14/03/2026
Ayidde Cambalaalla! - አይዴ ጫምባላላ!!
Hawalle Sidaamu daga diru soorro Fichee-Cambalaallate ayyaanira keerunni iillishinke, yaanni ayyaanu kuni:- keerunniha, fayyimmaanniha hattono latishshunniha ikkankera wodaninni halcheemmo.
የዓለም እንቁ ሀብት ለሆነው የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም አደረሰ! አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።
የጥንት አባቶቻችን በዘመናት ዑደት ውስጥ ጠብቀው ያቆዩልን የፍቼ ጫምባላላ በዓልና በውስጡ ያሉ እሴቶች የዛሬው ትውልድ የሚደምቅበትና የሚኮራበት፣ ሀገራችና ህዝባችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብለው እንዲታዩ ያስቻለ ልዩ ሀብታችን ነው::
የፊቼ- ጫምበላላ በዓል የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል እንደመሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ በፍቅርና በይቅርታ ተሰባስበው፣ የበደለና የተበደለ በይቅርታ የሚተቃቀፍበት፣ ያለ ልዩነት ወገንና ቤተሰብ ተሰባስቦ በአንድነት ፈጣሪን የሚያመሰግኑበትና አዲሱ ዘመን የፍቅር፣ የተድላና የጤና እብዲሆንልን የሚለምኑበት የአብሮነት በዓል ነው::
ፊቼ ጫምባላላ ከአዲስ ዘመን መለወጫነቱ ባሻገር በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ሰብዓዊነት የሚጎላበት፣ ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚደረግበት፣ እንስሳት ክብር የሚያገኙበት፣ ሴቶችና ህፃናት በእኩልነት የሚሰባሰቡበትና ፍቅርና አብሮነት ጎልቶ የሚታይበት መሆኑ የዓለም የራሱ ሀብት አድርጎ በቅርስነት መዝግቦታል::
በየዓመቱ የሚከበረውን የፍቼ ጫምባላላ በዓል ለመታደም በርካታ የውጪና የሀገር ውስጥ እንግዶች፣ የብሔሩ ተወላጆችና ቱሪስቶች ወደ ከተማችን ሀዋሳ ይመጣሉ:: ከተማችን ሀዋሳም ከወትሮው በተለየ መልኩ እንግዶችን "ዳዎኤ ቡሹ" ብላ ለመቀበል አምራና ተሞሽራ ዝግጅቷን አጠናቃ የበዓሉን ታዳሚዎች እየተቀበለች ትገኛለች::
የከተማችን ነዋሪዎችም እንደሁልጊዜው ሁሉ ለእንግዶች መልካም አቀባበል በማድረግ ምቾት ተሰምቷቸው በዓሉን እንዲያከብሩ፣ በከተማችን ቆይተው እንዲዝናኑ የሲዳማን የባህል ምግብ አዘጋጅተው፣ ባህል አልባሳት ደምቀው በፍቅር ለመቀበል እየጠበቁ ይገኛሉ::
በመጨረሻም ሁላችሁንም ወደ ሀዋሳ በመምጣት የበዓሉ ታዳሚ እንድትሆኑ እየጋበዝኩ እንኳን ለሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል አደረሰን! አደረሳችሁ እያልኩ በዓሉ የሰላምና የጤና እንዲሆንልን እመኛለሁ::
መልካም የፍቼ ጫምባላላ በዓል ይሁንልን!
Dancha harro diro ikoke!!