11/10/2025
✍️ ጸሎት እንዴት ይጸለያል?
( በዲ/ን ቴዎድሮስ ዘለቀ )
➺ጸሎት ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋራ የሚነጋገራት ነገር ናት|ጸሎት ብሒል ተናግሮ ምስለ እግዚአብሔር እንዲል|፤
➛አንድም የተበደለ ድኃ ከንጉሥ እንዲጮህ ሰው ወደ ልዑል እግዚአብሔር የሚጮሃት ጩኸት ናት፤
➺ባለፈው እያመሰገነ፥ ለሚመጣው እየለመነ የሚኖርባት፤
➛እግዚአብሔርን አንድም ራሱን ደስ የሚያሰኝበትን ነገር ሽቶ ወደ እግዚአብሔር የሚጮሃት ጩኸት ናት፤
✍️ለሚጸልይ ሰው ብዙ ሥርዐታት አሉት።
፩. በእግሩ ቀጥ ብሎ መጸለይ ይገባዋል፤ "በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፥ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ፥ እጠብቃለሁም።" መዝ.5፥3።
፪. ወገብ ልቡናን በንጽህና ዝናር መታጠቅ ነው፤ "ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤" ሉቃ.12፥35 እንዲል።
፫. ፊትን ወደ ምሥራቅ መመለስ ነው፤ "በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል።" መዝ. 67፥33።
➛ከዚኽ ኹሉ ጋራ ወዲያና ወዲህ ማየትን፤ አንድም ልቡና ማባከንን መተው ይገባናል።
፬. አቲብ በአፅባዕት በአምሳለ መስቀል |ፊትን በትእምርተ መስቀል ማማተብ ነው|፤
➬ከላይ ወደ ታች|ትእምርተ ርደት ነው፦ ይኽም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር የመውረዱ ምሳሌ|፥
➬ከግራ ወደ ቀኝ|እኛን ከኃሣር ወደ ክብር፥ ከሲኦል ወደ ገነት የማውጣቱ ምሳሌ|፤
➣በጣት ፊትን ማማተብ አጋንንት ለማራቅ ነው። "እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።" ሉቃ.11፥20።
➥በትእምርተ መስቀል ፊትን ማማተብ፦
ሀ/. ፈጣሪ በመስቀሉ ድኅነተ ምዕመናንን ፈጽሞበታልና፤
ለ/. ዳግመኛም ስለኛ የተሰቀለ የቸርነቱን ነገር እናስብ ዘንድ ነው፤
ሐ/. ቅዱሳን ሐዋርያትም ረስጣ ፵ወ፱ እንዲኹም ሐዋርያት በመጀመሪያው ቀሌምንጦስ 49ኛው አንቀጽ፦ "ሰይጣን ከኛ ይርቅ ዘንድ በተረዳች ሃይማኖት ኹል ጊዜ ፊታችንን በመስቀል አምሳል እናማትብ ዘንድ፤ አጋንንት ከሚያመጡት ጉዳት እንድን ዘንድ ይኽን ምልክት አደረጉልን።
➲በትእምርተ መስቀል የሚያማትቡባቸው ጊዜያት፦
➦ጸሎት ሲጀመር፥
➦መስቀል፥ መስቀልን የሚያነሳ አንቀጽ ሲደርስ ነው።
፭. በፍርሃት፥ በረዓድ ኹኖ ጸሎቱን መጸለይ ነው።
➬የሚጸልየውም ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚሳብበት ይኹን፤ አፍ ንባብ ይነዳ፥ ልብ ጓዝ ያሰናዳ እንዲሉ።
፮. አስተብርኮ፥ ሰጊድ ነው። "... ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ፡ ተብሎ ተጽፎአልና፡ አለው።" ማቴ. 4፥10።
➛አንድም ወንጌል በምሴተ ሐሙስ እንደጸለየ፤ በጉልበቱ እንደተንበረከከ ይመሰክራል። "ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም፡—..." ሉቃ. 22፥41እንዲል።
✍️የሚሰገድባቸው ጊዜያት፦ ቁጥሩ በኛ ጉባዔ ተጽፏል። ሐተታ፦ ጊዜያቱ ሰባት የጸሎት ሰዓታት አሉ። የአንዱ ሰዓት 36 ሰጊድ ሲኾን የሰባቱ፦ 36x7= 252 ጊዜ ይሰገዳል። እንደ ጽናቱ መጠን 100, 200, 1000 ጨምሮ የሚሰግድ አለ።
