
11/03/2025
ባህላችንን የማያውቁ አካላት ባህላችንን እየጣሱ ሲሉ የሲዳማ አባቶች ተናገሩ
የሲዳማ የባህል እና የሃገር ሽማግሌዎች ከሲዳማ ባህል ውጪ በሆነ መልኩ የሲዳማ ህዝብንም ሆነ ባህል በማይወክል መንገድ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን አወገዙ።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የሲዳማ ዘመን መለዋጫ (ፊቼ ጨምበላላ) በመጋቢት አጋማሽ በሲዳማ ክልል በሀዋሳ በደማቅ ሊከበር በቀን ተቆርጦለት እያለ በዓሉን ለማደብዘዝ እና ባህሉን ባልጠበቀ ስርዓት በሌለው መልኩ ከሰሞኑን በተለየዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የውሸት ወሬዎችን እና ግጭት እየሰበኩ ያሉ አካላትን የሲዳማ ሃገር ሽማግሌዎች ከባህል ያፈነገጡ ሲሉ ገልፀዋል።
የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት ዋጋ ከፍሎ ያገኘውን የክልልነት ጥያቄ መልስ ዋጋ ለማሳነስ የህዝቡን ሰላምና ልማት ለማደፍረስ እየሰሩ ያሉ አካላት ህዝባችንን የማይወክሉ ለግል ፍላጎታቸው እና ጥቅማቸው ብለው የበርካታውን ህዝባችንን ጥቅም እና ፍላጎት የትግል ዋጋ ለማሳነስ እየሄዱ ያሉበት አካሄድ ከሲዳማ ባህል እና ቱሪፍት አንፃር አስነዋሪ መሆኑን የሀገር አባቶች ገልፀዋል።
ሲዳማ የሁሉንም ህዝብ እና ብሔር ብሔረሰቦች በማዕቀፍ በሰላም እና በአብሮነት እየኖረ ያለ ትልቅ ህዝብ ሲሆን “ጥያቄውም መልሱም” በባህል በስርዓት የተቃኘ እንጂ በስድብ የሚታወቅ ባለመሆኑ ከሰሞኑን በዚህ ድርጊት የተሳተፉ እየተሳተፉ ያሉ አካላትን አባቶች አውግዘዋል።
ህዝባችንን ከመላው በክልሉ ውስጥ ሆነ ክልሉ ውጪም ከአጎራባች ህዝቦቻችን ከሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በሰላምና በደጋገፍ እየኖረ ያለ ህዝብ ሲሆን ይህንን የጠሉ አካላት የህዝባችንን ሰላም ለማደፍረስ ከጎረቤት እና አጎራባች ህዝቦቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ጥርጣሬ ውስጥ ለመክተት እየሰሩ መሆናቸው የገለፁት የሃገር ሽማግሌዎች እኝህ ሃይላት የሲዳማ ህዝብ ጠላት፥ የሲዳማ ባህል ጠላት፥ የሲዳማ ህዝብ ስርዓት ጠላት፥ የሲዳማ ህዝብ ሰላም ጠላት ናቸውም ሲሉ የሲዳማ አባቶች (አያንቶች) ገልፀዋል።
ከቀናት በኋላ የሚከበረውን የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ (ፊቼ ጨምበላላ) በዓልን በሰላም ለማክበር ህዝባችንን ከመንግስት ጋር እየሰራ ነው ያሉት የሃገር ሽማግሌዎች ሰላማችንን ባህላችንን ጠብቀን ስርዓታችንን አፅንተን እናከብራለን ብለዋል።
አክለውም በዚህ የውሸት ድርጊት እና ውሸቶች ተሳትፋችሁ የሲዳማ ህዝብ በማይወክል መንገድ ውስጥ ሆናችሁ የሲዳማ ሃላሌን (እውነትን) ተጣርሳችሁ ያላችሁ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡም ሲሉም አሳስበዋል።
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ የፊቼ ጨምበላላ በዓል አከባበር ዝግጅት አስመልክቶ ተገኙበት መድረክ ላይ የሃገር ሽማግሌዎች ይህንን መልዕክት አስተላልፈዋል።