አሚኮ በኲር/AMECO BEKUR

አሚኮ በኲር/AMECO BEKUR በኲር
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የምትዘጋጅ ሳምንታዊ የቤተሰብ ጋዜጣ

የመስከረም  5 -1-2018
17/09/2025

የመስከረም 5 -1-2018

“ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታህሳስየማን ሆድ ይችላል እስከዚያው  ድረስ”የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትምበዚህ ሀገርኛ ግጥም ውስጥ ያለው የጉደል ልመና እና እስከዚያው አልችልም ሃሳብ ...
17/09/2025

“ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታህሳስ
የማን ሆድ ይችላል እስከዚያው ድረስ”
የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

በዚህ ሀገርኛ ግጥም ውስጥ ያለው የጉደል ልመና እና እስከዚያው አልችልም ሃሳብ ዝም ብሎ ቤት የመምታት ዝም ብሎ ግጥም የመግጠም ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ በአንዱ የውሃ ሙላት ወቅት ሰኔ ወይም ሐምሌ አሊያም ነሀሴ የአባይ ሞልቶ አላሻግር ባለ የሆነ አንድ ውሽንንፍራም ቀን የተጻፈ ናፍቆት ያናወዘው ናፋቂ ወንዙ ዳር ቁጭ ብሎ የጻፈው ግጥም ብቻም አይደል፡፡ ይህ ግጥም እንዳሰበው ካሰበው ለመድረስ ያልቻለ ናፋቂ ወንዙ ዳር ቁጭ ብሎ መች ትጎድላለህ ብሎ ደጅ የሚጠና ትግስት አልባ ናፋቂ የጻፈውም አይደለም፡፡

በዚህ ግጥም ውስጥ አንድ ሰው አይደለም የመሸበት አንድ ሰው አይደለም የናፈቀ፤ አንድሰው ብቻ አይደለም እስኪጎድል የሚጠብቅ፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ ትውልድ ነው የጠበቀው፡፡ ይህ ጥያቄ የአንድ ሰው ሳይሆን የትውልድ ጥያቄ ነው፡፡ ዓባይን እንደ አንድ ሰው የጠየቀው አንድ ሰው ሳይሆን ትውልድ ነው፡፡
በዓባይ ውሃ ሙላት የተመሰለ ለዘመናት የተጠራቀመ ችግርና መከራ ነው፡፡ እስኪጎድል እንደሚያስጨንቅ ውሃ ሙላት ችግርም እስኪያልፍ እንደዚያው ነው፡፡ የማያልፍ የሚመስል ቀን ያልፋል፤ ውሃ ሙላቱም ይጎድላል-ሰውም ወደናፈቀው ይሻገራል፡፡ ከዘመድም ጋር ይገናኛል፤ ደስም ይለዋል፡፡

ይህንን የትውልድ እንጉርጉሮ መሻገር በናፈቀው መንገደኛ አሳቦ ትውልድ ሲያንጎራጉረው ዘመናትን ያስቆጠርንበት የአባይ እንቅፋትነት በትውልድ ቅብብሎሽና በትውልድ ትብብር ዛሬ ሁሉንም ሊክስ ወደእንጀራነት ተቀይሯል፡፡ አሁን “ዓባይ እንደሁሌው ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል ” የሚለው አሽሙርን ዛሬ አባይ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሊሰጥ በተንጣለለው የሀገሩ አድባር መክተሙን እያዬ አይደግመውም፡፡

በሕይወትም እንዲሁ ነው፤ አንዳንድ ከባድ ቀን ማቅ ለብሶ በማልቀስና ቁጭ ብሎ በመጠበቅ አያልፍም፡፡ አንዳንዳን ችግር በመሸሽና በሌሎች በማሳበብ፣ አንዳንዱን ራስን በመውቀስ፣ አንዳንዱን ደግሞ እንደማያልፍ ራስን በማስነፍ ካሉበት ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡
በወቅት መፈራረቅ ተፈጥሮ እንደሚቀየረው ሁሉ ተፈጥሮ ደስታና ሀዘንን የምንሸከምበት ትክሻና የምንወጣበትን ዘዴም አብራ ለግሳናለች፡፡ እንደወቅት መፈራረቅ ደስታና ሀዘንም ይፈራረቃል፤ ደስታው ዘላለማዊ አይደለም- ሀዘንም እንዲሁ፡፡

ስለዓባይ የነበረን ቁዘማና ተስፋ መቁረጥ በትውልድ ብርቱ ልፋትና ትብብር ተቀይሯል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የዜጎች ተባብሮ መስራትና ታሪክ የመቀየር ፍላጎት በተግባር የታየበት ነው፡፡ እንደህዝብ በአንድ መቆምና መተባበር፤ አይቻልም የሚልን የሰነፍ ሃሳብ ሰርቶ መቀየር በሚችል ብርቱ ክንድ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አስረኛ የሆነውን ታላቅ ግድብ ገንብቶ የኢትዮጵያውያንን ታላቅነት ዳግም የመለሰ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

ይህን መከወን መቻል ዝም ብሎ ግድብ ከመገንባትና ከማጠናቀቅ ሃይልም ከማመንጨት በላይ ነው፡፡ የዚህ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ከዚህም በላይ የመስራትና የመጨረስ አቅም እንደለን ማሳያ ነው፡፡
የዓባይን ወንዝ ጥቅም ላይ መዋል ያየ ትውልድ ላለፈው ሳይሆን ለመጪውም በአንድነትና በጋራ እንዲሁም በስራና ተስፋ ባለመቁረጥ ያሰበውን ያሳካ ዘንድ የሕዳሴው ግድብ ተገንብቶ መጠናቀቅ ለትውልድ እንደ አብነት ነው፡፡

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

የመስከረም 5 ቀን 2018
15/09/2025

የመስከረም 5 ቀን 2018

ካናዳየመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትምየበርካታ ሀገራት ዜጎች መኖሪያቸው አድርገዋታል። ከዓለማችን ሀገራት መካከል ከሩሲያ በመቀጠል በስፋቷ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ለዛሬው ሽርሽር መዳ...
15/09/2025

ካናዳ
የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

የበርካታ ሀገራት ዜጎች መኖሪያቸው አድርገዋታል። ከዓለማችን ሀገራት መካከል ከሩሲያ በመቀጠል በስፋቷ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ለዛሬው ሽርሽር መዳረሻ ያደረግናት -ካናዳ።
በሰሜን አሜሪካ አህጉር የምትገኘው ካናዳ፣ በሰሜን የአርክቲክ ውቅያኖስ፣ በደቡብ የአሜሪካ ግዛት(United States) ጋር ረጅም ድንበር ትጋራለች። በምሥራቅ አትላንቲክ፣ በምዕራብ ደግሞ ፓስፊክ ውቅያኖስን ታዋስናለች።
ካናዳ 10 ክፍለ ግዛቶች(Provinces) እና ሦስት ግዛቶች(Territories) አሏት። እያንዳንዳቸው የራሳቸው አስተዳደር አላቸው።

ካናዳ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት አላት። የኢትዮጵያን ዘጠኝ እጥፍ እንደማለት ነው። በሕዝብ ብዛት ግን ከእኛ በሦስት እጥፍ ታንሳለች። እ.አ.አ የ2024 ትንበያ እንደሚያመላክተው ከ40 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርባታል።
ካናዳ ፌዴራላዊ ፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ እና ሕገ መንግሥታዊ ንጉሣዊ የመንግሥት አስተዳደርን ትከተላለች። የእንግሊዝ ንጉሠ ነገሥት የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ የመንግሥት መሪ ናቸው።

የካናዳ የፖለቲካ ሥርዓት በመድብለ ፓርቲ መዋቅር ተለይቶ የሚታወቅ ነው። ሊበራል ፓርቲ እና ወግ አጥባቂው ፓርቲ ሁለቱም የሀገሪቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።
ካናዳ በፈረንሳይ እና እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ቆይታለች። እ.አ.አ ከ1982 ወዲህ ግን ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ግዛት ነፃ መሆኗን አውጃለች። አሁንም ድረስ ግን የእንግሊዝ ንጉሣዊ አገዛዝ አካል ሆና ቀጥላለች።

ከስፋቷ አንፃር ሰው የሚኖርበት የሀገሪቷ ክፍል 10 ከመቶው ብቻ ነው። 90 ከመቶው የካናዳ መሬት በጫካ፣ በተራራ፣ በወንዝ፤ ከምንም በላይ በሐይቆች የተሸፈነ ነው። ሐይቆች ዘጠኝ ከመቶውን የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት ይይዛሉ። ዓለማችን ላይ ከሚገኙ ሐይቆች 60 ከመቶ የሚሆኑት መገኛቸው ካናዳ ናት። ሁለት ሚሊዮን ሐይቆች አሏት። ከዓለማችን የባሕር ዳርቻዎች ውስጥም 57 ከመቶዎቹ የሚገኙት በካናዳ ነው።

በስፋቷ ምክንያት ስድስት የሰዓት አቆጣጠር ዞኖችን ትጠቀማለች። እዚያው ካናዳ አንዱ ከተማ ውስጥ ሆነው ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሲሆን ሌላው ከተማ ላይ አስራ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ይሆናል ማለት ነው።
የካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ ትባላለች። እ.አ.አ በ1857 ነበር ለዋና ከተማነት በንግሥት ቪክቶሪያ የተመረጠችው። በፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል መገኘቷም ለመመረጧ ምክንያት መሆኑ ይገለጻል። ኦታዋ የሻዋርማ/የደሮ አሮስቶ/ ዋና መገኛም ናት። በካናዳ ከሚገኙ ብርዳማ ከተሞችም አንዷ ናት።

