27/06/2025
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ከራያ አላማጣ፣ አላማጣ ከተማ፣ ራያ ባላ፣ ኮረም ከተማ፣ ኦፍላ እና ዛታ ወረዳዎች ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች ከ1983 ጀምሮ በአያቶቻችን እና በአባቶቻችን ርስት መሬቱ የእኛ ነው ለቃችሁ ውጡ ስንባል ኖረናል ነው ያሉት። እኛ ባለርስቶቹ ግን ወጡ አላልናቸውም፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን ብለዋል።
የህውሐት ኃይል ከአንድ ዓመት በፊት ዳግም ወሮናል ያሉት ተሳታፊዎቹ ወደ ራያ ምድር ሲገባ በወረራ ነው፣ ይህ ሊነገራቸው ይገባል ብለዋል። በተፈናቃይ ስም ወረራ መፈጸሙን ገልጸዋል። በወረራ የገባው ታጣቂ ይውጣልን፣ በተፈናቃይ ስም የገባውም ተጣርቶ የሕዝብ ቅቡልነት እንንዲኖረው ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።
የህውሐት ኃይሎች አካባቢያችንን በድጋሚ በመውረር ግፍ እየፈጸሙብን፣ እየዘረፉን ነው ብለዋል። ልጆቻችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው በማለታችን ትምህርት እንዲቋረጥ ኾኗል ነው ያሉት።
የፌደራል እና የክልሉ መንግሥት መፍትሔ እንዲሠጧቸውም ጠይቀዋል። የደኅንነት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አንስተዋል።
ጥያቄያችን በሕግ አግባብ ዘላቂ መልስ እስከሚያገኝ ትምህርት ይጀመርልን፣ የጸጥታ ኃይሎች ደኅንነታችን ይጠብቁልን ያሉት ተሳታፊዎቹ የህወሐት ታጣቂ ቡድን ከአካባቢው እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም አንስተዋል። አካባቢው ተረጋግቶ ወደ ቤታችን መመለስ እንፈልጋለን ነው ያሉት።
የባዕዳን ተላላኪ የኾነው እና በስማችን የሚነግደው ጽንፈኛ ኃይል የማንነት ጥያቄያችን መልስ እንዲዘገይ ምክንያት ኾኗልና ድርጊቱን እናወግዛለን ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የተነሱ ጥያቄዎች እና ችግሮች በሚመለከታቸው መዋቅሮች መፍትሔ እንዲያገኙ የክልሉ መንግሥት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
የወሰን እና የማንነት ጥያቄው በዘላቂነት መልስ እንዲያገኝ ዋናው ተዋናይ ሕዝቡ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕዝቡ ሚናውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
በመጀመሪያ ዙር ከትግራይ ክልል ተመልሰው በሀገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ሰዎች ልየታ የገቡ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል መንግሥት እውቅና የተፈጸመ መኾኑንም ገልጸዋል። ከዚያ በኋላ የተፈጸመው ግን ህወሐት በወረራ መልክ የፈጸመው መኾኑን ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥት ተፈናቃዮች ይመለሱ ከማለቱ በፊት የክልሉ መንግሥት አጣርቶ የያዘው ቁጥር እና ተመለሱ የተባሉት ቁጥር ምጥጥን በሦስቱ አካላት የተጣራ ባለመኾኑ ቅዲሚያ መጣራት አለበት ነው ያሉት።
የህወሐት ታጣቂ ወረራ ሲፈጽም የተፈናቀሉ ወገኖች ሁኔታዎች እስከሚረጋጉ ድረስ ቆቦ ከተማ እንዲጠለሉ መደረጉንም ገልጸዋል። ነገሮች ሲስተካከሉ እና የደኅንነት ስጋት ሲቀረፍ ወደቤታቸው እንደሚመለሱም አንስተዋል።
ጉዳዩ ሰላማዊ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ የፌደራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥት እና ኮሚቴዎች በየድርሻቸው እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
"መንግሥት ዛሬን ብቻ ሳይኾን ነገን ታሳቢ አድርጎ እየሠራ ነው" ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ለተፈረሙ ውሎች ዋጋ የሚሰጥ እና ለዘላቂ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚጨነቅ መኾኑን ገልጸዋል። ለዘላቂ አብሮነት እንቅፋት ከሚሆኑ አካሄዶች መጠንቀቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።