
10/09/2025
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2018 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አጋርተዋል፡፡
2018 ለኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያ ወዳጆችና ለድፍን አፍሪካውያን በከፍተኛ ብስራትና ድል የታጀበ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ነው ያሉት አቶ ሙስጠፋ ሀገራችን ኢትዮጵያ በክቡር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ( ዶ/ር) ቆራጥ አመራር ሰጪነት እውን የሆነውንና መላው የሀገራችን ህዝብ በነቂስ አሻራውን ያሳረፈበት የታላቁ ህዳሴ ግድብን በመረቅን ማግስት የምናከብረው እንደመሆኑ ልዩና ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያን ትንሽ ትልቅ ሳይሉ በአንድነት የቆሙለትና የመቻል ማሳያ የሆነው “አይቻልም፣ አይሆንም፣ አይሳካም” ሲባል የነበረው ግድባችን መጠናቀቅን ተከትሎ የምናከብረው እንደ መሆኑ በግድቡ ላይ እንደ አንድ ሆነን ያሳረፍነውን አሻራ በክቡር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተበሰሩ የታላቅነታችን፣ የአንድነታችን፣ የህብረታችን ማሳያ የሚሆኑ ቀጣይ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በተባበረ ክንድ በማሳካት የተጀመረውን የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ አስቀጥለን ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ቃል የምንገባበት ዘመን ነው ብለዋል፡፡
ነገ አንድ ብለን በምንቀበለው አዲስ ዓመት ብስራትና ድሎቻችን ይበልጥ የሚያንጸባርቁበት፣ ከበረከቱ ፍሬ የምንቋደስበት፣ የኢትዮጵያ የመነሳት ደውልም ከሀገራችን አልፎ ለአህጉራችንም የሚሰማበት እንዲሆን እመኛለሁ ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ለመላው ኢትዮጵያውያን በሙሉ የ2018 አዲስ ዓመት የሰላም፣ የአንድነት፣የፍቅርና የሰላም እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክት አጋርተዋል፡፡