ቶሮንቶ ደግሞ የካናዳ ትልቋ ከተማ ናት። ከሀገር አቀፉ ኢኮኖሚ 20 ከመቶውን ታመነጫለች። ቶሮንቶ እና ግሬተር ቶሮንቶ በመባልም በሁለት ትከፈላለች። ቶሮንቶ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ፣ ግሬተር ቶሮንቶ ደግሞ ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ነዋሪዎች አሏቸው። ሲኤን ከሚባለው ታወር በመውጣት ቶሮንቶን ሙሉ በሙሉ ቁልቁል መመልከት ይቻላል። የቶሮንቶ የምድር ውስጥ ከተማ በመባል የሚገለጽ የ30 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የምድር ውስጥ መንገድም አላት። መንገድ ብቻ አይደለም፤ 1200 ሱቆች አሉት። ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የገበያ ማዕከላት፣ የችርቻሮ ሱቆች፣ … በዚህ የምድር ውስጥ መንገድ ፈልገው የሚያጡት ነገር የለም። የከተማዋን የተለያዩ ክፍሎች እና የባቡር መስመሮችንም ያገናኛል።

ሞንትሪያል የካናዳ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ናት። በሞንትሪያል ክረምቱ በጣም ይከብዳል። ብርዱን ለማቅለል ታስቦም ልክ እንደ ቶሮንቶ ሁሉ የ33 ኪሎ ሜትር የምድር ውስጥ መንገድ ተገንብቷል። ሌላኛዋ የካናዳ ከተማ ቫንኩቨር ደግሞ ዝናብ የማያጣት ናት። በተለይ ከታህሳስ እስከ ሚያዚያ ባለው ጊዜ ጫን ይላል። ከፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ የምትገኘው ቫንኩቨር ዓለማችን ላይ ለኑሮ ምቹ ከሚባሉ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ታጥታ አታውቅም። የተቃርኖ ከተማም ናት። ቢሊየነሩ እና ጎዳና ተዳዳሪው ይኖሩባታል። ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እና የተፈጥሮ ፏፏቴዎችም መገኛ ናት።

ካናዳ ተገኝቶ ኒያግራን ሳያዩ መመለስ “ወንጀል ከመፈጸም አይተናነስም” ይባልለታል። ኒያግራ በውበቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ከዓለማችን ትላልቅ ፏፏቴዎች አንዱ ነው። በአሜሪካ እና ካናዳ ድንበር ላይ ይገኛል። ለጉብኝት በመርከብ የ20 ደቂቃ የፏፏቴ መሃል ጉዞ ማድረግ ይቻላል። 14 ሚሊዮን ቱሪስቶችም በየዓመቱ ይጎበኙታል። በፏፏቴው አቅራቢያ የምትገኘው የኒያግራ ከተማም የ90 ሺህ ሰዎች መኖሪያ ናት። የምትተዳደረውም ከቱሪስቶች በሚገኝ ገቢ ነው።

በርካታ የዱር ሃብት፣ ተራራማ ስፍራዎች እና ልዩ ልዩ ውበትን የተላበሱ መልካምድሮች፣ ከተፈጥሮ ለካናዳ የተሰጡ በረከቶች ናቸው። በመሆኑም 11 የተፈጥሮ እና አንድ የባሕላዊና ተፈጥሮ ቅይጥ በድምሩ 12 የመስህብ ሃብቶችን በዩኔስኮ አስመዝግባለች። የተፈጥሮ ውበትን እና የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ ተብለው ስምንት ታላላቅ ብሔራዊ ፓርኮች በካናዳ ተቋቁመዋል።

የተፈጥሮ ሃብቶቿ ተወዳጅ ጉዞዎችን ለማድረግ፣ ለበረዶ ላይ መንሸራተት ስፖርት፣ ለብስክሌት ግልቢያ፣ የተለያዩ አዋፋትን እና የእንስሳት ዝርያዎች ለመመልከት እንዲሁም ለተፈጥሮ ማረፊያነት ያገለግላሉ። የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብም የቱሪዝም ገቢን ያመነጫሉ።

ካናዳን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስጠሯት ነገሮች አንዱ የትምህርት ስርዓቷ ነው። እድሜያቸው ከ25 እስከ 64 ከሚሆኑት ውስጥ 57 ከመቶዎቹ ከኮሌጅ ወይንም ከዮኒቨርሲቲ የተመረቁ ናቸው። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት ያስቀምጣታል። 81 ከመቶ ዜጎቿ የሁለተኛ ደረጃ፣ 99 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ የቀለም ትምህርት ወስደዋል።

በካናዳ ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው ትምህርት በነፃ ይሰጣል። መክፈል አለብኝ ላለም የግል ትምህርት ቤቶች አሉ። ሆኖም ግን 93 ከመቶ ካናዳውያን ልጆቻቸውን በመንግሥት ትምህርት ቤት ያስተምራሉ።

ከሌሎች ሀገራት በተለዬ ካናዳ በፌደራል ደረጃ የትምህርት ሚኒስቴር የላትም። የትምህርት ፖሊሲውም፣ ካሪኩለሙም፣ በጀቱም የሚመራው በግዛቶች ነው። እናም ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላው ግዛት ሲቀይሩ የትምህርት ሥርዓቱ አብሮ ሊቀየር ይችላል። በአብዛኛዎቹ የካናዳ ግዛቶች ለምሳሌ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚጠናቀቀው 12ኛ ክፍል ላይ ነው። በኩቤክ ግዛት ግን አንድ ቀንሶ 11ኛ ክፍል ላይ ያልቃል። ግዛቶች የዚህን ያህል መብት አላቸው።

ካናዳ መጀመሪያ በፈረንሳይ ቀጥሎ በእንግሊዝ ቅኝ በመገዛቷ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ይፋ የሥራ ቋንቋዎቿ ናቸው። ይህ በትምህርት ሥርዓቱም ላይ ይንጸባረቃል። እንደየሚኖሩበት ግዛት አንዱን ቋንቋ መርጠው መማር ይችላሉ። ሆኖም በእንግሊዝኛ የሚማሩ ፈረንሳይኛ፣ በፈረንሳይኛ የሚማሩም እንግሊዝኛ ተጨማሪ የቋንቋ ትምህርት ሆኖ ይሰጣቸዋል።
ካናዳ መምህርነት የሚከበርባት ሃገር ናት። መምህር ሆኖ ለመቀጠርም፣ ለመቀጠልም ከፍተኛ ብቃት ይጠይቃል። መምህራን በየአምስት ዓመቱ የብቃት ፈተና ይሰጣቸዋል። ተገቢውን ክብር እና ጥቅማጥቅምም እንዲያገኙ ይደረጋል።

ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በካናዳ አይታወቅም። ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ውጤት ብቻውን በቂ ነው። የዚህ ጽሑፍ መጠናቀቂያም እዚህ ላይ ሆኗል፤ ቸር ይግጠመን።
ምንጭ፦ canada.ca፣ am.al.ain.com፣ statcan.gc.ca፣ ceochronicles፣ breathelife2030.org፣ gustice.gc.ca

አጭር እውነታ

ካናዳ
• ከዓለማችን ሀገራት መካከል ከሩሲያ በመቀጠል በስፋቷ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
• ካናዳ 10 ክፍለ ግዛቶች(Provinces) እና ሦስት ግዛቶች(Territories) አሏት።
• ካናዳ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት አላት።
• ካናዳ በፈረንሳይ እና እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ቆይታለች።
• ከስፋቷ አንፃር ሰው የሚኖርበት የሀገሪቷ ክፍል 10 ከመቶው ብቻ ነው።
• 90 ከመቶው የካናዳ መሬት በጫካ፣ በተራራ፣ በወንዝ፤ ከምንም በላይ በሐይቆች የተሸፈነ ነው።
• ሐይቆች ዘጠኝ ከመቶውን የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት ይይዛሉ።
• በስፋቷ ምክንያት ስድስት የሰዓት አቆጣጠር ዞኖችን ትጠቀማለች።
• የካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ ትባላለች።
• ቶሮንቶ ደግሞ የካናዳ ትልቋ ከተማ ናት።
• ካናዳን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስጠሯት ነገሮች አንዱ የትምህርት ስርዓቷ ነው።
• ካናዳ መምህርነት የሚከበርባት ሃገር ናት።

(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

“ኢትዮጵያዊያን አይበገሬ ናቸው!” - ፔትሮ ሳሊኒየመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትምታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም የምረቃ ሥርዓ ተበስሯል፤ በወቅቱ ንግግር ...
15/09/2025

“ኢትዮጵያዊያን አይበገሬ ናቸው!” - ፔትሮ ሳሊኒ
የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም የምረቃ ሥርዓ ተበስሯል፤ በወቅቱ ንግግር ያደረጉት የጣሊያኑ ሳሊኒ (ዊ ቢውልድ) ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ ኢትዮጵያዊያንን ኤበገሬ ሲሉ ነው ያወደሷቸው::
የግድቡን መጠናቀቅ በተመለከተ ሲናገሩም “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ሆነ። የእኔ እና የኢትዮጵያ ሕልማችን እውን ሆነ። ከዚህ በላይ ምን የሚያኮራ ስኬት ይኖራል!” ነው ያሉት።

“የግድቡ ፕሮጀክት ደኅንነት የነበረው ፕሮጄክት መሆኑን ያነሱት ሳሊኒ ታላላቅ ስኬቶች ዋጋ እንደሚከፈልባቸው ሁሉ በግድቡ ግንባታ ሂደትም የሰው ዋጋ እንደተከፈለበት አክለዋል። ለአብትም በግንባ ሂደቱ 33 የድርጅቱ ሠራተኞች በመንገድ አደጋ እና በሌሎች ምክንያቶች ሕይወታቸውን እንዳጡ አንስተዋል።

