
15/03/2024
የኢትዮጵያ ቅጥረኛ ወታደር ከዩክሬን ጎን ሆኖ ሩሲያን እየተዋጋ እንደሆነ ተገለጸ
ሩሲያ ከዩክሬን ጎን የቆሙ ቅጥረኛ ወታደሮችን ማንነት ይፋ አድርጋለች
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ89 ሀገራት የተውጣጡ ከ13 ሺህ በላይ ቅጥረኛ ወታደሮች ለዩክሬን እየተዋጉ ነው ተብሏል
ኢትዮጵያዊው ቅጥረኛ ወታደር ከዩክሬን ጎን ሆኖ ሩሲያን እየተዋጋ እንደሆነ ተገለጸ።
ለአንድ ሳምንት በሚል የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሁለት ዓመት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጎን ቆመው እየተዋጉ ያሉ ቅጥረኛ ወታደሮችን ማንነት ይፋ አድርጋለች።
እንደ ሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር መረጃ ከሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ከዩክሬን ጎን ሆኖ ሩሲያን እየወጋ ይገኛል ተብሏል።
ይህ ኢትዮጵያዊ እስካሁን በህይወት እንዳለ የተገለጸ ሲሆን ወታደሩ ኢትዮጵያዊ ከመሆኑ ውጪ ማንነቱ ይፋ አልተደረገም።
በአጠቃላይ ይህ ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ89 ሀገራት የተውጣጡ 13 ሺህ 387 ቅጥረኛ ወታደሮች ከዩክሬን ጎን ተሰልፈዋል።
ከጠቅላላው ቅጥረኛ ወታደሮች ውስጥም 5 ሺህ 962 ያህሉ በሩሲያ ጦር መገደላቸው ተገልጿል።
ፖላንድ ቅጥረኛ ወታደሮችን በማዋጣት ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን 2 ሺህ 960 ዎቹ ተገድለዋል ተብሏል።
ከፖላንድ በመቀጠል አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጆርጂያ እና ብሪታንያ ብዙ ዜጎቻቸው ከዩክሬን ጎን የቆሙ በቅጥረኛ ወታደርነት የተመዘገቡ ሀገራት ናቸው።
ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 13 ሀገራት የተውጣጡ 249 ወታደሮች ከዩክሬን ጎን ሆነዋል የተባለ ሲሆን 103 ያህሉ መገደላቸው ተገልጿል።
ናይጀሪያ፣ አልጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ በአንጻራዊነት ብዙ ዜጎቻቸው ለዩክሬን በቅጥረኛ ወታደርነት የተመዘገቡባቸው ሀገራት ናቸው።
Al Ain Amharic አል ዐይን አማርኛ