
18/09/2025
የቀድሞው የወልድያ ከተማ ከንቲባ የነበሩት መሐመድ ያሲን ስለ #ግዕዝ ይሄን ብለዋል
አዎ ቋንቋ ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ይሞታል። ግእዝ ግን እንዲሞት ተፈረደበት እንጂ ራሱን አልገደለም‼️
#መቅድም
የግእዝ ትምህርትን በተመለከተ በ3 ተከታታይ ክፍሎች ያለኝን የግል አመለካከት መሰረት በማድረግ ባጋራሁት ፅሁፍ መነሻነት በውስጥ መስመር በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች እየደረሱኝ ይገኛል።
ይህ ከሆነ ዘንዳ ከዚህ በታች ካሰፈርኩት አመለካከት የተለየ አቋም ያለው ግለሰብ የፈለገውን ስያሜ ወይም ትችት ሊሰጥ ይችል ይሆናል። ይህንን ግን በራሱ ገፅ እንዲያደርገው ከወዲሁ እመክራለሁ።
#ማሳሰቢያ
📝 ይህንን አተያይ በጨዋ ደንብ በሐሳብ ለሚሞግቱ ትልቅ ክብር አለኝ። የሚሰጡት አመክኒዮም አሳማኝ ከሆነ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
🙈 ነገር ግን ለስድድብ፣ ለብሽሽቅ፣ ለዘለፋ ተብለው የሚሰጡ ትችቶችን መልስ ለመስጠት በሚል የማጠፋው ጊዜ አይኖረኝም።
❶ ያኔ በኢትዮጵያ በጥንት ዘመን ለ200 ዓመታት ገደማ የመንግስት የስራ ቋንቋ እና የህብረተሰቡ መግባቢያ ቋንቋ የነበረው ግእዝ፤
❷ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ ስነ ሃውልቶች የተሸከመው ግእዝ፤
❸ አያሌ ድርሳናት (ስለ ህክምና፣ ስለ ፍልስፍና፣ ስለ ማዕድናት፣ ስለ ፈዋሽ እፅዋት፣ ስለ ከዋክብት፣ ስለ አርኪዮሎጂ፣ ስለ ድንቅ ሐገራዊ ታሪኮች፣ ስለ ቀን ቆጠራ ወዘተ…) የተከተቡበት ግእዝ፤
❹ ለትግርኛና አማርኛ ቋንቋዎች መወለድ ስር ሁኖ ያገለገለው ግእዝ፤
❺ ሥርወ ቃላትን ለመመርመር ሰዋሰውን ለመለየት በእጅጉ የሚጠቅመው ግእዝ፤
❻ ሐገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት ዑደት ስፍር ቀምራ የራሷን አሃዝ ያደላደለችበት ግእዝ፤
❼ ሐገር እንጂ ብሄር የሌለው ብቸኛ ቋንቋ ግእዝ፤
❽ ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ እንድትኖር የቀድሞ ነገስታት ይመሩበት የነበረው የአስተዳደር ዘይቤ የተከተበበት ግእዝ፤
➒ ነጮች ጥቅሙን በቅጡ ተገንዝበው ኢትዮጵያውያንን በአስተማሪነት በመቅጠር በየዩኒቨርስቲዎቻቸው ዜጎቻቸውን የሚያስተምሩት ግእዝ ወዘተ…
እንዴትና ስለ ምን በጊዜ ሂደት የተናጋሪው ሰው ቁጥር ቀንሶ ከብሄራዊ ቋንቋነቱ ሊወርድ ቻለ❓ለግእዝ ቋንቋ መዳከም አቢይ ምክኒያት የአማርኛ መተካት ብቻ ሳይሆን ለቋንቋው የሚሰጠውና የተሰጠው ትኩረት መላላቱ የማያወላውል ምክኒያት መሆኑ ነው። በዚህም ተተኪው ትውልድ የትላንቱን ለዛሬ ማበርከት ያልቻ ሆኖ ይገኛል። በመሆኑም ትላንት የኢትዮጵያ የከፍታ መሰረት የነበረው ግእዝ ከነበረበት የብሔራዊና የውል ቋንቋነት ይቅርና ዛሬ ዛሬ ለእውቀት እንማረው መባል ሲጀመር የልዩነት ማዕከል እየተደረገ ይገኛል።
ግእዝ ከአሁኑ ዘመን ጋር እኩል ለመጓዝ የማይጠቅም ጊዜ ያለፈበት ያረጀ ቋንቋ ነውን❓አንዳንድ ሰዎች ከግእዝ ይልቅ እንግሊዝኛ፣ ቻይንኛ፣ ፈረንሳይኛ ወዘተ… ቢማሩ በእጅጉ የሚያተርፉ መሆኑን በመከራከሪያነት ሲያነሱ ይስተዋላል። እነዚህን መማር ጥቅሙ የላቀ መሆኑ አይካድም። ነገር ግን “አባቱን አያውቅ አያቱን ይናፍቅ” ያሰኛል።
በአሁኑ ዘመንስ ከሙታንነት ተቀስቅሶ በትውልዱ ላይ ሊጫን የተፈለገ የሃይማኖት መስበኪያስ ነውን❓በኔ ምልከታ ዛሬ ግእዝን ያወቀና የተማረ ሁሉ ነገረ ሀይማኖት ተረዳ ማለት አይደለም። ምክኒያቱም ቋንቋን ማወቅና መማር እምነትን የሚያስቀይር ቢሆን ኖሮ በእርግጥም ዛሬ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የግብጽ ኦርቶዶክስ አማኞች እስልምናን በተቀበሉ ነበር። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በግእዝ የተጻፉ ብዙ የእስልምና እምነት መፀሀፎች ሲኖሩ በአረብኛም የተከተቡ ብዙ የኦርቶዶክስ ድርሳናት ይገኛሉ። ስለሆነም ግእዝ ሃይማኖታዊ ቋንቋ አይደለም። It’s Part of Our LIVING History.