25 ሺህ ወጣቶች በሥራ ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደተሰጣቸው በማሳት ይህም በቀጣይ ለኢትዮጵያ መሠረታዊ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ፔትሮ ሳሊኒ የግድቡን መሠረት ከጣሉት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በቅርበት መሥራታቸውን ተናግረዋል። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም “’ለሀገሬ ሕልም አለኝ፤ የተትረፈረፈ የኃይል ሉዓላዊነት። ዓባይ ላይ ፕሮጀክት ልትነድፍልኝ ትችላለህ? በፍጥነት ሥራው አለኝ” እንዳሏቸው ገልፀዋል።

በግድብ ግንባታ እርሳቸው እና ቤተሰባቸው የቆዬ ትስስር እንዳቸው የተናገሩት ሳሊኒ ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ በብዙ ፈተና ውስጥ ተከባ እንደገነባች ነው የጠቀሱት።
“ሀገሪቱ ይህንን ግድብ እንድትገነባ ማንም አልፈለገም። ማንም ገንዘብ ለማቅረብ አልፈለገም። ብዙ ፖለቲካዊ ጉዳዮች፤ ብዙ ችግሮች ነበሩ፤ መፍትሔው ቀላል አልነበረም። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ችግርን አይፈሩም። አይበገሬዎች ናቸው። ችግር እና ጠላት ሲገጥማቸው አንድነታቸው ይጠብቃል፤ ጥረታቸውንም በእጥፍ ይጨምራሉ:: እናም ማግኘት ያለባቸውን ያገኛሉ” በማት ነው ያደነቁት፡፡

(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

ስለ ግድቡ የሀገራት መሪዎች ምን አሉ?የመስከረም 5 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትምበአፍሪካ ግዙፉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም የፍጻሜው ብሥራት ተነግሮ ተመርቋል።...
15/09/2025

ስለ ግድቡ የሀገራት መሪዎች ምን አሉ?
የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

በአፍሪካ ግዙፉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም የፍጻሜው ብሥራት ተነግሮ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል። የኬንያ፣ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የቤርባዶስ መሪዎችን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካ ኩራት፣ ለቀጣናው ታሪካዊ ቀን፣ ለአህጉሪቱ ራስን የመቻል ማሳያ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት። የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ "ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካ የራሷን መዳረሻ የመወሰን አቅም እንዳላት ያሳየ ነው" ብለዋል። የምረቃ ሥርዓቱን በፕሬዚዳንቱ እና በሀገሪቱ ስቴት ሀውስ ትስስር ገጾች በቀጥታ ተሰራጭቷል።

በአፍሪካ በአሁኑ ወቅት ከ600 ሚሊየን በላይ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንደማያገኙ ያነሱት ፕሬዚዳንት ሩቶ ይህም በአህጉሪቱ ልማት ላይ እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል።
"ግድቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕሮጀከት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካ መገለጫ ነው"ም ብለዋል። እ.አ.አ በ2022 ኬንያ ከኢትዮጵያ ለ25 ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት መፈራረሟን አስታውሰው 200 ሜጋ ዋት እየገዛች ስለመሆኑ ነው የጠቆሙት።
ከታለቁ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ለማግኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር መነጋገራቸውንና ሌሎች ውይይቶች እንደሚኖሩም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ሩቶ በመጨረሻም "የሕዳሴው ግድብ መቶ በመቶ በኢትዮጵያውያን መሠራቱ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በራስ አቅም መሥራት እንደምንችል ያሳየ ነው" ብለዋል፤ አካባቢውን ለመለወጥም አብሮ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ በበኩላቸው "ቀኑ ለመላው የቀጣናው ሕዝብ ታሪካዊ ነው" በማለት ነው የግድቡን መመረቅ የገለጹት። ፕሬዚዳንቱ አክለውም በቀጣናው ያለው ውኃ እና ሃብት በድንበር የተገደበ ሳይሆን የጋራ መፃኢያችንን የሚወስን እንደሆነ ተናግረዋል።

በቀጣናው ልማትን ለማምጣት ከፉክክር በመውጣት በትብብር መሆን እንዳለበት ነው የተናገሩት።
"ዛሬ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቀጣናችን የኩራት ቀን ነው" ያሉት ደግሞ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪየር ናቸው። ሀገራቸው ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ለማግኘት የሚያስችል ስምምነት መፈራረም እንደምትፈልግም አስታውዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም "ግድቡ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የመስዋዕትነት፣ የአንድነትና የቆራጥነት ምልክት ነው፤ ግድቡ ሕዝብ በአንድ ራዕይ ላይ በአንድነት ከቆመ ሃገር ምን መሥራት እንደምትችል ያሳዬ ነው" ብለዋል።

(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

ሕዳሴ - የመቻል ማረጋገጫ ማሕተም የመስከረም 5 ቀን 2018  ዓ.ም  ዕትምኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ሠርቶ ከፍታዋን ለማረጋገጥ የነበራት የሐሳብ ጥንስስ ተስፋን የዘራው በአጼ ኃይለ...
15/09/2025

ሕዳሴ - የመቻል ማረጋገጫ ማሕተም
የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ሠርቶ ከፍታዋን ለማረጋገጥ የነበራት የሐሳብ ጥንስስ ተስፋን የዘራው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይነገራል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነበሩ የተለያዩ መንግሥታት ቅብብሎሽ ግድብ የመገንባት ሐሳቡ ቢቀጥልም የተጀመረው ግን መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነው። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒሥትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያውያን ከተረጂነት ለመውጣት ሕዳሴን በራሳቸው አቅም እንዲሠሩት የጀመሩት ግድብ በአቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ ቀጥሎ ከ14 ዓመታት የግንባታ ጊዜ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተጠናቋል። ይፋዊ ምረቃውም ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሂዷል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ላይ የታሰረው ቀዳሚ ዓላማው የኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጨት ነው። በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባም አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኅይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል። ባለፈው ዓመት ከተገኘው ኀይል 33 በመቶ የሚሆነው ከሕዳሴ ግድብ የተገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል መግለጫ ያሳያል። የኀይል ማመንጫ ግድቡ በሙሉ አቅም ኀይል ማመንጨት ሲጀምር የሀገሪቱን የኀይል ተደራሽነት አሁን ካለበት 54 በመቶ ከማሳደግም ባሻገር በአሳ ሐብት፣ በቱሪዝም፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎችም ዘርፍ የሀገሪቱን ከፍታ እንደሚያሳድግ እምነት ተጥሎበታል።

ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን አሳልፎ ላለመስጠት በተደረገው ጦርነት በዓድዋ የተገለጠው ኢትዮጵያዊው አይበገሬነት እና አንድነት ዛሬም ሕያው መሆኑ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደግሟል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ከዓድዋ ድል ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ጸሐፊ እና የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪ ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) ለድርጅቱ በላኩት ጽሑፍመረጃ አሳውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያለማንም ረዳት፣ አጋዥ፣ ለጋሽ፣ አበዳሪ እና አይዞሽ ባይነት ብቻዋን የተወጣችው እና የተጐናፀፈችው ድል መሆኑን ቀዳሚው ማሳያ አድርገውታል፡፡

የዓድዋ ጦርነት እና የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያዊያን አመላቸውን በጉያቸው፣ ልዩነታቸውን በጓዳቸው ትተው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ላባቸውን፣ ደማቸውን አዋጥተው እና አስተባብረው ያከናዎኑት ዘመን ተሻጋሪ ድል መሆኑነም ዶ/ር ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡

ጸሐፊ እና ተመራማሪው የዓድዋ ድል እና የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሌላኛው ምስጢር ነው ያሉትንም ያስረዳሉ፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ በሀገራቸው እና በሉዓላዊ ግዛታቸው በነጻነት የመወሰን፣ ሦስተኛ ወገን ያወጣውን ሕግ መሰል ቀንበር፣ ውል መሳይ እግረ ሙቅ ያለመቀበል ጀግንነትን ያስተዋወቀ፣ በጥቅሉ የኮሎኒያሊስቶችን ቀንበር የሠበረ፤ ፍትሕን በራስ አቅም ያስከበረ ለመላው ታዳጊ ሀገር ሕዝቦች ትምህርት የሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ድሎች መሆናቸው ማረጋገጫ አድርገዋል፡፡

ሕዳሴ የዳግም ዓድዋ ተምሳሌት መሆኑን የተለያዩ የአፍሪካ እና የሌሎች አህጉራት መሪዎችም አረጋግጠዋል፡፡ የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንድትሠራ ማንም ፍላጎት አልነበረውም፤ ይህም ግድቡ ለምረቃ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዲያልፍ እንዳደረገው ገልጸዋል። ግድቡ ለምረቃ የበቃው ኢትዮጵያውያን ቀድሞውኑ በሚታወቁበት የቁጭት ስሜት ግለት እንደሆነ አንስተዋል።

"ኢትዮጵያውያን አይበገሬዎች ናቸው፡፡ ጠላት ሲገጥማቸው ጥረታቸውን በእጥፍ ይጨምራሉ፡፡ ማግኘት ያለባቸውን ሳያገኙ ወደ ኋላ አይሉም" በማለት በኢትዮጵያውያን አንድነት የተጠናቀቀ ግድብ መሆኑን ጠቁመዋል። ግድቡ የሚያመነጨው ኅይል የሀገሪቱን የኅይል ሽፋን ከማሻሻል በተጨማሪ ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ትብብሯን ለማጠናከር እንደሚያግዛትም ተናግረዋል።
በምረቃው ወቅት የተገኙ የአፍሪካ እና የሌሎች ሀገራት መሪዎችም ሕዳሴ የጽናት ተምሳሌት፣ የአሸናፊነት አርማ፣ የመተባበር ውጤት መሆኑን ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ሕዳሴን የገለጹት የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት እና ለቀጣናው ሀገራት የመገናኛ መንገድ በማለት ነው፡፡ ለግድቡ ዕውን መሆን ኢትዮጵያውያን የከፈሉት ዋጋ ለልማት የማይበገሩ መሆኑ የታየበት እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ግድቡ ኀይል በማመንጨት በዘርፉ ለሚስተዋለው ችግር መፍትሄ ከመሆኑም በላይ ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሕዳሴ በረከት ለደቡብ ሱዳናውያን የገጠር ሰፈሮች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች የሚተርፍ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሀገራቸውም ከግድቡ ኀይል ለመግዛት የሚያስችል ስምምነት እንደምትፈራረም አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐመድ አሊ የሱፍ የሕዳሴው ግድብ የሕልም፣ የጠንካራ ሥራ ባህል እና ብልሃት የተሞላበት አመራር ውጤት ነው ብለዋል፡፡ ሕዳሴ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ ጉልበት፣ ደም እና ላብ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ዜጎችን በተለያየ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና በኀይል አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡ ሕዳሴ ደግሞ ግቡን ለማሳካት ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል አንደኛው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ኅይል ማመንጫ ግድቡ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ ለኤሌክትሪክ ኀይል እና ለሌሎችም የልማት ዘርፎች ትልቅ አቅም እንደሚሆን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

የባርባዶስ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒሥትር ሚያ አሞር ሞትሊ ሕዳሴ አፍሪካውያን እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጠ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ከማንም ምንም ሳይጠብቁ የሠሩት፣ የኢትዮጵያም መቻል ማሳያ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ የካሪቢያን እና የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ ከገለጠችው የይቻላል መንፈስ ትምህርት እንዲወስዱም ጠቁመዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትናንት ቁጭት ማሰሪያ፣ የመጪው ንጋት ማብሰሪያ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረው የንጋት ሃይቅ 74 ትሪሊዮን ሊትር ውኃ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ይህም በጥቁር ሕዝብ ታሪክ የመጀመሪያው ታላቅ ሥራ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ሕዳሴ ጥቁሮች ጀምረው መጨረስ እንደሚችሉ ያረጋገጠ አሻራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 15 ቢሊዮን ብር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሥትሩ፣ ንጋት ከኢትዮጵያ ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት የላቀ ሀብት መያዙን የግዙፍነቱ ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከጥልቅ ጨለማ ያወጣ እና ከእንቅልፍ ያነቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሕዳሴ የአሁኑ ትውልድ ታሪክ ከመሥማት ወደ መሥራት ያሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ትውልድ ጀምሮ ያጠናቀቀው የሕዳሴ ግድብ የዳግም ዓድዋ ተምሳሌት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሥትሩ፤ ይህም የኢትዮጵያ የልመና፣ የስንፍና እና የእንጉርጎሮ ዘመን እንዲባቃ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ለኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ሕዳሴ የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ልክ አይቀሬ መሆኑን ዳግም ያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግባቸው የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ አረጋግጠዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ችግር ይዞ እንደማይመጣ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሕዳሴን የሠራችው ለመበልጸግ፣ አካባቢውን በብርሐን ለመሙላት እና የጥቁር ሕዝብ ታሪክን ለመቀየር እንጂ በፍጹም ወንድሞቿን ለመጉዳት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡ “ኢትዮጵያ ሀቃችሁን አታስቀረም” በማለት ግድቡ ለተፋሰሱ ሀገራት ስጋት እንደማይሆን አረጋግጠዋል፡፡ “የግብጽ ረሃብ፣ የሱዳን ረሃብ እና የሌሎች ወንድሞቻችን ረሃብ እና ችግር የኛም ረሃብ ስለሆነ አብረን ከመብላት እና ከመካፈል ውጭ እኛ ተጠቅመን ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የለንም። ለወደፊት በምንሠራቸው ታላቅ ሥራዎች በትብብር እና በጋራ እንድንቆም ከወዲሁ በአደራ ጭምር ላሳስባቸው እወዳለሁ” በማለት ኢትዮጵያ ዛሬም በጋራ መልማት መርኋ ሆኖ መቀጠሉን አረጋግጠዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

ፍልሰት እና ሰቆቃዉየመስከረም 5 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትምስሙ ሀሰን ይባላል፤ የ25 ዓመት ወጣት ነው:: በምዕራብ ዳርፉር አል - ኑር በምትባል ትንሽ መንደር ነው የተወለደው:: አል - ኑር...
15/09/2025

ፍልሰት እና ሰቆቃዉ
የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

ስሙ ሀሰን ይባላል፤ የ25 ዓመት ወጣት ነው:: በምዕራብ ዳርፉር አል - ኑር በምትባል ትንሽ መንደር ነው የተወለደው:: አል - ኑር (ብርሃን እንደ ማለት ነው) በአንድ ወቅት ልክ እንደ ስሟ የብርሃን እና የተስፋ ምድር ነበረች:: ይሁን እንጂ አሁን ላይ ምድራዊ ሲኦል ሆናለች::

በአካባቢው ካለው እረፍት የለሽ ግጭት በተጨማሪ ተፈጥሮ ፊቷን እንዳዞረችባቸው ወጣቱ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ተናግሯል::
ታዲያ ሀሰን በዚህ ጊዜ ሁሉን ነገር ትቶ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ አደገኛ ከሆኑ የስደት ጉዞዎች አንዱ በሆነው የምሥራቁ መስመር ከሚጓዙት ከመቶ ሺዎች አንዱ ሆነ። ይህ የእርሱ ብቻ ታሪክ አይደለም:: በ2025 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ 238 ሺህ የሚገመቱ እንደ እርሱ ያሉ ግለሰቦች ይህንን ጉዞ አድርገዋል ይላል የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት መረጃ::

ይህም የሚያቃጥሉ በረሃዎችን እና ሞት የሚጠራውን ጨካኙን የኤደን ባሕረ ሰላጤ በማቆራረጥ ወደ አረብ ባሕረ ገብ መሬት የሚደረግ የዘመናችን አደገኛ ጉዞ ነው። በዚህ አደገኛ መስመር ብቻ የሚጓዙ ሕገ ወጥ ስደተኞች ታዲያ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 34 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የወጡ መረጃዎች እና ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ከ123 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ይገኛሉ:: ከ2023 እ.አ.አ ጋር ሲነጻጸር ይህ ቁጥር በ11 ነጥብ አምስት በመቶ መጨመሩን መረጃው ያስነብባል::

ለአብነት እስከ 2025 ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ 11 ሚሊዮን የሚሆኑ ሱዳናውያን ተፈናቅለዋል:: በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። በዓለም ላይ ሁለት ቢሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ወይም ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች መኖሩ ቁጥሩ እንዲጨምር አድርጎታል ይላል መረጃው::

በሶሪያ ከዐሥር ዓመታት በላይ የዘለቀው ግጭት ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል:: የዓለም ፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) በመስከረም 2025 ሪፖርቱ እንዳመላከተው ደግሞ በየመን የቀጠለው ቀውስ በየሳምንቱ ለአዲስ መፈናቀሎች ዋነኛ ምክንያት ሆኗል::

እንደ ሳህል እና ምዕራብ አፍሪካ ባሉ ክልሎች ውስጥ ያለው አካባቢያዊ አለመረጋጋት የማያቋርጥ ስደት እንዲኖር አድርጓል:: በማያንማር የሚገኙ የሮሂንጊ ብሄር ሕዝቦችም ቋሚ ቦታ የሌላቸው ሙሉ በሙሉ ሀገር አልባ ሰደተኛ ሕዝቦች ሆነዋል።

ከጦርነት እና ግጭት በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥም ሌላኛው የስደት ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል:: ባሳለፍነው ነሐሴ ወር እንደ ገዳሪፍ እና ደቡብ ዳርፉር ባሉ በርካታ የሱዳን ግዛቶች ከባድ የጎርፍ አድጋ ተፈጥሯል:: ይህም ከ500 በላይ አባወራዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ አስገድዷል። የድርቅ እና የዝናብ እጥረት መጨመርም የ2025 የፈረንጆች ዓመት ከገባ ወዲህ ለብዙ ሚሊዮን ሰዎች መሰደድ ምክንያቶች ናቸው::

በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) በአየር ንብረት ለውጥ ለሚከሰት ፍልሰት አዲስ መፍትሄ እንዲኖር አሳስቧል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሐመድ አብዲከር በስብሰባው መክፈቻ ላይ በአየር ንብረት ምክንያት የሚፈጠር ስደት እና መፈናቀል ከፈተኛ መሆኑን ተናግረዋል::
የአፍሪካ አህጉር ከዓለም አቀፍ የአየር ብክለት ልቀት መጠን ከአራት በመቶ በታች ድርሻ ቢኖረውም በአየር ንብረት ለውጥ ግን ክፉኛ ከተጎዱት መካከል አንዱ ነው። እየጨመረ የመጣው ድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የአካባቢ መራቆት በአህጉሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለስደት እና ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፤ እያደረገም ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ እንደ ሳህል፣ የአፍሪካ ቀንድ እና የቻድ ሐይቅ ተፋሰስ ባሉ ክልሎች ለሚከሰቱ ስደት እና መፈናቀሎች ዋናኛው ምክንያት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እንዲሁም ድህነት ለበርካታ ዜጎች መፈናቀል እና መሰደድ ሌላኛው ትልቁ ምክንያት መሆኑን የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድረጅት መረጃ አመልክቷል:: ይህ ችግር በላቲን አሜሪካ፣ በአፍሪካ እና በእስያ ባሉ ሀገራት የጠነከረ መሆኑን መረጃው ያስረዳል:: በቬንዙዌላ እና በአፍጋኒስታን የኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት የተሰደደው እና የተፈናቀለው ሕዝብ ቁጥር ጦርነት ካስከተለው ችግር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ሪፖርቶች አመልክተዋል::

በ2025 ጦርነትን እና ግጭትን የሸሹ ሶሪያውያን፣ ዩክሬናውያን እና ደቡብ ሱዳናውያን ሀገራቸውን ለቀው እግራቸው ወደ መራቸው ሀገራት ተሰደዋል:: ከመካከለኛው ምሥራቅ ሶሪያ እና የመን፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ፣ ከሳህል ክልል እና ከመካከለኛው አፍሪካ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዲሁም ከእስያ አፍጋኒስታን እና ማያንማር (በተለይ የሮሂንጊያ ብሄር) ዜጎቻቸው የሚሰደዱባቸው ሀገራት ናቸው::
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ምድር ትልቁ የስደተኞች ቁጥር የተመዘገበው በዩክሬን ነው:: ከስድስት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ተሰደዋል:: ቬንዙዌላ፣ ሆንዱራስ፣ ጓቲማላ እና ኤል ሳልቫዶር ከላቲን አሜሪካ አህጉር በርካታ ሰዎች ለስደት የሚዳረጉባቸው ሀገራት ናቸው::

የሜዲትራኒያንን መስመር፣ የአሜሪካ - ሜክሲኮ ድንበር እና ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን ያለውን “የምሥራቁ መስመር” ስደተኞች ለመተላለፊያነት የሚጠቀሙት ዋነኛ መስመር ነው:: ባሳለፍነው የነሐሴ ወር በምሥራቁ መስመር አንድ ጀልባ በመስጠሟ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም:: ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑም ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ በሰሃራ በረሃ በውኃ ጥም እና በወንበዴዎች በአሰቃቂ መንገድ ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች በርካታ ናቸው::

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ወይም ዓለም አቀፍ ድንበር ያላቋረጡ ነገር ግን ቀያቸውን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የለቀቁ ሰዎች ቁጥር ከ73 ሚሊዮን በላይ ደርሷል:: ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት አፍሪካውያን ስደተኞች ከአህጉራቸው ሳይወጡ በጎረቤት ሀገራት ይጠለላሉ። በተመሳሳይ አብዛኞቹ የሶሪያ ስደተኞች በመካከለኛው ምሥራቅ ይገኛሉ።

ችግሩን ለመቀነስ ሰሜን አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሱ ቢሆንም ችግሩ ግን ሲቀንስ አይሰተዋልም:: ብቸኛው እና ዘላቂ መፍትሄ ሰዎች እንዲሰደዱ የሚያስገድዷቸውን ምክንያቶች መቀነስ እንደሆነ የሪሊፍ ዌብ መረጃ ያመለክታል። ይህ ካልሆነ ግን ዓለም ባንክ እ.አ.አ እስከ 2050 ድረስ ከ200 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለስደት ሊዳረጉ ይችላሉ ሲል ስጋቱን አስቀምጧል::

(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

የብሔራዊ አንድነት አርማ - ሕዳሴየመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትምመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ግንባታው በይፋ የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ...
15/09/2025

የብሔራዊ አንድነት አርማ - ሕዳሴ
የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ግንባታው በይፋ የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም (በመንግሥት፣ በመላው ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን) ርብርብ የተገነባ ነው፤ ይህ የአንድነት አርማ የሆነው ግድብ ጷጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ተመርቋል፡፡

በዓለም ካሉ 20 ግዙፍ ግድቦች አንዱ እና ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍፃሜ መድረስ ፋይዳው ለአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤቶቻችን በተለይም ለታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጭምር ነው።

የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ግድቡ፣ አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው፤ ግድቡ ባለፉት ዓመታት 74 ትሪሊየን ሌትር ውኃ ይዟል። የግድቡ ርዝመት (ከፍታ) 145 ሜትር እና ወደ ጎን ያለው ርዝመት ደግሞ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ነው።

ግድቡን በተመለከተ የእንግሊዝ የዜና ማሠራጫ የሆነው ቢቢሲ በግዙፍነቱ በአፍሪካ ቀዳሚ ነው በማለትም ዘግቧል። የግብፁ አስዋን ግድብ ከሚያመነጨው ኃይል ከእጥፍ በላይ የማመንጨት አቅም እንዳለውም ጠቅሷል። ይህ የሕዳሴ ግድብ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀም በመሆኑ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ቶን ካርበን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንዳይገባ ያደርጋል ሲልም ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ ለአየር ንብረት መጠበቅ የሚኖረውን አወንታዊ አስተዋጽኦ አስፍሯል። ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ቦንድ በመግዛት እና በስጦታ መልክ ገንዘብ በማዋጣት መገንባታቸውንም በአድንቆት አስፍሯል።

ላለፉት 14 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል የተደረገበት የኢትዮጵያዊያን አንድነት የታየበት እና የአፍሪካዊያን ጭምር ኩራት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍፃሜ መብቃቱ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ብስራት ነው።
የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕውቀት፣ ሀብት እና ልምድ ያመጣ ፕሮጀክት ነው። ከ14 ዓመታት በኋላ በመላ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት ለስኬት የበቃው ሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ አድዋ ተብሏል።

በትውልዶች ቅብብል ዕውን የሆነው ሕዳሴ ግድብ ከዚህ እንዲደርስ መላው ኢትዮጵያዊያን ሀብታቸውን እና ላባቸውን አፍስሰውበታል። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ካላት 130 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 60 ሚሊዮኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም፤ የግድቡ ዕውን መሆን ታዲያ በተለይ በጭስ እና በጨለማ ለሚሰቃዩ እናቶች ታላቅ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ቀን ዕውን እንዲሆን በዱር በገደሉ ከአዞ ጋር ታግለው የዓባይን ተፋሰስ ካጠኑ ባለሙያዎች ጀምሮ፣ የጉባን ሀሩር ተቋቁመው ግንባታውን ያሳኩትን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

አመራር ከሰጡ መሪዎች ጀምሮ በየዘርፉ ያለስስት ዕውቀታቸውን እስካበረከቱት ባለሙያዎች ድረስ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ ለግድቡ ግንባታ ከመቀነታቸው እየፈቱ የለገሱ እናቶች እና አረጋዊያን፣ በሰው አገር እየኖሩ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የታገሉ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ሁሉም በየደረጃው የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በሕዳሴ ግድብ ላይ በተፈጠረው ንጋት ሐይቅ ላይ አዳዲስ መርከቦች ወደ ሥራ እንደሚገቡ እና የመርከብ መሠረተ ልማቶችም እየተገነቡ መሆኑን ያስታወቀው ደግሞ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ነው። ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት ንጋት ሐይቅ በኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ ነው፡፡ ይህን የውኃ አካል ለትራንስፖርት እና ለሌሎች ጥቅሞች ለማዋል እየተሠራም ነው፡፡

መርከቦቹ ለተለያዩ ጥቅሞች የሚውሉ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለሕብረተሰቡ ትራንስፖርት፣ ዓሳ ለማጥመድ እንዲሁም ለጎብኚዎች መዝናኛ የሚውሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ሳይሆን በቱሪዝም፣ በዓሳ እርባታ እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፎች አንድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለፍፃሜ መድረስ ለኢትዮጵያዊያን የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የልማትና አካባቢ እንክብካቤ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋሻው ሙሉ ናቸው።

ግድቡ ከፍተኛ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋሻው እንዳሉት ግድቡ የሀገራችን የአንድነት ምልክት፣ ትልቅ የሕዝብ መነሳሳትን የፈጠረ፣ ከህፃን እስከ ሽማግሌ፣ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከተማሪ እስከ ዲያስፖራ፣ ከወታደር እስከ ወዝአደር፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ብሔር፣ ዘር እና ሃይማኖት ሳይለየው በአንድነት አሻራ ያሳረፈበት ነው። በደለል እንዳይሞላ ታዲያ በበጋው ወራት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ መሥራት እንዲሁም በክረምት ወራት ደግሞ ተራሮችን በችግኝ መሸፈን ይገባል፤ በአጠቃላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና እንክብካቤ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

የታሪክ ምሁር እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንዳብራሩት ዓባይ ጉዞውን ሲጀምር በየዓመቱ ከ10 ሚሊዮን ቶን በላይ አፈር እንዲሁም ማዕድናትን ይዞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይጓዝ ነበር። ይህ ሁሉ ክስተት አሁን ላይ አከተመ ብለዋል። “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚለው ታሪክ ማብቃቱን አስረድተዋል።
ምሁሩ እንዳብራሩት ይህን ግድብ ለመገደብ ሲታቀድ ኢትዮጵያን ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለማውጣት ነው። እጅግ በጣም ከፍተኛ መሰናክሎችን እና ችግሮችን አልፎ ለዚህ የደረሰ መሆኑን አስታውሰው “ኢትዮጵያ ጥበብ በተሞላበት ዲፕሎማሲ ዓባይን ለፍሬ ያበቃች ስኬታማ ሀገር ናት” ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ማብራሪያ 86 በመቶ የዓባይ ድርሻ የኢትዮጵያ ነው፤ ይሁን እንጂ ያለአንዳች ጥቅም ነው ዘመናትን ያሳለፍነው። ግብጽ እና መሰል ሀገራት “ዓባይ ከፈጣሪ የተቸረን የኛ ብቻ ሃብት ነው የሚል አመለካከት ተጸናውቷቸው ኖሯል”ም ብለዋል።
የቀደሙት የግብጽ መሪዎች ማንኛውም የግብጽ ዜጋ 18 ዓመት ከሞላው በኋላ ውትድርና መሠልጠን እንዳለበት ያዝዙ እንደነበር የታሪክ ምሁሩ አውስተዋል። ለሀገር ዳር ድንበር ሳይሆን ለዓባይ መሞት እንዳለባቸው ይነገራቸው እንደነበርም ያስረዳሉ።

የግብጽ እመቤት ሕጻን ወልዳ ጡቷን ስታጠባ “ይህ የማጠባህ በዓባይ አማካኝነት ከፈጣሪ ላንተ የተመደበልህ ትሩፋትህ ነው” እያለች እያጠባች ነው የምታሳድገው ይላሉ። ይህ አመለካከት ደግሞ የኔ ብቻ የሚል ትርክትን ወልዶ እንደኖረ ነው የገለጹት።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት፣ በዓሳ እርባታ እና በንግድ እንቅስቃሴ ትልቅ ፍይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል። የዓለም ሀገራት የግድቡን መጠናቀቅ ተከትሎ ኢትዮጵያ የምትባለውን የዓባይ (የታላቁ ሕዳሴ ግድብ) ባለቤት ሄደን መጎብኘት አለብን በሚል እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

“ግድቡ ከ70 በላይ ደሴቶች ያሉበት ነው። ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚሰደደው ዜጋ በሀገሩ የሥራ ዕድል ተፈጥሮለት እንዲሠራ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ከውጭ የምናስገባቸው የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ ዕድል ይሰጣል። ኢትዮጵያ ከሰማይ ውኃ ጠብቃ የምታመርተው ምርት አዋጭ ባለመሆኑ ግድቡ በዓመት አራት ጊዜ እንድናመርት ዕድል የሚሰጥ ነው” ብለዋል። የመስኖ ሥራን እጅግ በዘመነ መንገድ እንድናለማ ያግዛል። ይህም የሀገሪቱን የምግብ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ብሎም ለዓለም ምርቶችን በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የምናገኝበት ዕድልም ከፍተኛ ነው።

ግድቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃብት በመሆኑ ሁሉም በነቃ ተሳትፎ እንዳስገነባው ሁሉ ግድቡን የመጠቀም፣ የመንከባከብ እና የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ለኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በሚሰጠው ጠቀሜታ ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የሀገርን ገቢ ያሳድጋል ብለዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር እና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሰይድ መሐመድ ለበኩር እንደገለፁት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ለዓሳ ሀብት ልማት፣ ለቱሪዝም እና ለሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በብዙ መልክ ያግዛል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ለአብነትም በኃይል፣ በምርት አቅርቦት እንዲሁም እንደ ሀገር የኢንቨስትመት ተወዳዳሪነታችንን የማሳደግ ትልቅ አቅም አለው ብለዋል፡፡

እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ግድቡ የጎረቤት ሀገራትን ከማስተሳሰር ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ከፍተኛ ገቢን ያስገኛል። ይህም በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል። ፋብሪካዎችን እና ኢንዱስትሪዎችን በማንቀሳቀስ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን በማዘመን ከፍተኛ ጥቅምም አለው።

ኢንዱስትሪዎች ከተንቀሳቀሱ ደግሞ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ይፈጠራል፣ ብዙ ምርት ይመረታል፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም ይጨምራሉ። በዚህም የሕዝቡ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል ነው ያሉት።
ከ300 እስከ 400 ዓመታት ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል የተባለው በአፍሪካ ግዙፉን ግድብ መጠበቅ ደግሞ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ተናግረዋል።

(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

የትኛዉ ይሻላል?የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትምበኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እንዳይዙ መታገዱን እናንተ እንዴት ዓያችሁት?እኔ በበኩሌ አዋጁ በፍጥነት ...
15/09/2025

የትኛዉ ይሻላል?
የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እንዳይዙ መታገዱን እናንተ እንዴት ዓያችሁት?

እኔ በበኩሌ አዋጁ በፍጥነት መተግበር አለበት ከሚሉት ጎራ ተሰልፌያለሁ፤ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያቶችን ማቅረብ እችላለሁ::

ተማሪዎች የእጅ ስልካቸውን እንዳይጠቀሙ መከልከል ኋላ ቀርነት ነው ብለው ለሚያስቡ ወገኖቼ በመጠቀማቸው ምን ተጠቀሙ? የሚል ማነጻጸሪያ ጥያቄ ማቅረብ ግድ ይለኛል::
የእጅ ስልካችን ትምህርት በሬዲዮ ከተማርን የቀድሞ ተማሪዎች እና ትምህርታቸውን በፕላዝማ ከተከታተሉ የቅርብ ጊዜ ተማሪዎች በተሻለ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዳለው አይካድም:: ችግሩ ያለው ምን ያህል ተማሪዎች በእጅ ስልካቸው ይማሩበታል? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ላይ ነው::

ምንም እንኳን ሃሳቤ በጥናት የተመለሰ መሆን ቢኖርበትም በአብዛኛው በዙሪያችን የሚገኙ ተማሪዎች የእጅ ስልካቸውን የሚጠቀሙት ለአልባሌ ነገሮች ነው:: ፌስ ቡክ፣ ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም፣ ዩቲዩብ እና መሰል የማኅበራዊ ገጽ ትሥሥሮች ወጣቶችን በተለይም ተማሪዎችን የሌላ ዓለም እሥረኞች እንዳደረጓቸው አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል::

ተማሪዎች ገደብ በሌለው መልኩ በነዚህ የማኅበራዊ ገጾች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ አያሳድርባቸውም ማለት አይቻልም::በእነዚሁ የቲክቶክ እና የፌስ ቡክ መንደሮች ለተማሪዎቹ የሚቀርቡት ጽሑፎች እና ምስሎች አብዛኞቹ በአቻዎቻቸው የተዘጋጁ በመሆናቸው ሃሳቦቻቸውን የሚጠልፉ ገመዶች አይሆኑም ለማለትም ያዳግታል:: የአቻ ግፊት አንዱ የመሰናከያ ገመድ በመሆኑ ማለቴ ነው::
ተማሪዎች በእጃቸው የሚይዟቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮች እየተማሩ ባለበት ወቅት ድንገት ጥሪ ቢያሰሙ (ቢጮሁ) የሌሎች ተማሪዎችንና የአስተማሪያቸውን ሃሳብ አይበርዙም ብሎ መከራከርም ረብ የሌለው ክርክር ይሆናል::

ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሆነው የእጅ ስልካቸውን ድምጽ አልባ (ሳይለንት) ቢያደርጉት እንኳን መልዕክቶች ሲላኩላቸው ስልኮቹ በሚኖራቸው ንዝረት ምክንያት ለመልዕክቱ ጉጉት ማሳደራቸው አይቀርም:: የሚደርሳቸውን መልዕክት እስካላዩት ድረስ አስተማሪዎች ከሚያስተምሩት ትምህርት በበለጠ ቀልባቸውን የሚወስድባቸው ጉዳይ እንደሚሆንም አያጠራጥርም::

ብዙ ወጣት ተማሪዎች በተለይም ወንዶች በእጅ ስልኮቻቸው የውጭ ሀገር እግር ኳስ ጨዋታዎችን ውጤት ይከታተላሉ፤ የዚሁ ውጤትን የመከታተል ፍላጎት ደግሞ በዕለታዊ ትምህርታቸው ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋቸዋል ብሎ አለማሰብ የዋህነት ነው::
በእጅ ስልኮቻቸው የሚደግፏቸውን ክለቦች ውጤት ከመከታተልም ባለፈ በውጤት ግመታ ውርርዶች (ቤቲንግ) ሱስ የሚጠመዱ ታዳጊዎች ቁጥርም “ብዙ” የሚባል ይሆናል:: ትምህርት እና ቁማር (ምንም እንኳን ውርርድ እያልን ስሙን ብናሰማምረውም) ደግሞ ፈጽሞ መሳ ለመሳ የማይሄዱ ተቃራኒ ነገሮች ናቸው::

ተማሪዎች ትምህርት ቤትን ጨምሮ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከእጅ ስልካቸው ጋር ሲያሳልፉ፣ አብረዋቸው ለሚውሉት የክፍል እና የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጊዜ ያጣሉ:: በትምህርት ቤት ውስጥ ከጓደኛ የሚገኘውን አብሮነት እና ፍቅር ማጣት ደግሞ በየትኛውም የሥነ ልቦና መመዘኛ ቢመዘን ጉዳቱ እንደሚያመዝን አያጠራጥርም::

ከእጅ ስልካቸው ጋር ፍቅር የያዛቸው ታዳጊዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ከሚያገኟቸው ጓደኞቻቸው እና አስተማሪዎቻቸው ጋር ከመራራቃቸውም በተጨማሪ ወደ ቤት ሲመለሱም ለቤተሰቦቻቸው የሚኖራቸው ፍቅርም ውስን ይሆናል:: በትምህርት ቤት ውስጥ በትምህርታቸው ምክንያት ለጥቂት ጊዜያት የተራራቁትን የእጅ ስልካቸውን እቤት እንደገቡ መጎርጎር የሚጀምሩ ልጆች ፍቅራቸው ከቤተሰባቸው ይልቅ በእጅ ስልካቸው ውስጥ ለሚያዩት ዝባዝንኬ እንደሆነም እርግጠኞች መሆን እንችላለን::

የእጅ ስልክን በትምህርት ቤቶች ውስጥ ይዞ መገኘት ለኩረጃም በር የሚከፍት ይመስለኛል:: በሙከራ ፈተናም ይሁን በዋናው ፈተና ወቅት ጎበዝ ተማሪዎች ለሰነፎች መልሶችን በእጅ ስልኮቻቸው በመላክ፣ ሰነፎች ይበልጥ ሰንፈው የሚቀጥሉበት ሁኔታም ይፈጠራል::

