
21/04/2025
በአማራ ክልል ከ25 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ተገኝቷል።
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የአዋበል ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገድፍ ይታይህ በያዝነው በጀት ዓመት ከ10 የሽግግር ዘመናዊ ቀፎ ከ110 ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የንብ ማነብ ሥራቸውን ከግብርና ሥራቸው ጎን ለጎን በመሥራታቸው ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ እና ኑሯቸውንም መለወጥ እንደቻሉ አርሶ አደሩ ለአሚኮ ገልጸዋል።
በዞኑ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት ለገበያ መቅረቡንም የዞኑ የእንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የጽሕፈት ቤቱ የንብ ሃብት ባለሙያ ስማቸው ደምሴ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየለማ ያለው ደን ንብ በማነብ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በዚህም በያዝነው በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ማር ለማምረት ታቅዶ እስካሁን ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ማምረት ተችሏል።
የአማራ ክልል የእንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት በ2017 በጀት ዓመት 31 ሺህ 531 ቶን ማር ለማምረት አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል።
ክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥም 25 ሺህ 857 ቶን ማር ማምረት መቻሉ ነው የተገለጸው። ይህም ከዓመታዊ ዕቅዱ 82 በመቶ የሚኾነውን ይሸፍናል።
የጽሕፈት ቤቱ የንብ እና ሀር ልማት ባለሙያ ሙሐመድ ጌታሁን እንደገለጹት የተገኘው የማር ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ብልጫ አሳይቷል።
ባለፈው ዓመት በዚሁ ወቅት የተገኘው የማር ምርት 22 ሺህ ቶን እንደነበርም ባለሙያው አስታውሰዋል።
የማር ምርት በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚመረት የገለጹት ባለሙያው ሁለተኛው የምርት ሥብሠባ ሲጠናቀቅ በዓመት ከታቀደው በላይ ምርት ይሠበሠባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ይህ የተሻለ ውጤት የተገኘው 35 ሺህ 179 ባሕላዊ ቀፎዎችን ወደ ዘመናዊ ቀፎዎች በመቀየሩ፣ በሽግግር ቀፎ 29 ሺህ 171 ኅብረ ንቦችን የማዛወር ሥራ በመሠራቱ እና በፊት ከነበረው የኅብረ ንብ ብዛት 155 ሺህ የሚኾን በከፈላ የተገኘ አዲስ ኅብረ ንብ ቁጥር በመጨመሩ እንደኾነ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ የወቅቱ የዝናብ ስርጭት ምቹ መኾን፣ የደኖች መስፋፋት እና በመስኖ ልማቱ ንቦች የሚቀስሟቸው የአበባ ዛፎች በስፋት መኖር ለምርቱ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ባለሙያው ተናግረዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ለንብ አናቢዎች ሙያዊ ምክረ ሃሳብ በመስጠት፣ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች በመገኘት ድጋፍ በማድረግ፣ በተለያዩ መድረኮች እና ፕሮጀክቶች ሥልጠናዎችን በመስጠት እና ጥራቱን የጠበቀ ዘመናዊ ቀፎ ገዝተው እንዲጠቀሙ የማመቻቸት ሥራ በመሥራት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉንም አብራርተዋል።
በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥም ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ለአምራች አርሶ አደሮች ሙያዊ እገዛ እየተደረገ መኾኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን