
28/05/2025
እግሩ ተቆርጦ አገኘሁት..
መቼም መገናኛ የማያሳየን የለም።
አንድ ለአልፎ ሄያጁ ግራ የሚያጋባ፣ መተዳደሪያውን ልመና ላይ ያደረገ ሰው ነበረ::
ሁለት እግሮቹ በፋሻ ተጠቅልለዋል:: በአለፍኩ በአገደምኩ ጊዜ ሁሉ አየዋለሁ።
በፋሻ በተጠቀለለው እግሩ ላይ ጂቪ እና ደም ይታያል:: እግሮቹን የህክምና ባለሙያ እንዳላየው በፋሻው አጠቃለሉ ያስታውቃል:: እነደነገሩ ነው ሸብ ያደረገው።
የ'ዚህ ሰው ቁስል አለመዳን በመንገዴ በአጋጠመኝ ቀን ሁሉ ይገርመኝ ነበር። አጃኢብ ነው ይላል ወሎ። ሰውየው ነጭ ጅብ አይቶ 'የሚአጅብ ነጭ ጅብ' ይል ነበር በተገረመበት ነገር። ይህን ሰው በመንገዴ ባየሁት ቀን ሁሉ ይአጅበኝ ነበር።
አንድ ቀን ቀረብ ብዬ "ለምን ወደ ህክምና ተቋም አትሄድም ? እግርህ በቀላሉ መታከም እና መዳን ይችላል።" ብዬ ጥያቄ እና ምክር እንዳይመስልብኝ ፈራ ተባ እያልኹ ሀሳቤን አቀረብኩ:: እንዲህ ያደረኩት አንድ ቀን ብቻ አልነበረም። ደጋግሜ ጠይቄዋለሁ::
ድሮ ድሮ ከምክሬ በፊት ወይም በኋላ ትንሽ ገንዘብ ስለማስጨብጠው ይሁን በሌላ ምክንያት አላውቅም ' እሺ፣ ልክነህ፣ ሄጄ እታከማለሁ' ይለኝ ነበር።
ምን አገባህ ባይለኝም፣ ሲሰለቸው ጊዜ ይህን አለኝ:: “እግሬን ካላቆሰልኩት እና እንደ እሳት ካልቆሰቆስኩት መች ይሆንልኛል ብለህ። ይህን ሳላደርግ መብላት እና መጠጣት እንዴት ይታሰባል? ”አለኝ::
ሱስ የሆነበትን እና ገቢ የፈጠረለትን ቁሰሉን አድኖ ልመናውን ማቆም እንደማይፈልግ በግልፅ ነው የነገረኝ። መጠየቄን፣ መጨነቄን እና መጨቅጨቄን ተውኩት::
ከዚያ ቀን ጀምሮ ረዘም ላለ ጊዜ አይቸው አላውቅም::
ሰሞኑን መንደር እና መንገድ ቀይሮ፣ ከፊቱ ከተነጠፈው ገንዘብ መሰብሰቢያ ጨርቅ ላይ አፈንግጠው ዳር የወጡትን ፍራኮች ሲሰበስብ አየሁት::
ነገር ግን እንደከዚህ ቀደሙ ሁለት እግሩን በፋሻ ጠቅልሎ አልነበረም ያየሁት::
አንድ እግሩ የለም ተቆርጧል::
በአንድ እግሩ ሆኖ መለመኑን ቀጥሏል::
" አንድ አይን ያለው በአፈር አይጫወትም " የሚለው ይትበሀል አላስጨነቀውም። ሱስ ሆኖበት አልያም ገቢው በለጦበት፣ ታክሞ ሊድን የሚችለውን አንድ እግሩን እንዳስቆረጠው፣ ቀሪውንም ማቁሰሰሉን ቀጥሏል::
ከዚያስ ? .... ራሱን ገዝግዞ ጣለ ።
ለመዳንም ለመሞትም ጊዜ አለው።
ከዚያስ?
ሁለተኛውን ደግሞ ሲያስቆርጠው እነግራችኋለሁ።