ተማሪዎች የእጅ ስልክ መያዛቸው ጉዳት እንጂ ፈጽሞ ጠቀሜታ የለውም የሚል ጭፍን ሃሳብ እንደሌለኝ በጽሑፌ መግቢያ ላይ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፤ ይልቁንም በአንጻራዊነት ስናየው ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ በሚይዙት የእጅ ስልካቸው ከሚጠቀሙበት ይልቅ የሚጎዷቸው ነገሮች ይበዛሉ የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ:: ማሳያዎችን አሁንም እቀጥላለሁ::
በእጅ ስልካቸው ላይ ቁንጽል መረጃዎችን በፍጥነት ማግኘት እና ማንበብ የለመዱ ተማሪዎች ጥልቀት ላላቸው መረጃዎች ፍላጎትም ሆነ ጊዜ አይኖራቸውም::ሁሌም በውስጣቸው ያለውን ዕውቀት ሳይሆን የእጅ ስልካቸውን ዋቢ የሚያደርጉ ተማሪዎች በውስጣቸው የሚቋጥሩት ብዙም የክህሎት ስንቅ አይኖራቸውም::

በኔ የተማሪነት ዘመን ብዙ በማንበብ ብዙ ዕውቀት የሚሸምቱ ተማሪዎች (ሸምዳጆች እንላቸዋለን) ነበሩ፤እኛ እነዚህን ልጆች ሸምዳጆች እያልን ብንተቻቸውም እነሱ ግን ደብተሮቻቸውንም ሆነ መጸሐፎችን አብዝተው በማንበብ በብዙ የሚበልጡን ጎበዝ ተማሪዎች ናቸው:: የእጅ ስልኮቻቸው ከእጃቸው የማይለያቸው የአሁን ዘመን ተማሪዎች ግን ሸምድደው በውስጣቸው ከሚያስቀምጡት ይልቅ ከሞባይላቸው ላይ መረጃዎችን ለማግኘት ሲፈጥኑ ይስተዋላሉ::

በእጅ ስልካቸው ቁምነገርን ሳይሆን ጌሞችን ሲጫወቱ የሚውሉ ልጆች ደግሞ ይሄው ሱሳቸው ትምህርት ቤት ድረስ ተከትሏቸው በመሄዱ አስተማሪ ወጥቶ አስተማሪ እስኪተካ ባለው ጊዜ ሳይቀር ጌም የሚጫወቱ ሱሰኞች ይሆናሉ::

የጌሞች እና የእጅ ስልኮችን የመነካካት ሱስ ደግሞ ከሰው ተነጥሎ በራስ ዓለም ውስጥ መኖርን ያላምዳል::እነኚህ ክፉ ልማዶች ደግሞ ልጆችን በራሳቸው ምህዋር እንዲሽከረከሩ ከማድረጉም በላይ ሽክርክሪታቸው አጠገባቸው ያለውን እውነት ሳይቀር ስለሚደብቅባቸው በሥነ ልቦና ጎዶሎ ይሆናሉ::

በእነዚህ እና በሌሎችም መስፈሪያዎች ስናየው ተማሪዎች የእጅ ስልክ ይዘው ትምህርት ቤት ከሚገቡ ይልቅ የእጅ ስልክ አለመያዛቸው ይጠቅማቸዋል:: ወይም ደግሞ ተማሪዎች የእጅ ስልካቸውን ከሱስ በጸዳ መልኩ በአግባቡ ይጠቀሙበት ዘንድ አማራጮችን መፈለግ ጥሩ መፍትሔ ይሆናል::

በርካታ የዘመኑ ተማሪዎች ጫት፣ ሲጃራ እና ሀሺሽን ለመሰሉ ሱሶች ሲጋለጡ በእጃቸው የሚይዟቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ምንም ሚና አልነበራቸውም ብሎ ማሰቡም ስህተት ነው:: በአለባበስ፣ በአነጋገር፣ በአመጋገብ እና በሌሎችም የኛ በሆኑ ነገሮች ላይ ተማሪ ልጆች ከባሕላቸው ሲያፈነግጡ እያየን በስልካቸው የሚያዩት ነገር ምንም ለውጥ አላሳደረባቸውም ብሎ ማሰብም የዋህነት ብቻ ሳይሆን ስህተትም ጭምር ነው::

ተማሪ እና ወጣት የሆኑ ልጆች በሚይዟቸው ስልኮች ዙሪያ የቤተሰብ ክትትል እምብዛም በመሆኑ የወሲብ ቪዲዮዎችን (ፖርኖግራፊ) በማየት ጭምር ከኢትዮጵያዊ እሴቶች ላፈነገጡ ስህተቶች እና ላልተፈለገ እርግዝናም ጭምር እንደሚጋለጡ ነጭ ነጩን መነጋገር ይኖርብናል::
የእጅ ስልኮቻቸው ጥገኛ የሆኑ ተማሪዎች ስለ ሀገራቸው እና ስለ ሕዝባቸው በመጸሐፍ መልክ የተከተቡ ታሪኮችን የማወቅ ዕድላቸው ጠባብ ነው:: ለእነዚህ ዓይነት ወጣቶች ከአድዋ ታሪችን ይልቅ የሆሊውድ እና ቦሊውድ ፊልሞች እውነተኛ ታሪኮች ይመስሏቸዋል:: ከኃይሌ ገብረ ሥላሴ ድንቅ የአትሌቲክስ ገድሎች ይልቅ የጀስቲን ቢበር ኪናዊ ውድቀት ያሳስባቸዋል::
የእጅ ስልኮቻቸው ጥገኛ የሆኑ ተማሪዎች የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ከማወቅ ይልቅ ከአድማሱ ባሻገር ያሉትን የውጭ ሀገር ከያኒያን እና የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ማወቅ ይበልጥ አዋቂነት ይመስላቸዋል::

በእጅ ስልኮቻቸው ዙሪያ የታጠሩ ተማሪዎች አራቱን የሒሳብ መደቦች ማለትም መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት እና ማካፈልን በህሊናቸው ከማስላት ይልቅ በእጅ ስልካቸው ላይ ባለው ሒሳብ መሥሪያ (ካልኩሌተር) ቁጥር ሲያሰሉ ይስተዋላሉ:: በዚህም ምክንያት የሒሳብ ዕውቀታቸው ምንም የሚባል ነው:: የታክሲ መልሳቸውን እንኳን ለማወቅ ሞባይላቸው ከኪሳቸው መዥረጥ የሚያደርጉ ከቁጥር የሸፈቱ አላዋቂዎች ይሆናሉ::

መቼም ትዝብቴ ሁሉንም የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ተማሪዎች እንዳልሆነ ግልጽ ነው:: ግን ደግሞ በሞባይል ስልኮቻቸው ምክንያት በደብተሮቻቸው ላይ ያለውን የጊዜ ቤት ቁጥሮችን እንኳን የማያውቁ ብዙ ተማሪዎች እንዳሉ እሙን ነው::

እኔ ተማሪዎች ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮቻቸውን ይዘው ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዳቸው ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል ባይ ነኝ፤ ለዚህም ምክንያት ያልኩትን በከፊል ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፤ ከኔ በተቃራኒ ሃሳብ ያለው ደግሞ ሃሳቡን በማንሸራሸር እንማማርበት ዘንድ ጋብዣለሁ:: ለሁሉም የሀገራችን ተማሪዎች 2018 ዓ.ም መልካም የዕውቀት መገብያ ዓመት እንዲሆንላቸው ምኞቴ ነው::

(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

ለዓላማ መጽናትየመስከረም 5 ቀን 2018 “በትምህርቴ የላቀ ውጤት እንዳመጣ መምህሮቼ እና ቤተሰቦች   ትልቅ ቦታ አላቸው!” በማለት ሐሳቡን የጀመረልን ተማሪ  ደግነት ታረቀኝ ይባላል፡፡ ትው...
15/09/2025

ለዓላማ መጽናት
የመስከረም 5 ቀን 2018

“በትምህርቴ የላቀ ውጤት እንዳመጣ መምህሮቼ እና ቤተሰቦች ትልቅ ቦታ አላቸው!” በማለት ሐሳቡን የጀመረልን ተማሪ ደግነት ታረቀኝ ይባላል፡፡ ትውልድ እና ዕድገቱ በደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ ዝሀ ቀበሌ የሆነው ተማሪ ደግነት ዕድሜው ለትምህርት ደርሶ ት/ቤት እስኪገባ ድረስ የታላቅ እህቱን ደብተር እና መጽሐፍ እየተቀበለ ፊደል መለየት እንደቻለ ያስታውሳል፡፡ ይህም በሰባት ዓመቱ አንደኛ ክፍል ሲገባ ፊደላትን ለማወቅ ቀላል ሆነለት፡፡ በትምህርት ዓመቱ ማጠናቀቂያም 8ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ 2ኛ ክፍል ተዛወረ፡፡ እስከ ስድስተኛ ክፍል በነበሩት የክፍል ደረጃዎችም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ለቆ አያውቅም፡፡

የመምህራን እና የቤተሰቦቹ ድጋፍ እንዳልተለየው የሚናገረው ተማሪ ደግነት በተለይ አጎቱ አጋዥ መጽሐፍትን እና ሌሎች ለትምህርቱ የሚያግዙትን ቁሳቁሶች ገዝቶ እንደሰጠው ያስታውሳል፡፡ ታዲያ ያኔ ደግነት ለሚወደው ትመህርቱ አቅም የሚፈጥርለት ግብዓት በማግኘቱ በደስታ ስሜት አጐቱን “ተምሬ ስጨርስ ያደረግህልኝን ውለታ ለመመለስ ያብቃኝ!” በማለት ምስጋናውን ቃል በመግባት ገለፀለት፡፡ አጐቱም በአፀፋው “የኔን ውለታ የምትመልስልኝ አንደኛ ስትወጣ ነው” በማለት ነገ ሳይሆን ዛሬ በትምህርት ውጤቱ እንዲያረጋግጥለት ቃል አስገባው፡፡

