16/11/2025
ሥሉጥ ከተማ
በከተማ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን ሥሉጥ ማድረግ ወጪ ቆጣቢ ቀልጣፋ አገልግሎት ነዋሪዎች እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ በሥሉጥ ከተሞች ነዋሪዎች ዉል ለመስጠትና ለመቀበል በአካል መገኘት አይጠበቅባቸዉም፡፡ የንግድ ስራ ለመጀመር አብዛኛዉን ሂደት በአካል ለመቅረብ አይገደዱም፡፡ የመንግሥት ግዥ ሂደቶች አካላዊ ግንኙነቶችን በመቀነስ ወይም በአካል ሳይገኙ እንዲከዉኑ ያስችላል፡፡
ሥሉጥ ከተሞች አገልግሎታቸዉ ከዚህም በላይ ነዉ፡፡ ዘላቂ የከተማ ልማትን ያረጋግጣል፡፡ አረንጓዴ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት ይጠቅማሉ፡፡ እንዲሁም ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ያሻሽላሉ፡፡ ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር ከተማን ለመገንባት ሥሉጥ የከተማ መፍትሄዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸዉ፡፡ ሥሉጥ ከተሞች ህይወት እንዲኖራቸዉና የሰዉ ልጅ ህይወቱንና ስራዉን በረጋ መንፈስ እንዲመራ፣ ለአረንጓዴ ቦታና ለህዝብ ቦታ ልማቶች ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ፡፡
የከተሞች ሥሉጥ መሆን ምቹ የፈጠራ ሥነ ምህዳር ይፈጥራል፡፡ የዲጂታል ፈጠራን ያጎለብታል፡፡ የመደመር መንግሥት እሳቤን ያስፋፋል፡፡ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ኢንዱስትሪዎችን እድገት ያፋጥናል፡፡ በዚህም እዉቀት መር ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል፡፡
በአጠቃላይ ሥሉጥ ከተሞች በመረጃ የተደገፉ መፍትሄዎችን ይሰጣሉ፡፡ በዲጂታል ቴከኖሎጂና በኔትዎርክ በተገናኙ ሥርዓቶች ተጠቅመዉ የከተማ ልማት ራዕይን ዉጤታማ፣ ዘላቂና ሁሉን አካታች ያደርጋሉ፡፡ የነዋሪዎችን፣ የኩባንያዎችንና የማህበረሰቡን ፍላጎቶችንና ግቦች ለማሳካት የሚያስችል አቅም ይፈጥራሉ፡፡ ሥሉጥ ከተሞች ለቀጣይ ዘመን ዕድሎችና ተግዳሮቶች ዝግጁ የሆነ ከተማ ይፈጥራሉ፡፡ የዲጂታል ሽግግሩን እዉን በማድረግ፣ ኢኮኖሚዉ ከዲጂታል ኢኮኖሚ ወደ እዉቀት መር ኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያደርግ ያስችላሉ፡፡
ከተሞቻችንን በአዲሱ ዘመን እሳቤና ተግባር ማልማትና ፈጣን እድገት ማረጋገጥ አለብን፡፡ ያሉንን የመሰረተ ልማት አቅሞች አሟጠን መጠቀምና ኋላ በቀረንባቸዉ ፈጥኖ መልማት አለብን፡፡ ከተሞቻችን ከዲጂታል ዘመን እድል እንዲቋደሱ ከፈለግን በፍጥነት ሥሉጥ ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህም መሳካት የከተሞች አስተዳደር በመደመር መንግሥት ዕሳቤ መቃኘት አለበት፡፡
የመደመር መንግሥት ገጽ 238