ዛሬስ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መሰጠቱን ደግፎ ነገር ግን በ1ኛ እና 2ተኛ ደረጃ ትም/ት ቤቶች እንዲሰጥ መወሰኑን በይፋ መቃወም የቋንቋውን ጠቃሚነት ካለመረዳት በሚመነጭ አመለካከት ይሆን❓ይህንን ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ሊገነዘቡት ያልቻሉት ነገር ቢኖር ጥያቄው በራሱ የግእዝን መማር አስፈላጊነት የሚጠቁም መሆኑን ነው። በተጨማሪም አሁን እየተጠቀምንበት ያለው አማርኛ ቋንቋ ሆሄያቱ የግእዝ ፊደላት ሁነው ሳለና በዚሁ ቃላት እየፃፉ ግእዝን ማስተማር አያስፈልግም ሲሉ እንደመስማት የሚያሳዝን ነገር ከወዴት ይገኝ ይሆን።
እንደ ጥቅል እነዚህንና ተያያዥ ተጠየቆችን ስንመለከት ኢትዮጵያዊያን በአለም ፊት አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት የሚናገሩለትን ማለትም ጥንታዊ የስርዓተ መንግስትና የስልጣኔ መነሻ፣ የራሷ ቋንቋና ፊደል፣ የቀን አቆጣጠር ወዘተ… ያላት ብርቅየ ሐገር ለመሆኗ መነሻ የሆነው ግእዝ በእርግጥም እንዲሞት ተፈረደበት እንጂ ራሱን አልገደለም የሚል ድምዳሜ እንዲያዝ ያደርጋል።
ዛሬም ዳግም እንዳይነሳ መቃብሩን አርቀው እየቆፈሩና በላዩ ላይ የልዩነት ቋጥኝና አለት እየጫኑበት ያሉት እሱ (ግእዝ) ባስገኘው የሚኮሩ ነገር ግን እሱን (ግእዝን) መማር በሚረግሙ አካላት ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። እነሆ ይፋዊ ጥቃትም ውግዘትም በግእዝ ላይ ተከፍቶበት ይገኛል። ለዚህም ነው በድጋሚ ግእዝ እንዲገደል ተወሰነበት እንጂ ራሱን አላጠፋም የምንለው።
#መደምደሚያ
ግእዝ ከአማርኛና ሌሎች ኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች ጋር ሲወዳደር ንጹህ ሴማዊ ቋንቋ ነው። በተጨማሪም ግእዝ በመላው የአፍሪካ ሐገራት ውስጥ የመጀመሪያውና ብቸኛ አፍሪካዊ የራሱን ፊደላት የያዘ ቋንቋ ሲሆን በዓለምም ላይ ዋናና የስልጣኔ አራማጅ ከሚባሉት ቋንቋዎች አንዱ ሁኖ ይገኛል።
ስለሆነም ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን በእርግጥም የምንኮራበት ከሆነ ለኩራታችን ምንጭ የነበረውን ግእዝ ከታች ጀምሮ ለማስተማር በትግበራ ላይ ስለሚገኝ በቀጣይ ስርዓተ ትምህርቱ እየዳበረ እንዲሄድ ለማሻሻያነት ግብዓት የሚሆኑ ጉዳዩችን በተደራጀ መንገድ ለሚመለከተው ተቋም በማቅረብ የዜግነት ግዴታዎን ሊወጡ ይገባል።
በመጨረሻም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሐገር፣ የታሪክ እና የቅርስ ባለአደራ ነው‼️