10/09/2025
“በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ዋዜማ ዕለት በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የሕወሓት ቡድን ታጣቂዎች በአላማጣ ከተማ የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ አድረዋል”
- አቶ ኃይሉ አበራ፣ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ
ረቡእ ጳጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ( #አዲስ ማለዳ)
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ዋዜማ ዕለት በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የሕወሓት ቡድን ታጣቂዎች በአላማጣ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ዝርፊያ፣ በገበያ ማዕከል ላይ ጥይት ተኩሰው ቃጠሎ በማስነሳት ንብረት በማውደምና ንጹሐንን በመግደል የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ማደራቸውን የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የሕወሓት ቡድን ታጣቂዎች በአላማጣ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ያስታወሱት ከንቲባው፤ ጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ዋዜማ ዕለት ደግሞ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ሕዝቡ የግድቡን ምርቃት ወጥቶ እንዳያከብር በሚል አስተሳሰብ በአላማጣ ከተማ ሽብር ሲፈጽሙ ማደራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በዕለቱ ምሽት ሦስት ሰዓት ጀምሮ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ዝርፊያ ፈጽመዋል። በተለይም ወደመሆኒ፣ ቆቦና ኮረም መሄጃ መስቀለኛ መንገድ አደባባይ ላይ ሆነው ተኩስ በመክፈት በአካባቢው በሚገኝ ባለአራት ወለል ሕንጻ የገበያ ማዕከል ላይ እሳት እንዲነሳ በማድረግ የገበያ ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ አውድመዋል።
በገበያ ማዕከሉ በተነሳው እሳትም በውስጡ የሚገኙ ከአርባ በላይ ሱቆች ሙሉ በሙሉ ወድሟል። አንድ ሰው በከፍተኛ ደረጃ የቆሰለ ሲሆን የሦስት ሰዎች ሕይወትም አልፏል።
የሕወሓት ታጣቂዎች በከተማዋ አካባቢዎች ከፈጸሙት ዝርፊያ በአሻገር በገበያ ማዕከሉ በከፈቱት ተኩስ በውስጡ ያሉ ተቀጣጣይ ነገሮች የተነሳ በተፈጠረው ቃጠሎ የሞቱትን ጨምሮ በድምሩ በንጹሐን ላይ በፈጸሙት ጥቃት በአራት ሰዎች ላይ የሞትና በአምስት ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ መፈጸሙን ከንቲባው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የጥቃቱን ዓላማ በተመለከተም “በተለያየ ጊዜ በሞከሩት ተመሳሳይ ጥቃት አልሳካ ያላቸውን ሕዝቡን ንብረቱን በመዝረፍ፣ መኖሪያና መስሪያ ቦታውን በማቃጠልና በመግደል ሕዝቡን በማሸበር በኃይል ማፈናቀልና ከከተማው በማስወጣት የራሳቸውን አስተዳደር መመሥረት ነው” በማለት አብራርተዋል።
በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የሕወሓት ታጣቂ ቡድን ዋነኛ ዓላማው እንዲያስተዳድረው ወዳልተፈቀደለት አካባቢ በኃይል በመግባትና ሕዝብን በማሸበር የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በማፍረስ በአካባቢው ግጭትና ጦርነት ለመቀስቀስ መሆኑንም ከንቲባው አመላክተዋል።
ይህን የተገነዘበው የከተማው ሕዝብና መንግሥትና በስፍራው የሚገኜው የመከላከያ ሠራዊት አባላትም የታጣቂ ቡድኑን ሕገ ወጥና አፍራሽ ድርጊት በትግስት እየተከታተሉት መሆናቸውንና እስከመጨረሻው ድረስ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተጠባበቁ መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባው፤ ጉዳዩን ለክልልና ለፌደራል መንግሥታት ማሳወቃቸውንም ገልጸዋል።
“የትግራይ ሕዝብም ጉዳዩን ተገንዝቦታል፤ የታጣቂ ቡድኑን ድርጊት እየተቃወመውም ነው፤ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ችግሩን የተገነዘበው ይመስላል፤ እኛ ለሁሉም በመረጃና በማስረጃ አሳውቀናል” ያሉት የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ፤ እስከመጨረሻው በትግስትና በሰላማዊ መንገድ ሄደን ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ የሽብር ድርጊቱ የማይመለስ ከሆነ ግን ሕዝቡ በእጁ ያለውን አማራጭ ለመጠቀም የሚገደድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኜት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA