
03/07/2025
በቦዲቲ ከተማ አስተዳደር የወላይታ ልማት ማህበር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የእስካሁን ስራ አፈጻጸም እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሄደ።
ቦዲቲ ፤ ሰኔ ፤26/2017 ዓ.ም በወላይታ ዞን በቦዲቲ ከተማ አስተዳደር የወላይታ ልማት ማህበር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የእስካሁን ስራ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
ውይይቱ በዋናነት የማህበሩ አጠቃላይ የገቢ ስራዎችን በሚመለከት እና በከተማ ደረጃ የሚካሄደውን የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ የሚካሄድበትን ጊዜ ለመወሰን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል።
የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና በከተማው የወ/ል/ማህበር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጳውሎስ በቀለ መድረኩን መርተዋል።
ክቡር ከንቲባ አቶ ጳውሎስ በቀለ በመድረኩ እንደገለፁት ከወላይታ አልፎ በሀገር ደረጃ ዘርፈብዙ የሆኑ የልማት ስራዎችን በብቃት እያከናወነ የሚገኘው የወላይታ ልማት ማህበር በገቢ አቅሙ እንዲያድግ መደገፍ የሁሉም ህብረተሰብ ሀላፊነት እንደሆነ ገልጿል።
ስለዚህ ልማት ማህበሩ በገቢ አቅሙ አድጎ በቀጣይ ከዚህ በበለጠ ስራዎችን መስራት እንዲችል ኮሚቴው ከገቢ አሰባሰብ ጋር ባሉ ስራዎች ላይ ሀላፊነት ወስዶ በተጠያቂነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስ አሳስቧል።
በተለይ የገቢ ስራን በሚመለከት በ2024 እአአ/2016 ዓ.ም ክንውን ወቅት በጉድለት የተገመገሙ ጉዳዮች በውጤት መፈጸም እንዲችል በ2025 እአአ/2017 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ተይዘው በትኩረት መመራት አለባቸው ተብሏል።
ለወላይታ ልማት ማህበር ገቢ አሰባሰብ ስራ እንዲረዳና ጤናማ የገቢ አሰባሰብ ስራ እንዲኖር ታስቦ በተለያዩ ጊዜያት የተሰራጩ ደረሰኞች በአሰራር መሰረት ተመላሽ በሚደረጉበት ሁኔታ ላይ ኮሚቴው ሀላፊነት ወስዶ እንዲሄድ አመራርም ተሰጥቷል።
የወላይታ ልማት ማህበር የሚያከናውናቸው ሁሉም ተግባራት የጠቅላላ ህብረተሰብ ጥቅምን መሰረት ያደረጉ እንደሆኑ የተናገሩት ክቡር ከንቲባው አንዳንድ ተቋማትና አካላት ዘንድ የሚገኙ ውዝፍ እዳዎች በአፋጣኝ ተመልሰው ገቢ እንዲሆኑ ኮሚቴው አቋም ይዞ ቀጣይ ስራዎችን እንዲመራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።