➛የሚጸልይ ሰው በሚጸልይበት ጊዜ ሰጊድን ከሚያነሳ አንቀጽ ሲደርስ ለልዑል እግዚአብሔር ይስገድ። በአንድ ሰጊድ ከጀመረ በዚያው አንድ እየሰገደ መጨረስ፥ ሦስት ጊዜ እየሰገደ ከጀመረ ሰጊድ በሚልበት ኹሉ ሦስት፥ ሦስት ጊዜ እየሰገደ መጨረስ አለበት።
➬ጸሎቱን በጨረሰ ጊዜ እንዲህ ያድርግ በአንድ ጀምሮ እንደኾነ በአንድ ይጨርስ፤ አንዱ የአንድነት፥ ሦስቱ የሦስትነት ምሳሌ ነው።
✍️ከስግደት የሚከለክሉባቸው ጊዜያት፦
➾ሠለስቱ ምዕት በኒቅያ በጻፉት መጽሐፍ በ20ኛው አንቀጽ እሑድ፥ እሑድ፤ በባለሃምሳ አትስገዱ አሉ።
➾ዘኒቅያ 32ኛው አንቀጽ፦
➦ በጌታ በዓል፥
➦በእመቤታችን በዓል፣
➦ሥጋውን ደሙን ከተቀበሉ በኋላ አትስገዱ አሉ።
✍️ ስለምን እሑድ፥ እሑድ፤ በባለሃምሳ ስግደት ከለከለ ቢሉ፦
➥አክብሩ ያለውን ትእዛዝ ማፍረስ ነውና፤
➥አንድም በዚኽ ቀን ዕረፍተ ሥጋ አርፋችሁ ዕረፍተ ነፍስ ዕረፉበት ብሏል።
✍️ ስለምን በጌታ በዓል፥ በእመቤታችን በዓል ስግደት ከለከለ ቢሉ፦
➥በእመቤታችን ቃል ኪዳን በጌታ ካሳ አልዳንም ያሰኛልና፤
➲አንድም በዓል የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው። በዚህ ቀን ሲሰግዱ መዋል መንግሥተ ሰማያት ከገቡ በኋላ ኃጢኣት ሰርቶ ንስሓ መግባት አለ ያሰኛልና።
✍️ ስለምን ሥጋውን ደሙን ከተቀበሉ በኋላ መስገድ አይገባም አለ፤
➥ወዙ ይንጠፈጠፋልና፤
➥አንድም በሥጋ ወደሙ አልዳንም በትሩፋታችን ዳን ያሰኛልና።
✍️በጸሎት ጊዜ የሚገባስ ጣታችንን ዘርግተን፥ እጃችንን ማንሳት ነው።
➱"በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም ባርኩ።" መዝ.133፥2።
➱"እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች።" መዝ.142፥6
✍️ ዳግመኛም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ባስነሣው ጊዜ ወደ ሰማይ እንዳየ ዓይናችንን ወደ ሰማይ ማቅናት ነው።
➥"ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ፡— አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ።" ዮሐ.11፥41።
➥"ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ፡— ..." ዮሐ.17፥1-2።
👏የነግሁንና የመንፈቀ ሌሊቱን ጸሎት እጃቸውን ከታጠቡ በኋላ ይጸልዩ አለ።
➺ሰው ከተኛ ዝንየት አይጠፋምና፤ ወለእመ ኢረከቡ ማየ በውእቱ ጊዜ ይንፍሑ እደዊሆሙ ወይዕተቡ በምራቅ ዘይወጽእ እምአፉሆሙ|ያን ጊዜ ውኃ ባያገኙ እፍ ብለው ከአፋቸው በሚወጣው ምራቅ እጃቸውን አሻሽተው ያማትቡ|።
➦እመሰ ማየ ዮርዳኖስ ይወጽእ እም አፉከ|የዮርዳኖስ ውኃ ከአፍህ ይወጣልና|እንዲል።
➬ሚስት ያለችው ሰው ቢሆን ኹለቱም አንድ ጊዜ ይጸልዩ። ባለጸጋ ቢኾን እሱ ከአዳራሽ እሷ ከእልፍኝ፤ ድኃ ቢኾን እሱ ከጉበኑ እሷ ከማጀት ኹነው ይጸልዩ።
➬ሚስቱ ያላመነች|ከተጋቡ በኋላ በእምነት ባትመስለው| ብትኾን ግን ተለይቶ ብቻውን ይጸልይ።
➲በሩካቤ አንድ የኾኑ|ሩካቤ ፈጽመው ያደሩ| ሰዎች ከመጸለይ ወደ ኋላ አይበሉ።
➥ከውሽባ ቤት|ሻወር ቤት| ገብተን እንታጠብ አይበሉ።
➥ዘእንበለ ተሐጽቦ እድ ባሕቲቱ|እጃቸውን(ኃፍረተ ሥጋቸውን) ብቻ ይታጠቡ| እንጂ።
➲ዘር የወጣበትን ዘር የነጠበበትን አካል ይታጠቡ እንጂ፤ እስመ ሰብሳቦሙ ንጹህ ውእቱ|ሩካቤያቸው ንጹህ ነውና|።
➲"መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።" ዕብ.13፥4 እንዲል።
✍️ባስልዮስ በጻፈው መጽሐፍ በ28ኛዋ አንቀጽ ሳይበላ አስቀድሞ መጸለይ የሚገባ እግዚአብሔር የሚበላውን ምግብ ያበረክት ዘንድ፤ ሥራይ ቢኖርበት ያጠፋ ዘንድ ነው።
