23/02/2026
የውጊያ ማርሽ ቀያሪው
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የካቲት 14 ቀን 2018 ዓ.ም
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚሠጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በእምነት የሚፈፅምና በከፍተኛ ፅናት ዘብ የሚቆም እንዲሁም በተሰማራበት የውጊያ ውሎ የውጊያው ማርሽ ቀያሪ እና አይበገሬ ሠራዊት ሆኖ በመገንባት ባሳለፍናቸው ዘመቻዎች አኩሪ የጀግንነት ታሪክ እንደ ዕዝ በመፈፀም የላቀ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡
በዕዙ ሥር ካሉት ክፍሎች አንዱ የዕዙ ማሠልጠኛ ማዕከል ሲሆን ማዕከሉ ማንኛውንም ወታደራዊ ግዳጅ ህዝባዊ ባህሪን ተላብሶ፣በላቀ አስተሳሰብ፣ ስነልቦና፣ አካላዊ፣ ቴክኒካዊና ሥልታዊ ብቃት መፈፀም የሚችሉ የኮማንዶ ፣የአየርወለድ፣ የልዩ ኃይል እና ፀረ-ሽብር ተዋጊ ወታደሮችን እና የበታች ሹም አመራሮችን በማፍራት ሀገራዊ ተልዕኮውን በውጤት እየፈፀመ ይገኛል፡፡
ማሠልጠኛ ማዕከሉ የሀገር ወዳድነት ተምሳሌቶች እና ገፀ በረከቶች የሆኑ የሰራዊት አባላት እና ብቃታቸውን በተግባር ያረጋገጡ አሰልጣኞችን በመያዝ የበኩሉን ድርሻ የተወጣ እና እየተወጣ የሚገኝ የግንባታ ማዕከል ነው፡፡
የኮማንዶ ማሠልጠኛ ልዩ የሆነ የግዳጅ አይነቶችን እንደ አስፈላጊነቱ ከየብስ ፣ከባህር እና ከአየር በመነሳት ውጊያን ማከናወን የሚያስችል አቅም ያላቸውና በተሰማሩበት የግዳጅ ቀጠና ተጣጣፊ በሆነ ወታደራዊ ብልሃት ተልዕኳቸውን የሚፈፅሙ የውጊያ ማርሽ ቀያሪና ጠላት አንበርካኪ አባላትን በሚገባ አሠልጥኖ የሚያበቃ አንጋፋ ማሠልጠኛ ነው፡፡
ማንኛውንም የውጊያ ግዳጅ ለመወጣት የሚያሥችሉትን እና ድንገተኝነትን የሚያላብሱ ወታደራዊ አቅምን የሚያሥጨብጡ የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ሁለንተናዊ ብቃትን የተላበሱና የተመረጡ አቅም ፈጣሪ አቅም ያላቸው በዘመኑ የውጊያ ጥበብ ወታደራዊ አስተሳሰብ ላይ የረቀቁ ቴክኒኮችን እና ታክቲኮችን በብቃት በማስጨበጥ አሰልጣኞች አሥተዋጿቸው ከፍተኛ ነው፡፡
በከፍተኛ የዓላማ ፅናትና ቁርጠኝነት እንዲሁም በዲስፕሊን አክባሪነት የተገነቡ በሃገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ የሚሰጣቸውን የልዩ ኦፕሬሽን ውጊያ ተልዕኮ በነፍስ ወከፍ እና በቡድን በላቀ የጀግንነት ውጤት ተልዕኳቸውን የሚወጡ ወታደሮችን በማሠልጠን ማሰልጠኛ ማዕከሉ ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል፡፡
ጠንካራ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ዕምነት ያላቸው በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ የሚሰጣቸውን የኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል በብቃት መምራትና ግዳጃቸውን መወጣት የሚችሉ እንዲሁም መመሪያና ደንብና ጠንቅቀው ያወቁ በመመሪያ መፈጸምና ማስፈፀም የሚችሉ የበታች ሹም አመራሮችን ማፍራት ላይም ማሠልጠኛ ማዕከሉ ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል፡፡
በድምሩ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በአራቱም የሀገራችን ማዕዘናት በመንቀሳቀስ ለተፈጥሮ መሰናክሎች ሳይበገር በርሃውን፣ ውሀ ጥሙን፣ አስቸጋሪውን የእግር ጉዞ አልፎ ለሀገራችን ሰላምና ፈጣን ልማት በመስዋዕትነት የደመቀ ህያው ታሪክ ያኖረ ዕዝ ሲሆን አሁንም አባላቱ በታላቅ ሀገራዊ ጀግንነት ተልዕኳቸውን በውጤት እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