
10/04/2025
"መቀመጥ አዲሱ ማጤስ እየሆነ ነው"
መቀመጥ አዲሱ ማጤስ እየሆነ ነው ይላል የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት፡፡ ሲጋራ ማጤስ ጤናን የሚጎዳውን ያህል አሁን የዘመናችን አዲሱ የጤና ጠንቅ ረዥም ሰዓት ስራ ላይ መቀመጥ ነው ብሏል ጥናቱ፡፡
እንደ አለም ጤና ድርጅት ጥናት በአማካኝ አንድ ሰው በቀን ለዘጠኝ ሰዓታት ተቀምጦ ያሳልፋል፡፡ መቀመጥ ሲባል በስራ ቦታ፣ በትራንስፖርት ላይ እንዲሁም ቤት ውስጥ ያለ እንቅስቃሴ የምናሳልፈውን ጊዜ እንደሚጨምር ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ ዝርዝር ውጤቶችን ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል፡፡ በቀን ከ6 ሰዓታት በላይ መቀመጥ ከ3 ሰዓት በታች ከሚቀመጡት ጋር ሲነጻጸር ሞት የማስከተል አደጋው ከጠቅላላው የሞት ቁጥር በ19% ከፍ ያለ ነው፡፡ ለረዥም ሰዓታት መቀመጥ የልብ በሽታን የሚያመጡ ክስተቶችን በ147% እንዲጨምሩ ያደርጋል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት ጥናት አሁን ላይ ከሚከሰቱ 10 ሞቶች ውስጥ አንዱ በመቀመጥ ብዛት እንደሚመጣ ይፋ አድርጓል፡፡
በቀን 30 ደቂቃ የአካል ብቃት ልምምድ እንኳን ረዥም ሰዓታት በመቀመጥ የተፈጠረውን ጉዳት ሙሉ ለሙሉ አያስወግድም፡፡ የእንቅስቃሴ መቀነስ የደም ፍሰትን ይቀንሳል፣ ትኩረት ማጣትን፣ የማስታወስ አቅምንና ስሜትን ይጎዳል ነው የሚለው ጥናቱ፡፡
ጥናቱ መፍትሄ ነው ያለው በ30 እና በ45 ደቂቃ ልዩነት እያስታወሱ እንቅስቃሴ ማድረግ እና በተቻለ መጠን ቆሞ መስራትን መለማመድ፣ ሁኔታው አመቺ ሲሆን እየተንቀሳቀሱ ስብሰባዎችን ማካሄድ፣ ሊፍት በመጠቀም ፈንታ በእግር ወለሎችን መውጣትና መውረድ፣ ከምግብ በኃላ የእግር ጉዞዎችን ማድረግ ይህንን የዘመናችንን የማጤስ ያህል እየጎዳን ያለውን መቀመጥን የምንዋጋበት መሳሪያ ነው ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት፡፡ “እንቅስቃሴ የሚደረገው በጂም ብቻ ነው፡፡’’ የሚል ሃሳብን በመተው በየቀኑ ትናንሽ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ለምሳሌ መኪናን ከስራ ቦታ ትንሽ ርቀት ላይ ማቆም እንኳን በሂደት ለውጥ ያመጣል ሲል ይመክራል፡፡