘመን መለወጫ በዓል

ተናፋቂው መስከረም በዘመን መለወጫ በዓል አንድ ብሎ ይጀምራል፡፡ በዓሉም በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጉጉት የሚናፈቅና በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የወራት ሁሉ መጀመሪያ መስከረም ነው፡፡ መስከረም ወር ዘመን መለወጫ፣ ዕንቁጣጣሽ በሚሉ እና በሌሎች ስሞች ይጠራል፡፡

አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የዕድሜያችን ቁጥር የሚጨምርበት ብቻ ሳይሆን በኑሮ ላይም አዎንታዊ ለውጥን ለማድረግ ዕቅድ ይዘን የምንነሳበትም ነው። አዝመራዉ እንዲያሽት፣ ውጥን እንዲሳካ፣ የጠባው አዲስ ዓመትም ሰላምን፣ ጤናን፣ ፍቅርንና መግባባትን ሰንቆ እንዲያልፍ ምኞት የሚገለጽበት ጭምር ነው። በአዲስ ዘመን ሀገርና ህዝብ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ ዕቅድና በአዲስ ተስፋ መጪውን ዘመን ይቀበሉታል፤ ከአሮጌው ዘመን በመማር ለአዲሱ ዓመት የተለያዩ ዕቅዶችን ያወጣሉ ይላል ዶቼቬለ እ.ኤ.አ በ2010 በአዲስ ዓመት “አዲስ ግብ አዲስ ተስፋ” በሚል ርእስ ባሰፈረው ጹሑፍ። በእርግጥም መስከረም አዲስ ነው፡፡ ተማሪዎች በአዲስ መንፈስ ወደ ትምህርት ቤት ያቀናሉ፡፡ ሰዎች በአዲስ ስሜት ለአዲስ ለውጥ ይነሳሉ። ሁሉም አዲስ ነው፡፡ የዘመን መለወጫም በመስከረም ወር የሚከበረው የመጀመሪያው በዓል ነው፡፡

መስቀል

በመስከረም ወር ከሚከበሩ በዓላት መካከል መስቀል ሌላኛው ተጠቃሽ ነው፡፡ የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘት ካላቸው በዓላት ተርታ የሚመደብ ነው። የመስቀል በዓል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበር ሲሆን፤ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶችም በብዛት ይታደሙበታል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ ዕለቱ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥነ ስርዓቶች ጭምር ደምቆ ይውላል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል ማራኪ ህብረ ቀለም ይታይበታል፤ በዝማሬ፣ ችቦና ደመራ በማብራትም ይከበራል፡፡ መስቀል ምንም እንኳን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ቢሆንም ከኃይማኖታዊ ክንዋኔው ባሻገር፣ ባህላዊ በሆነ ገፅታ የሚያከብሩት የማህበረሰብ ክፍሎችም በርካታ ናቸው፡፡

የመስቀል በዓል አከባበር በ2006 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ይታወሳል፡፡ በዓሉ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ በተካሄደ 8ኛው ጉባዔ ላይ ነበር፡፡

07/10/2025

የዐዲሱ ዓመት የ2018 ዓ.ም. የመስከረም ሙሉዋ ጨረቃ በአበባው የመፀው ወቅት ራሴን በራሴ ሰልፊ ከምሽቱ 1:21 መስከረም 27 ላይ አነሣኹ። መሬት መሬት ማየት ሳይኾን ሰማይን ቀና ብላችኹ ማየት የለመዳችኹ የእናንተን ፎቶዎች
በቴሌግራም https://t.me/+xN518gdGKvswNzE0
አጋሩኝ። መላው ዓመት እንደ ሙሉዋ ጨረቃ ሕይወታችን በእግዚአብሔር ብርሃን የሞላ፣ ያበራና የደመቀ ይኹን። እንደ አበባው ወቅት የፈካ፣ ያበበ፣ በበጎ መዐዛ የተሞላ ይኹን። ቀጣይዋ ሙሉ ጨረቃን ጥቅምት 26 እናገኛታለን።

07/10/2025

♥ መስከረም 29 የቅድስት አርሴማ ዓመታዊ ክብረ በዓል በዐዲስ አበባ በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲኾን መጥታችኹ በዓሉን በማክበር የቅድስት አርሴማ በረከት ተካፋይ ኹኑ፨
"ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? "
(1ኛ ቆሮንቶስ 6: 2)

Address

Addis Ababa

Telephone

+251913122946

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when GrandMom The Promise Land posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to GrandMom The Promise Land:

Share