
24/08/2025
በክልሉ ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በቅንጅት በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል
ባህር ዳር፤ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ።
በአማራ ክልል የተቋቋመው የፀረ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ቁጥጥር ጥምር ግብረ ኃይል የወንጀል ጉዳዮች ክትትል ቴክኒክ ኮሚቴ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ አያሌው አባተ (ዶ/ር) በመደረኩ እንደገለጹት በክልሉ ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።
ግብረ ሀይሉ ከፌደራልና ከክልሉ የተውጣጡ አካላት እንዳሉበት ገልጸው፣ በ2017 በጀት ዓመት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል ትርጉም ያለው ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
ይህም በኢኮኖሚ ወንጀል ዘርፍ ሊፈፀሙ የታቀዱ ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከልና ምርመራን በተገቢው መንገድ በመምራት ለቀረቡ የወንጀል ክሶች ውሳኔ ለመስጠት ማስቻሉንም ጠቁመዋል።
ጥምር ግብረ ኃይሉ ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባከናወናቸው ተግባራት ውጤት መመዝገቡንም አያሌው (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
በቢሮው የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሻግሬ ባቀረቡት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በበጀት ዓመቱ ለጤና ጎጂ የሆኑና ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ምግብና ምግብ ነክ ዕቃዎች እንዲወገዱ መደረጉን ገልጸዋል።
ለክልሉ ዐቃቤ ህግ፣ ለፌዴራል ፍትህና ገቢዎች ሚኒስቴር ዐቃቤ ህግ ተልከው ክስ ከተመሰረተባቸው 998 መዝገቦች ለ311ዱ የፍርድ ውሳኔ መሰጠቱንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በተጭበረበረ መንገድ መንግስት እንዲከፍል የተጠየቀ ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ጥምር ግብረ ኃይሉ በቅንጅት ባከናወነው ስራ ለማዳን ተችሏል ብለዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈንታው ፈጠነ በበኩላቸው እንዳሉት ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተደረገ የተቀናጀ ጥረት 104 ሺህ 167 ሊትር ነዳጅ ተይዟል።
እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቁም እንስሳት እና የኤክስፖርት ምርቶች በህገወጥ መንገድ ወደጎረቤት ሃገር ሊሻገሩ ሲል በጥምር ግብር ኃይሉ ክትትል መያዛቸውን ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ህገወጥነትን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ የሚጠናከርበት ነው ሲሉም አመልክተዋል።
ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል ከሌሎች የፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ናቸው።
በመድረኩ የክልሉ ፍትህ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ንግድና ገበያ ልማት፣ ጤና ቢሮ፣ ጉምሩክ ኮሚሽንና ገቢዎችን ጨምሮ የ13 የግብረ ኃይሉ አባል ተቋማት አመራሮች ተሳትፈዋል።
#ኢዜአ