
29/09/2025
በዞኑ ባህላዊ እሴቶች ሳይበረዙ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ
አርባ ምንጭ ፡ መስከረም 19 / 2018 ዓ.ም. (ጋሞ ቴሌቪዥን)
በጋሞ ዞን ባህላዊ እሴቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ
ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ደምሴ አድማሱ ገለጹ።
የጋሞ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ ዮ- ማስቃላ በዓል በዞኑ ካምባ ዙሪያ ወረዳ ባልታ ቀበሌ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ደምሴ አድማሱ እንዳሉት በዞኑ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በትኩረት እየተሠራ ነው።
ይህ ጥረት ባህላዊ ይዘታቸው ሳይበረዝ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
ከዞኑ 42 ደሬዎች አንዱ በሆነው ባልታ ቀበሌ የተከበረው የዮ ማስቃላ በዓል ህብረተሰቡ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አድምቆ ማክበሩን አስረድተዋል።
ይህም ልዩ ደስታን እንደፈጠረባቸው ዶክተር ደምሴ ተናግረዋል፡፡
አክውም በዓሉ በደመቁ ተከብሮ በሠላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካትም ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጋሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሀኪሜ አየለ በበኩላቸው የጋሞ ህዝብ ዘመን መለወጫ በዓል ያዘኑ የሚጽናኑበት፤ የተጣሉ የሚታረቁበትና የይቅርታ በዓል ነው ብለዋል፡፡
በዓሉም ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም የጥጋብና የደስታ በዓል መሆኑን አስረድተዋል።
አባቶቻቸውን የሚሰሙና የሚያከብሩ ወጣቶች የወጡት ከመሰል በአላት መሆኑን የሚስረዱት አቶ ሀኪሜ ወጣቶች ከአባቶቻቸው የወረሱት ባህል ሳይበረዝ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ ከዮ-ማስቃላ ክዋኔዎች አንዱ የሆነው የሽማግሌዎች ምርቃት በባህሉ መሠረት ኃላፊነት በተሰጣቸው የአገር ሽማግሌ የሚከወን ሲሆን "ፑስኬ" በመባል እንደሚታወቅ ተናግረዋል።
የሶፌ ስርዓት በባልታ መስቀል ከሚዘወተሩ ክዋኔዎች መካከል አንዱ እእደሆነም ጠቅሰዋል።
በሶፌ በዓመቱ ጋብቻ የፈጸሙ ሙሽሮች በባህላዊ አልባሳት ደምቀው ከዘመድ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙበትና ከማህበረሰቡ የሚቀላቀሉበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጋሞ ዱቡሻና ዱቡሻ ወጋን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዚሁ የዮ-ማስቃላ በዓል የካባ ዙሪያ ወረዳ ባልታ ቀበሌና አካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