
02/07/2025
ኤርትራ ሠራዊቷን እያጠናከረች ነው ተባለ
| ኤርትራ ጦሯን እንደገና እያጠናከረች ነው ፤ ጎሮቤቶቿን በተለይም «ኢትዮጵያን እንዳትረጋጋ እያደረገች ነው» ሲል አንድ መንግስታዊ ያልሆነ የአሜሪካን የመብት ተመልካች ድርጅች አሳሰበ።
ዘ ሴንትሪ የተባለው ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው ዘገባ በጎርጎሮሳዊው 2018 የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የተነሳላት ኤርትራ፣ ጦር ሠራዊቷን እንደገና እየገነባች ፣መከላከያዋን እያጠናከረች ነው፤ ጎረቤቶቿም እንዳይረጋጉ ማድረጓን ቀጥላለች ብሏል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች በጎርጎሮሳዊው 2018 የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ የተመድ በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረዉን የጦር መሣሪያ ሽያጭና ግዢ ማዕቀብ አንስቷል።
የአሜሪካዉ ድርጅት ሁኔታው ካልተለወጠ ኤርትራ በዚህ ድርጊቷ ትቀጥላለች ተብሎ ይጠበቃል ሲልም አስጠንቅቋል።
ስለዘገባው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት AFP አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል «የተፈበረከ »ያሉትን ዘገባ «የሌላውን ጥፋት በኤርትራ ላይ ያላከከ» በማለት አጣጥለውታል።
አቶ የማነ በአካባቢው የተከሰተው አዲሱ ውጥረት «ሕገ ወጥ» ያሉት «ኢትዮጵያ ወደብና እና የባህር በር የማግኘት ፖሊሲዋን የማስተዋወቅዋ ውጤት ነው ብለዋል።
ጦርነቶችን በፋይናንስ የሚደግፉና በሙስና የሚገኝ ገንዘብ ጉዳይ የሚከታተለው ዘሴንተሪ ኤርትራ የሶማሊያ ጂሀዲስቶችን ትደግፋለች በሚል በጎርጎሮሳዊው 2009 ማዕቀብ ተጥሎባት እንደነበር አስታውሷል።
ከዚሁ ጋር በትግራዩ ጦርነት ወቅት ተፈጸሙ የተባሉ በደሎችንም ዘገባው ገምግሟል። የአፍሪቃ ኅብረት እንዳለው ኤርትራም ተሳትፋበታለች በሚባለው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ቢያንስ 600 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።
#ዶቼ ቨሌ