➾ከተበላ በኋላ መጸለይ የሚገባም እግዚአብሔር ሥጋን ከኃጢኣት ለመጠበቅ፤ ጤና ለማግኘት ምግቡን ከሰውነቶ ያስማማ ዘንድ ነው።
➬ካህናት ከሕዝቡ ጋራ ይጸልዩታል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ አባቱ አመልክቶ አምስቱን እንጀራ በባረካት ጊዜ ተቀምጦ እንደጸለየ ተቀምጠው ይጸልዩዋታል።
✍️መንገድ ሊነሡ የሚጸልዩት ጸሎት አለ።
➾"ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፥ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንም ተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፥ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።" ሐዋ.21፥5-6።
✍️መነኮሳት አሳጥረው ለይተው የሠሯት ጸሎት ናት።
➦ከደጅ የሚመጣ ፊቱን አማትቦ አቡነ ዘበሰማያት ደግሞ ይግባ፤
➦ከውስጥ የሚወጣው ፊቱን አማትቦ አቡነ ዘበሰማያት ደግሞ ይውጣ ብለው ሥርዐት ሰርተዋል።
👌ለምእመናን ኹሉ የታዘዘው ጸሎት ሰባት ጊዜያት ነው።
፩. መጀመሪያ ፀሐይ ሳይወጣ ከእንቅልፋቸው በነቁ ጊዜ ከመኝታቸው ተነሥተው በነግህ የሚጸልዩት ጸሎት ነው።
➥ጽልመተ ሌሊትን አርቀህ ብርሃነ መዓልትን ያመጣልን ሲሉ፤
➥አንድም የኹሉ አባቱ አዳም የተፈጠረበት ነውና።
➥አንድም ጌታ በጲላጦስ ፊት ቁሞ የተመረመረበት ጊዜ ነውና።
👏 እጃቸውን ከታጠቡ በኋላ ከተግባረ ሥጋ አስቀድመው መጸለይ ይገባል።
፪. ሦስት ሰዓት የሚጸልዩት ጸሎት ነው።
➥የኹሉ እናት ሔዋን የተፈጠረችበት፤
➥አንድም ዳንኤል የጸለየበት፤ "ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም።" ዳንኤል 6፥10 እንዲል።
➥አንድም እመቤታችን ብስራተ መልአክን ሰምታ ጌታችን የጸነሰችበት፤
➥አንድም ጌታ በጲላጦስ ፊት የተገረፈበት፤
➥አንድም በጽርሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበት ሰዓት ነውና።
፫. በ ፮ ሰዓት የሚጸለይ ጸሎት ነው።
➥በቀትር ጊዜ ዋዕየ ፀሐይ ይጸናል፥ ከናላ ላይ ይወድቃል፥ ሐሞት ይበተናል፥ ሰውነት ይዝላልና ያን ጊዜ አጋንንት ይሠለጥናሉና እንዳይሠለጥኑበት፤
➥አንድም አዳም የካደበት፤
➥ኄኖክ ቤተ መቅደስን ያጠነበት፤
➥ጌታ የተሰቀለበት ሰዓት ነውና።
፬. በ ፱ ሰዓት የሚጸልዩት ጸሎት ነው።
➥መላእክት የሰውን ምግባርና ጸሎት የሚያሳርጉበት ሰዓት ነውና፤
➥አንድም ጌታ ነፍሱን ከሥጋው የለየበት ሰዓት ነውና።
፭. በሠርክ የሚጸለይ ጸሎት ነው።
➥ሠርክ የምጽአት ምሳሌ፤
➥ሰው ሲሰራ ውሎ ዋጋውን የሚቀበል በሠርክ ነው። ምእመናንም ምግባር ትሩፋታቸው ሲሠሩት ኑረው ዋጋቸውን የሚያገኙ በምጽአት ነውና።
➥አንድም ጌታ ወደ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነውና።
፮. በንዋም ጊዜ|ከምሽቱ ፫ ሰዓት| የሚጸለይ ጸሎት፦ ጸሎተ ንዋም ነው።
➥ሥራኃ መዓልትን አሳልፈህ ዕረፍተ ሌሊትን ያመጣህልን ሲሉ፤
➥አንድም ጌታ የጸለየበት ሰዓት ነው፤
፯. ጸሎተ መንፈቀ ሌሊት|ከሌሊቱ ፮ ሰዓት| የሚጸለይ ጸሎት ነው።
➤እጃቸውን በውሀ ከታጠቡ በኋላ በመንፈቀ ሌሊት የሚጸለይ ጸሎት ነው።
➦ጌታ የተወለደበት፥ የተጠመቀበት፥ የተነሣበት፥ ዳግመኛም የሚመጣበት ሰዓት ነውና።
➦አንድም ጳውሎስ ጊዜ መንፈቀ ሌሊት እንዲል። "በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር።" ሐዋ.16፥25።