ከባድ አደራና ኃላፊነት የተቀበለው ደግነት የአጐቱን ቃል ጠብቆ ከድሮው በበለጠ ትመህርቱን በአግባቡ ተከታተለ፤ ሰባተኛ ክፍል በአንደኛው መንፈቀ ዓመት በዘጠኝ የትምህርት ዓይነቶች /ከ900 ውጤት/ 840 በማምጣት ሁለተኛ ደረጃን ያዘ፡፡ ይሁን እንጂ ያጐቱን አደራ ባለመወጣቱ ይበልጥ ቁጭት ተፈጥሮበት የበለጠ በማንበብ 847 ውጤት በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃን በመያዝ ወደ 8ኛ ክፍል ተዘዋወረ፡፡ አደራውን የተወጣው ደግነት አጎቱን ጨምሮ የሌሎች ቤተሰቦቹ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ደግነት የሚደረግለትን ማበረታቻ ምርኩዝ አድርጐ ደረጃውን አስጠብቆ መገስገሱን ቀጠለ፡፡
ይሁንና በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም እጦት በ2016 ዓ.ም ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው ነበር፡፡ ከነዚህ ተማሪዎች መካከል ደግሞ ደግነት አንዱ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ትምህርት ቤት ሄዶ መማር፣ የናፈቁትን መምህራን ማግኘት ቀረ፡፡ ይህን ወቅትም ሲያስታውሰው “በተለይ የፈተና ወቅት እና ውጤት የሚሰጥበትን ጊዜ ሳስበው አዝን ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከዚህ በኋላ ትምህርት ባይቀጥልስ? የሚል ጭንቀት ይስማኝ ነበር” በማለት ነበር፡፡

ደግነት ትምህርቱን ካቋረጠ ከአንድ ዓመት በኋላ /በ2017/ ዓ.ም ከአጐቱ ወደ ባሕር ዳር በማቅናት በግዮን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ1ዐኛ ክፍል ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ከት/ቤቱ እና ከጓደኞቹ ቢርቅም፣ ከወላጆቹ ቢለይም የነበረውን ብቃቱን አሳድጐ በአንደኛው መንፈቀ ዓመት 94 ነጥብ ሁለት በማምጣት አንደኛ ደረጃ እንዲሁም በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት 95 ነጥብ አምስት በማምጣት 2ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ 11 ክፍል ተዛውሯል፡፡

“አንድ ዓመት በማቋረጤ ባዝንም ተስፋ አልቆረጥሁም ነበር፡፡ ቀን ተመልሶ እማራለሁ፡፡ አንድ ቀን ትምህርት እጀመራለሁ! የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ ያልሁት አልቀረም አሁን ትምህርቴን በመቀጠሌ በጣም ደስተኛ ነኝ!” በማለት በደስታ ስሜት አስተያየቱን ሰጥቶናል፡፡
ለደግነት የጥናት እና የክፍል ውስጥ ትምህርት ተሞክሮውን እንዲያካፍለን ጥያቄ አንስተንለት ነበር፡፡ “በየዕለቱ በክፍል ውስጥ የተማርሁትን ዛሬ ምን ተማርሁ? በማለት አጠናለሁ፡፡ ጥያቄዬ ከተመለሰልኝ በኋላ ለቀጣይ ቀን የምንማረውን ደግሞ በቀላሉ እንዲገባኝ ቀድሜ አጠናለሁ” ብሎናል፡፡

“እኔ ፈተና ደረሰ ብዬ አልሯሯጥም፡፡ ‘ሙሽራ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ' የሚለውን አባባል ሳይሆን 'ሙሽራ ሳይመጣ በርበሬ ቀንጥሱ' አይነት መንገድ ነው የምከተል” በማለት የጥናት ስልቱን አካፍሎናል፡፡
ደግነት በግል እንደሚያጠናው ሁሉ የጋራ ጥናትንም ያደርጋል፡፡ “ብቻዬን በቂ ግንዛቤ ላልይዝ እችላለሁ፡፡ ምክንያቴ ደግሞ መምህራን ሲያስተምሩ እኔ የእነሱን ሀሳብ በትክክል ላልረዳ እችላለሁ፡፡ በጋራ ሳጠና ግን እኔ ባልተረዳሁበት መንገድ ሌሎች ጓደኞቼ ተገንዝበው ይሆናል፡፡ እናም በጋራ ስናጠና ነገሮችን በብዙ አማራጮች ልረዳ እችላለሁ” ብሎናል፡፡

ደግነት በክፍል ውስጥ ሲማርም ያልገባው ካለ መምህራንን በክፍል ውስጥ ጠይቆ እንዲሁም ማጣቀሻ መጻሕፍትን በማንበብ ይረዳል፡፡ “ማንኛው ሰው በትምህርቱም ሆነ በሥራ ዓለም ለውጤታማነት ተፎካካሪ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ካስቀመጠው ራእይ መድረስ ይቻላል” የሚል ጽኑ እምነት ያለው ደግነት፤ ዘንድሮ ከ98 በመቶ በላይ ለማምት አቅዷል፡፡
ደግነት በመጨረሻም ባለፉት ዓመታት ትምህርት በተቋረጠባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ሰላም ሰፍኖ እንደሱ የትምህርት ዕድል እንዲያኙ ተመኝቶላቸዋል፡፡

መረጃ
ለፈተና ለመዘጋጀት የሚጠቅሙ ነጥቦች

ምናልባት ነገሮችን ቦታ ቦታ ለማስያዝና እቅድ ለማውጣት የምታጠፉት ጊዜ የባከነ ሊመስላችሁ ይችላል። ነገር ግን እውነታው በተቃራኒው ነው። ምክንያቱም ምን ማጥናት እንዳለባችሁና መቼ ማጥናት እንዳለባችሁ እቅዳችሁ ይነግራችኋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምን ያክል እንደተጓዛችሁ ለመመዝገብና ለመከታተል ይረዳል።
የትኞቹን ማስታወሻ ደብተሮች መቼ መመልከት እንዳለባችሁ፣ የትኞቹን መጻህፍት ለተጨማሪ ማብራሪያ እንደምትጠቀሙ እንዲሁም የፈተና ጥያቄዎችን መቼ መለማመድ እንዳለባችሁ በእቅድ ውስጥ ማስገባት ውጤታማ ያደርጋል።
እዚህ ጋር መርሳት የሌለብን ለእረፍትና አካላዊ እንቅስቃሴም ቦታ መስጠት እንዳለብን ነ
 ከፋፍሎ ማጥናት፦
በአንድ የትምህርት ዓይነት ላይ 10 ሰዓት ሙሉ ከማሳለፍ በየቀኑ አንድ ሰዓት በማጥናት በ10 ቀን መጨረስ ውጤታማ ያደርጋል።
ያጠናነውን ለማስታወስና በቀላሉ ለመሸምደድ ጭንቅላት ጊዜ ይፈልጋል። ከፋፍሎ ማጥናት ደግሞ ለዚህ ፍቱን መድሃኒት ነው።
 ራሳችሁን ቶሎ ቶሎ ፈትኑ፦
የሥነ አዕምሮ ጥናት ባለሙያዎች እንደሚሉት የማስታወስ ችሎታን ለማዳበርና በራስ መተማመንን ለመጨመር ራስን መፈተን ውጤታማ ያደርጋል።
ከዚህ በተጨማሪ እየተዘጋጀንበት ያለነውን ጉዳይ በደንብ እንድናውቀው ከማድረጉ በተጨማሪ የረሳናቸው አልያም የዘለልናቸው ርዕሶችን ለመለየት ይረዳናል።
 መምህር መሆን፦
ከባዱን የክለሳና ራሳችሁን የመፈተን ሥራውን ካከናወናችሁ በኋላ ጓደኞቻችሁን ሰብሰብ አድርጋችሁ ራሳችሁን በመምህር ቦታ አድርጋችሁ እውቀታችሁን ለማካፈል ሞክሩ።
ይህ ዘዴ ምን ያህል እንደምታስታውሱ ለማወቅ ከመርዳቱ በተጨማሪ ጓደኞቻችሁንም ትጠቅሟቸዋላችሁ።
 ከተንቀሳቃሽ ስልካችሁ ራቅ በሉ፦
ስልክ በጣም ብዙ ጥቅም አለው። ነገር ግን በጥናት ወቅት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። በተለይ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምትጠቀሙ ከሆነ።
ብዙ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ብዙ ጊዜያቸውን ስልካቸው ላይ የሚያሳልፉ ተማሪዎች የትምህርት ውጤታቸው ሁሌም ቢሆን ዝቅ ያለ ነው። እናም ብትችሉ ስልካችሁን ከአጠገባችሁአታድርጉ።
ውጤታማ የክለሳ ጥናት ማለት እረፍት አልባ ጥናት ማለት አይደለም። በጥናት መሀል መሀል ላይ ጥሩ አየር ለማግኘትና ሰውነታችንን ለማፍታታት ወጣ ብሎ እንቅስቃሴ ማድረግ የማስታወስ ችሎታን በደንብ ከፍ ያደርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሰውነታችን እና ጭንቅላታችን በእጅጉ የተሳሰሩ በመሆናቸው እንቅስቃሴ ስናደርግ የደም ዝውውራችን ይስተካከላል፤ ይህ ደግሞ በቂ ኦክስጅን ወደ ጭንቅላታችን እንዲሄድ ይረዳል።
አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግም ጭንቀትን መከላከልና በራስ መተማመንን ይጨምራል፡፡

(ሙሉ ዓብይ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም - https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

Address

Bahir Dar

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when አሚኮ በኲር/AMECO BEKUR posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to አሚኮ በኲር/AMECO BEKUR:

Share