
25/07/2025
ሻደይ እና የወጣቶች ዝግጅት
ሰቆጣ: ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሻደይ በዋግ ኽምራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚከበሩ ባሕላዊ ጨዋታዎች መካከል ቀዳሚው ነው። በየዓመቱ ከነሐሴ 16-21 ባሉ የማርያም በዓላት ተብለው በሚጠሩት ቀናት ልጃገረዶች በነጻነት ያለከልካይ
"ሻደይ አበባየ ሻደይ
አሽከር ይሙት ይሙት ይላሉ የኔታ
አሽከር አይደለም ወይ የሚኾነው ጌታ
ሻደይ አበባየ ሻደይ"..እያሉ ያዜማሉ።
ወጣቶቹም የትዳር አጋርን ከመምረጥ ጀምሮ የሻደይ ተጫዋች ቆነጃጅትን በማጀብ በኩል ትልቅ ድርሻ አላቸው። በመኾኑም የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች የሻደይን በዓል በምን መልኩ እየጠበቁት ይገኛሉ ብለን ጠይቀናቸዋል።
ወጣት ዝናቡ በየነ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ሲኾን ሻደይን በድምቀት ለማክበር ከወዲሁ አስፈላጊ ባሕላዊ አልባሳት እና ጌጣጌጦችን አሟልቶ እየጠበቀ እንደሚገኝ አጫውቶናል።
ወጣቱ ትውልድ የውጭ ሀገር ፋሽን ተከታይ እየኾነ በመምጣቱ ለባሕላዊ አልባሳት ያላቸው ግምት እየቀነሰ መጥቷል ያለው ወጣት ዝናቡ የዋግ ሹሞቹን አለባበስ በጠበቀ መልኩ ሻደይን ለማክበር ወጣቶች ከወዲሁ አስፈላጊውን ቁሳቁስ እንዲያሟሉ አሳስቧል።
ሌላኛው በባሕላዊ የዋግ አለባበስ አሸብርቆ ያገኘነው ወጣት ዓለማየሁ ጥላሁን ሻደይን በአንድ አይነት አለባበስ እና በባሕላዊ አልባሳት ደምቀው ለመዋል በሰፈር ተደራጅተው አልባሳቱን እንዳሟሉ ጠቅሷል።
ሌሎችም ወጣቶች ለባሕሉ ቅድሚያ ሰጥተው መዘጋጀት እንደሚገባቸው የጠቆመው ወጣት ዓለማየሁ ሴቶቹ ላይ ያለው የባሕል ወዳድነት በአዎንታ የሚታይ ነው ብሏል።
በዓሉንም የዋግ ወጣቶች እና ቆነጃጅት በጉጉት እየጠበቁት እንደሚገኙ ነው የነገረን።
ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ መሰረት ያለው የሻደይ ጨዋታ ለዋግ ኽምራ ማኅበረሰብ የተለየ እንድምታ ያለው በዓል መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ኢዮብ ዘውዴ ገልጸዋል።
ይህ ሕዝባዊ የኾነውን የነጻነት በዓል በድምቀት እና በሰላማዊ መንገድ ለማክበር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ከወረዳ እስከ ቀበሌ በአግባቡ እየተሠራ እንደኾነ ነው ኀላፊው የገለጹት።
የአካባቢው ወጣቶች፣ ቆነጃጅት፣ ሕጻናት እና እናቶች ባሕሉ የፈቀደውን የባሕል አልባሳት አሟልተው በዓሉን እየጠበቁት እንደኾነ የተናገሩት አቶ ኢዮብ ሰቆጣ ከተማም እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች ብለዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!