02/10/2025
ይድረስ ለአክቲቪስት ስዩም ተሾመ እና ለወዳጄ ሳዲቅ አህመድ ❗
----
ፖለቲካ ካለ እውቀት እና በቂ መረጃ በየመንገድ አይወራም
ሰሞኑ ተወልጄ ባደግኩባት የፍቅር ከተማ በሆነችው ቡታጅራ ተፈጥሮ በነበረው የተወሰነ ግርግር ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት አካላት ከግርግሩ ጋር ፍጹም የማይሄድ ያልተገባ ስም እና ፍረጃ ሲሰጡት አይቻለሁ
ስዩም ተሾመ " ቡታጅራ ማለት ሌባ ማለት ነው ብለዋል አባ ጅፋር ሲል ሰማሁት ወዳጄ ሳዲቅ አህመድ ደግሞ ጭራሽ ግጭቱ ኃይማኖታዊ ይዘት ያለው ነው ብሎት እርፍ አለ
ሁለቱም ፍጹም የተሳሳተ ፍረጃ ነው የሰጡት
ሲጀመር ቡታጅራ የሚለውን ስያሜ የሰጡት የጅማው አባ ጅፋር አይደሉም ::
----
ከወላይታ ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ወላይታ እና ደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ይጓዙ የነበሩ ነጋዴዎች በመንገዳቸው መረጃ ለመለዋወጥ ሽፍታ አለ ወይ ? በአፋን ኦሮሞ ( ቡታ ጅራ ? ) ብለው ሲጠያየቁ የተፈጠረ ስያሜ ነው
ስዩም ተሾመ እንደሚለው ሌባ ማለት አይደለም ቡታጅራም ሌባ አይደለችም የአካባቢውን ተወላጆችን ብቻ ሳይሆን የኔን አባት ጨምሮ ከሌላ አካባቢ መጥተው ይኖሩ የነበሩ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆችን እንዴት አክብሮ ሹሞ ሸልሞ ለትልቅ ኃላፊነት አብቅቶ በአካባቢው አስተዳደርም ሆነ የሽምግልና ስርዓት ትልቅ ቦታ ሰጥቶ እስከዛሬ አክብሮ የኖረ የሰለጠነ ፍቅር የሚታፈስበት ሃገር ነው ቡታጅራ
----
ለዚህም እንደ ማሳያ የምጠቅሳቸው ከጎንደር ህብረተሰብ ተወልዶ ከአዲስ አበባ የመጣው ጋሽ በቀለ አየለ እስከዛሬ ከማክበር አልፎ ከመሸለም አልፎ በስሙ ትምህርት ቤት የተሰየመለት ጀግና ነው እስከዛሬ አስተምሯቸውም ሆነ በዳሬክተርነት ዘመኑ በሱ ስር ያለፉ ተማሪዎችም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ እንደሱ የሚፈሩት እና የሚያምኑት ሰው የለም ለዚህም ማሳያው ሆስፒታሉን ጨምሮ የተለያዩ ተቋሞችን እንዲያሰራ ሃላፊነት ጥለውበት እሱም ያለ ምንም ሌብነት በጨዋነት አጠናቆ አስረክቦአል ጀግናን ማክበር የሚያውቀው የቡታጅራ እና አካባቢው ማህበረሰብ ይኸው እንዳከበረው ዘልቆአል
---
ሁለተኛው ከሃድያ ብሔረሰብ የመጡት አቶ ማቲዎስ ባካ ( ነብሳቸውን ይማር ) ይሰጡ ከነበረው የህክምና ሙያ ጎን ለጎን የቡታጅራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ ሊቀ መንበር በመሆን ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት አገልግለው ለአካባቢው ልማት ደፋ ቀና እንዳሉ እንደተከበሩ አልፈውል
ለዚህ ክብራቸው ሆቴላቸውን የገዛው ጸጋዬ የተባለ ግለሰብ ምንም እንኳ ሆቴሉን የገዛው በገዛ ገንዘቡ ቢሆንም ለክብራቸው ሲል የሆቴሉን ስያሜ አልቀይርም ብሎ ይኸው እስከዛሬ የሆቴሉ ስም " ማቲዮስ ሆቴል " ነው የሚባለው
ከኦሮሞ ብሔረሰብ የተወለደው አባቴ አደም ሐሰን ከአካባቢው ሽማግሌዎች እኩል የተጣላ አስታርቆ ለሚያገባ ሽምግልና ተልኮ እኛን ወልዶ አሳድጎ ለቁም ነገር አብቅቶ እሱ የዋለበት ሽምግልና ውሸት አይነገርም ፍርድ አይጓደልም እንደተባለ እንደተከበረ አልፎአል ( አላህ ይርሃመው )
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ስዩም ተሾመ በቡታጅራ ላይ ለፈጸመው የስም ማጥፋት ይቅርታ ሊያስጠይቀው ወይም በህግ ሊጠይቀው ይገባል
---
ወደ ወዳጄ ሳዲቅ አህመድ ስመለስ ግጭቱ ኃይማኖታዊ ይዘት እንዳለው ጽፎአል ይሄ ፍጹም ቡታጅራን የማይወክል ፍረጃ ነው
ቡታጅራ መስጂድ ሲሰራ ክርስቲያኑ የመስጂድ አሰሪ ኮሚቴ የሚሆንባት እና ገንዘብ የሚያዋጣበት ቤተ ክርስቲያን ሲሰራ ሙስሊሙ ገንዘብ የሚያዋጣባት በዓሎቻቸውን በፍቅር ተጠራርተው በጋራ የሚያከብሩባት ጎረቤታሞች የሆኑት የትልቁ መስጂድ እና የቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያ ቅዳሴ እና አዛኑ የሚንፎለፎልባት ከፍ ሲልም ሙስሊም እና ክርስትያኑ ተጋብቶ የሚኖርባት የመቻቻል ውብ ከተማ ነች ቡትዬ
----
የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ በውጭ ሃገር እና በሃገር ውስጥ የሚኖሩ የቡታጅራ እና አካባቢዋ ተወላጆች በአካባቢው ለሚገኙ የእስልምና ተከታይ አቅመ ደካሞች በዓመቱ ሳይቋረጥ ለአረፋ በዓል እስከ አስር የሚጠጉ ሰንጋዎችን ገዝተው ለአረፋ በዓል አርደው የሚያበሉ እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ በውጭ ሃገርም ሆነ በሃገር ውስጥ ያሉ የቡታጅራ እና አካባቢዋ ልጆች ሁሌም በዓመት መስቀል አቅመ ደካማ ለሆኑ የክርስትያን ወገኖቻቸው እስከ አስር በሬዎችን ገዝተው ደሃዎች በዓመት በዓል ጾም እንዳይውሉ የሚያበሉ በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የክርስትናም ሆነ የእስልምና እምነት ተከታይ ታራሚዎች ያለ ልዩነት በየዓመቱ ለሁለቱም በዓላት ለአረፋ እና ለመስቀል አርደው የሚያበሉ እንቁ ልጆችን ያፈራች ነች ቡትዬ
---
የአንድ ሰው መብት በሚከበርባት የዓለም ህዝብ ተሰብስቦ በአንድ ህግ እየተመራ በሰላም በሚኖርባት አሜሪካ ተቀምጠን ለዘመናት አብረው በኖሩ ሲጋቡ ሲዋለዱ በኖሩ በሁለት ወንድማማች መካከል የሚፈጠሩ ጥቃቅን ችግሮችን በውይይት እና በመቻቻል እንዲፈታ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ሲገባን ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ መሄድ አይገባንም ወይም ከጉዳዩ እና ከአጀንዳው በላይ መጮህ እና ማስጮህ ጩኸቱ ከፍየሏ በላይ እንዳይሆን ያሰጋል
ለማንኛውም ተወልጄ ያደግኩበት የዋህ ህዝቤን አውቀዋለሁ
አባት አለው ሽማግሌዎች አሉት ሁሉም ነገር በሰላም እና በውይይት እንደሚያልቅ ምንም ጥርጥር የለኝም እገዛችንን ስትፈልጉ ጥሩን
---
ተወልጄ ያደግኩብሽ ጣፋጩን የልጅነት እና የወጣትነት ጊዜዬን ያሳለፍኩብሽ ትዳሬን የያዝኩብሽ ቡትዬ ሁሌም ሰላምሽን እና ፍቅርሽን እመኝልሻለሁ
====
# Milli Shamoro!